Saturday, 28 September 2013

በማሰርና ማደናቀፍ የታጀበው ሰላማዊ ሰልፋችን በታቀደለት ዕለት በድምቀት ይካሄዳል!!! – በአንድነትና በ33ቱ ፓርቲዎች በጋራ የተሠጠ ጋዜጣዊ መግለጫ


አንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ ለሶስት ወራት የሚቆይ ህዝባዊ ንቅናቄ በስትራቴጅው መሰረት በመጀመር፤ በመላው አገሪቱ የሚገኙ አባላቶቹንና ደጋፊዎቹን በማንቀሳቀስ ሕዝቡን ያሳተፈ ትግል በአዲስ አበባና ከአዲስ አበባ ውጭ በሚገኙ ዋና ዋና ከተሞች የተቃውሞ ሰልፎችንና ህዝባዊ ስብሰባዎችን ማከናወኑ የሚታወቅ ነው፡፡ የሚልዮኖች ድምጽ ለነፃነት በሚል መሪ ቃል የተጀመረው ይህ ህዝባዊ ንቅናቄ አራት መሰረታዊ ጥያቄዎችንና ወቅታዊ ጉዳዮችን ያነገበ ሲሆን እንደ ሁልጊዜውም ፓርቲው ሰላማዊነቱን በጠበቀ መልኩ ነገር ግን ሕጋዊ መብቱን ሳያስነካ፤ መከፈል የሚገባውን መስዋዕትነት በመክፈልና በቁርጠኝነት ንቅናቄውን በታቀደለት መሰረት ከአባላቱና አመራሩ ጋር በመሆን ለማከናወን ችሏል፡፡
አገሪቱን በማስተዳደር ላይ የሚገኘው ገዥ ሀይል በሰላማዊ ህዝባዊ ንቅናቄዎች ለሚነሱ ጥያቄዎች አፋጣኝ ምላሽ ከመስጠትና በተነሱ ጉዳዮች ዙሪያ ለመነጋገር በርን ከመክፈት ይልቅ ዙሪያ ጥምጥም በመሄድ ለጥያቄዎቹ አስተጋቢዎች የተለየ መልክ ለመፍጠር የሚያደርገው ሩጫ እንደተጠበቀ ሆኖ በህገ መንግስቱ በግልጽ የተቀመጡ ሰላማዊ ሰልፍ የማድረግ፣ የመሰብሰብና አቤቱታ የማቅረብ መብትን በአደባባይ እየጨፈለቀና እነዚህ መብቶች ይከበሩ ዘንድ የሚጠይቁ አባላቶቻችንን ከህግ አግባብ ውጪ በገፍ እያሰረም ቢሆን ህዝባችን ጋር ለመድረስና ተቃውሞ ድምፃችንን ከፍ አድርገን ማሰማት ችለናል፡፡
በጎንደርና ደሴ ከተማ በ7/11/2005 የጀመርናቸው የተቀውሞ ሰልፎች በባህርዳር፣ በአርባምንጭ፣ በጅንካ፣ በአዳማ፣ በፍቼ በተሳካ ሁኔታ የተካሄዱ ሲሆን በመቀሌና ባሌ ሮቤ በከፍተኛ ጫናና ህገወትነት ሳካሄዱ ቀርተዋል፡፡ በወላይታ ሶዶና አዲስ አበባ ህዝባዊ ስብሰባዎች ተከናውነዋል፡፡
ከላይ በጠቀስናቸው ከተሚች ሰላማዊ ሰልፎቹን ለማሰናከል ሃላፊዎቹ የየአካባቢዎቹን ሚሊሻዎች፣ የደንነት ሰዎች፣ ታጣቂዎችና ፖሊሶች በመጠቀም አባላቶቻችንን አስረዋል፣ አስፈራርተዋል፣ ደብድበዋል፣ አዋክበዋል፡፡ ከአንድ የመንግስት አካል በማይጠበቅ መልኩም አመራሮቻችንን አግተዋል፣ የተለጠፉ የሰላማዊ ሰልፍ ጥሪ ወረቀቶችን እንዲቀደዱ በማድረግና ህዝቡ በሰልፎቹ እንዳይገኝ በካድሬዎች አማካኝነት የቤት ለቤት ቅስቀሳ ከማካሄዳቸው በተጨማሪ የትራንስፖርት እንቅስቃሴ እንዳይኖር በማድረግ ከየከተሞቹ አቅራቢያ ከሚገኙ ወረዳዎች ዜጎች ድምጻቸውን ለማሰማት እንዳይመጡ እንቅፋት ፈጥረዋል፡፡ በተንቀሳቀስንባቸው አካባቢዎች ሁሉ ገዢው ፓርቲ ከህዝብ የተነጠለ መሆኑንና ህዝቡን እየመራሁ ነው የሚለው ህዝብን በማሸማቀቅ እንደሆነ መገንዘብ ችለናል፡፡
የመጀመሪው ዙር የሶስት ወር ሕዝባዊ ንቅናቄችን ከ33ቱ ፓርቲዎች ጋር በመሆን በአዲስ አበባ እንደሚጠናቀቅ በገለፅነው መሰረትም የተለያዩ እንቅስቃሴዎችንና ዝግጅቶቸን ስናደርግ ቆይተናል፡፡ በሕገ-መንግሥቱ አንቀጽ 3ዐ ተራ ቁጥር (1) መሰረት ዜጎች የመሰብሰብና በጋራ ሠላማዊ ሠልፍ ማድረግ እንደሚችሉ በተደነገገው መሠረት አንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትሕ ፓርቲ (አንድነት) በ24/12/2ዐዐ5 በተፃፈ ደብዳቤ ሕጉ የሚጠይቀውን አሟልቶ የተቃውሞ ሠላማዊ ሠልፍ መስከረም 5 ቀን 2ዐዐ6 ዓ.ም በመስቀል አደባባይ ለማድረግ መወሰናችንን ለአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የሠላማዊ ሠልፍ ማሳወቂያ ክፍል አሳውቀናል፡፡ ሆኖም በ12 ሰዓት ውስጥ መልስ ባለማግኘታችን ስለ ጉዳዩ ለማጣራት ከመስተዳድሩ የከንቲባው ጽ/ቤት ኃላፊ ጋር ተገናኝተን ሠፊ ውይይት ካደረግን በኋላ የጽሕፈት ቤቱ ኃላፊ በወቅቱ በመስቀል አደባባይ ለግንባታ ሥራ ተብሎ አካባቢው በቆርቆሮ የታጠረ ስለሆነ ጊዜ ተገኝቶ ቆርቆሮዎቹ ተነስተው ለጥበቃ አመቺ እስከሚሆን ድረስ የሠላማዊ ሠልፉ ከመስቀል በዓል በኋላ እንዲደረግ ስለጠየቁንና እንዲሁም የትምህርት ቤቶች መክፈቻ ወቅት ከመሆኑም በተጨማሪ በአካባቢውም ከአዲስ ዘመን መለወጫ ጋር በተያያዘ ብዙ ባዛሮች የሚስተናገዱበት ጊዜ በመሆኑ ጊዜው እንዲለወጥ የሚሉ ምክንያቶች በመቅረባቸው በመስቀል አደባባይ ለማድረግ የማንችል መሆኑን ቢነግሩንም በአደባባዩ ግን፡-
1ኛ. ነሐሴ 19 ቀን 2ዐዐ5 ዓ.ም የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ሙት ዓመት ምክንያት በማድረግ ሕዝባዊ ስብሰባና ሠላማዊ ሠልፍ የተካሄደበት መሆኑ፤
2ኛ. ነሐሴ 26 ቀን 2ዐዐ5 ዓ.ም የኢትዮጵያ የኃይማኖቶች ተቋማት ጉባኤ ሠላማዊ ሠልፍ እንዳካሄዱበት እየታወቀ የተሰጡን ምክንያቶች ውሃ የማይቋጥሩና አድሏዊ መሆናቸውን ብናምንም ሆደ ሰፊ በመሆንና እስከመጨረሻው ለመሄድ በማሰብ ሠላማዊ ሠልፉ ወደ መስከረም 19 ቀን 2ዐዐ6 ዓ.ም እንዲተላለፍ አድርገናል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ መስተዳድር የከንቲባው ጽ/ቤት መስከረም 3 ቀን 2ዐዐ6 ዓ.ም ሠላማዊ ሠልፉን መስከረም 19 ቀን ማድረግ እንደምንችል ለዚሁ ተግባር በተዘጋጀው ቅጽ ሲያሳውቀን በቅፁ ላይ መሠረታዊ የሆነውን የሠላማዊ ሠልፉን የመዳረሻ ቦታ ክፍት (ዳሽ) በማድረግ ቀደም ስንል የተስማማንበት ቦታ መስቀል አደባባይን ሳይጠቀስ ቀረ፡፡ ፓርቲያችንም ይህ ተገቢ ያለመሆኑንና የመስተዳድሩን ተዓማኒነት የሚያሳጣው ስለሆነ ሠላማዊ ሠልፉን በመስቀል አደባባይ እንድናደርግ እንዲወሰንልን በተደጋጋሚ ብናሳስብም ተወያይተን መፍትሔ እንሰጣለን በማለት መልሱን በአስር ቀናት ከአዘገዩ በኋላ በቁ.አ.አ/ከጽ/1ዐ/3ዐ.4/12 ሠላማዊ ሠልፉን በጃንሜዳ እንድናደርግ መወሰኑን ገለፁልን፡፡ ሆኖም በዚህ ደበዳቤ መጨረሻ ላይ ‹‹… ከመስቀል አደባባይ ውጭ ሌላ አማራጭ ካላችሁ ማቅረብ እንደሚቻል እናሳስባለን›› ባሉት መሠረት የፓርቲው አመራር በጉዳዩ ላይ ሠፋ ያለ ውይይት ከአደረገ በኋላ ከላይ በጠቀስናቸው ምክንያቶች የተሰጠን መልስ በመስቀል አደባባይ ሠላማዊ ሠልፍ የማድረግ መብታችንን የጣሰ፣ የደፈጠጠ፣ ኢ-ፍትሓዊና አድሎአዊ መሆኑን ሙሉ በሙሉ ብናምንም አሁንም መስተዳድሩ እውነት ልማት አስጨንቆት ነው ወይስ ሰላማዊ ሰልፎችን በወረቀት ብቻ ዕውቅና በመስጠት ሌሎችን የማፈን ተግባር የሚለውን በተጨባጭ ለመፈተሽ የተፈቀደልን ጃንሜዳ በአዋጅ ቁጥር 3/1983 ዓ.ም ለሠላማዊ ሠልፍና የተከለከሉ ሥፍራዎች በሚለው አንቀጽ ሥር ‹‹ማንኛውም ሠላማዊ ሠልፍ ወይም ሕዝባዊ የፖለቲካ ስብሰባ በጦር ኃይሎች፣ በጥበቃና የሕዝብን ሠላምና ደህንነት በሚቆጣጠሩ የመንግሥት የሥራ ክፍሎች አካባቢ 5ዐዐ ሜትር ርቀት ውስጥ ሊደረግ አይችልም›› የሚለውን በመጥቀስ ጃንሜዳን የማንቀበልበትን ምክንያቶች አቅርበናል፡፡ በዚህም መሰረት፡-
ሀ) በጃን ሜዳ ዋና መግቢያ በር ፊት ለፊት የመከላከያ ዩኒቨርስቲ በመኖሩ፤
ለ) በጃን ሜዳ ሁለተኛ በር የቀድሞ 3ኛ ሻለቃ ማዕከላዊ እዝ በመኖሩ፤
ሐ) በጃን ሜዳ 3ኛ በር የአራዳና የየካ ክፍለ ከተማ የፌዴራል መምሪያ የሚገኙ ስለሆነ ይህን ሥፍራ ለሠላሚዊ ሠልፍ መፍቀድ አዋጅን የሚጥስ በመሆኑ ትክክል እንዳልሆነ እና እኛም የሕግ ጥሰት ተባባሪ መሆን ስለማንፈቅድ መስከረም 13 ቀን በተፃፈ ደብዳቤ አማራጭ ይሆናሉ ያልናቸውን፡-
• ኢትዮ ኩባ አደባባይ ፊት ለፊት
• አራት ኪሎ አደባባይን
• ስድስት ኪሎ አደባባይ
• ቴዎድሮስ አደባባይ
• አብነት ሆቴል ፊት ለፊት ያለው አደባባይ
• ሳርቤት አካባቢ ያለው ፑሽኪን አደባባይ
• ብሔር-ብሔረሰቦች አደባባይ
• አዲስ አበባ ስቴድዩም
• በቦሌ ድልድይና በኢምፔሪያል ሆቴል መካከል ከቀለበት መንገድ ግራና ቀኝ ያለው ሜዳ መሆናቸውን በመግለጽ ምላሽ በመጠባበቅ የቅስቀሳ ስራችንን በከፍተኛ ጫና ውስጥ ሆነን እያከናወንን እንገኛለን፡፡
በቅስቀሳ ወቅትም ከማክሰኞ መስከረም 15 ቀን 2006 ዓ.ም ጀምሮ በእቅዳችን መሰረት ከ 33ቱ ፓርቲ አመራሮችና አባላት ጋር በመሆን የመኪና ላይ ቅስቀሳ፣ በራሪ ወረቀ፣ ፖስተር መለጠፍ የጀመርን ቢሆንም የከተማው መስተዳድር ህግ በተላለፈ ሁኔታ ነሐሴ 10 ቀን 2006 ዓ.ም የሰላማዊ ሰልፍ ቅስቀሳ የሚከለክል የውስጥ መመሪያ በማውጣት ፓርቲዎች፣ ምርጫ ቦርድና ሚደዲው ሳያውቅ በድብቅ ለአዲስ አበባ ፖሊስና ክፍለ ከተሞች በማሰራጨት አባሎቻችንና አመራሩ ለቅስቀሳ ሲወጡ እንዲታሰሩ አድርጓል፡፡
በዚህ ህገ-ወጥ መመሪያ የተነሳም ማክሰኞ መስከረም 15 ቀን 2006 ዓ.ም ሦስት መኪናና አጠቃላይ 30 ቀስቃሽ አባላት ከቀኑ 5 ሰዓት ጀምሮ ታስረው ከምሽቱ 1 ሰዓት ተለቅቀዋል፤ ዕሮብ መስከረም 16 ቀን 2006 ዓ.ም ሦስት መኪናና 28 ቀስቃሽ አባላት በተመሳሳይ ታስረው ማታ ተለቅቀዋል፤ ሐሙስ መስከረም 17 ቀን 2006 ዓ.ም ሁለት መኪናና 16 ቀስቃሽ አባላት የታሰሩ ሲሆን የፓርቲያችን ሊቀ መንበር ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ የታሰሩትን ለማስፈታ ወደ ሽሮ ሜዳ ፖሊስ መምሪያ ቢሄዱም የታሰሩ አባላት ካልተለቀቁ አልሄድም በማለት አብረው ታግተው ውለዋል፡፡ መስከረም 18 ቀን 2006 ዓ.ም የፓርቲው መሪ፣ የስራ አስፈፃሚ አባላትና አመራሩ በሁለት መኪና በመሆን አንደኛውን መኪና ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ እየመሩት፣ ሁለተኛውን መኪና የተከበሩ አቶ ግርማ ሰይፉ እየመሩት ቅስቀሳ ቢጀመርም አጠቃላይ 26 አመራሮች በቁጥጥር ስር ውለው እንዳይቀሰቅሱ ተደርጓል፡፡ ፓርቲያችን በተለያዩ መንገዶች ቅስቀሳውን ማድረግ አጠናክሮ በመቀጠል ሁለት መቶ ሺ በራሪ ወረቀቶች ተሰራጭተዋል፤ አስር ሺ ፖስተሮች ተለጥፈዋል፡፡ ሕዝቡም በነቂስ ወጥቶ ሰላማዊ ሰልፉን በመቀላቀል በሰላማዊ መንገድ የተቃውሞ ድምፁን እንዲያሰማ በአክብሮት ሀገራዊ ጥሪ እናቀርባለን፡፡
በዚህም መሰረት መንግስት በወረቀት ብቻ እውቅና ሰጥቶ በተግባር ቅስቀሳ የከለከለ ቢሆንም የተቃውሞ ሰልፋችን በታቀደለት ዕለት ሠልፉ በምንም አይነት ጫና የማይሰረዝ መሆኑን እያረጋገጥን መነሻውን ከፓርቲያችን ፅ/ቤት በማድረግ የሚካሄድ መሆኑን እየገለጽን፤ አንድነት ለሠላማዊ ትግል የሚከፈሉ መስዋትነቶችንን ከፍሎ የትግላችንን ፍሬ እንደምናረጋግጥ እርግጠኛ ብንሆንም በአሁኑ ወቅት መንግሥት በማከናወን ላይ ያለው ተግባር ከሠላማዊ ትግል ውጭ ያሉ አማራጮችን በቀጥታ እያበረታታና እየደገፈ መሆኑን ማስገንዘብ እንወዳልን፡፡ በመጨረሻም የመንግሥት ተግባር መሠረታዊ የሆነ የዜግነትና የአገራዊ ባለቤትነት ጥያቄን ስለሚያስነሳ፤ አፈናው እንዲቆም በአገርና በሕዝብ ስም እየጠየቅን ይህን ፍርደ ገምድልና ኢ-ፍትሓዊ ውሳኔን ተከትሎ ለሚደርሱ ችግሮች ተጠያቂው መስተዳድሩና መንግሥት መሆኑ እንዲታወቅ አበክረን እንገልፃለን፡፡
=======================================
ዘላለማዊ ክብር ለኢትዮጵያ!!!
የአንድነት ፓርቲና የ33ቱ ፓርቲዎች
መስከረም 18 ቀን 2006
አዲስ አበባ1378168_724896370860160_2046962854_n

0 comments:

Post a Comment