Wednesday 23 November 2016

38 እስረኞች በቂሊንጦ እስር ቤት እሳት በማስነሳት ወንጀል ክስ ተመሰረተባቸው


(ኢሳት) ከሳሽ አቃቢ ህግ 38 ተከሳሾች ከጥር ወር 2008 ዓም ጀምሮ የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) ግንቦት ሰባትና፣ በአልሸባብ የሽብር ቡድን ተልዕኮ ለመፈጸም በእስር ቤቱ በተለያዩ ወንጀሎች በእርማት ላይ ያሉ እስረኞችን በድብቅ በመመልመል አመጽ ለመፍጠር መረጃን ሲለዋወጡ ነበር ሲል በክሱ አመልክቷል።

ይሁንና ተከሳሾቹ ሽብርተኛ ከተባሉት ድርጅቶች ጋር በእስር ቤት እያሉ በምን መልኩ ግንኙነት ሲያደርጉ እንደነበር የሰጠው ዝርዝር መረጃ የሌለ ሲሆን፣ 38 ግለሰቦች 10 ሚሊዮን ብር የሚገመት ንብረት እንዲወድም ማድረጋቸውም በክሱ መካተቱን የመንግስት መገናኛ ብዙሃን ረቡዕ ዘግበዋል።

በነሃሴ ወር በቂሊንጦ እስር ቤት በደረሰው የእሳት ቃጠሎ አደጋ በትንሹ 23 እስረኞችን መሞታቸው ይታወሳል። በእለቱ በእስር ቤቱ ያለ ትጥቅ በጥበቃ ላይ የነበረ አንድ የጸጥታ ባልደርባ የእስር ቤቱ የጸጥታ ሃይሎች የእሳት ቃጠሎውን ተከትሎ የተኩስ ዕርምጃ ሲወስዱ እንደነበር ለአዲስ ስታንዳርድ መጽሄት እማኝነት መሰጠቱ ተዘግቧል። መንግስት በበኩሉ እስረኞቹ ከአደጋው ለማምለጥ በሞከሩ ጊዜ በተፈጠረ መረጋገጥ ህይወታቸው አልፏል ሲል ማስተባበያ መስጠቱ ይታወቃል።

38 እስረኞች ላይ ክሱን የመሰረተው አቃቤ ህግ ተከሳሾቹ አመጽ ማነሳሳት እንዲችሉ በውጭና ሃገር ውስጥ ከሚገኙ አባላትና ማረሚያ ቤት ውስጥ ከሚገኙ ታራሚዎች ገንዘብ ሲያሰባስቡ እንደነበር በክሱ አመልክቷል። ተከሳሾቹ በእስር ቤት ውስጥ እያሉ በምን ሁኔታ ገንዘብን ሲቀበሉ እንደነበር የታወቀ ነበር የሌለ ሲሆን፣ ግለሰቦቹ የአመጽን ድርጊት ይመራሉ ተብለው ለመለመሏቸው ታራሚዎች ክፍያ ሲፈጽሙ ነበር ተብለዋል።

በቂሊንጦ እስር ቤት የደረሰውን የእሳት አደጋ ተከትሎ ከኢሳት ጋር ቃለ-ምልልስን ያደረጉ የሟች እስረኛ ቤተሰቦች የቤተሰብ አባሎቻቸው የሞቱበት ሁኔታ እንዳይታወቅ አስከሬን በልዩ መንገድ ታሽጎ እንደተሰጣቸው አስታውቀዋል።
በእስር ቤቱ አካባቢ ያሉ ነዋሪዎች በበኩላቸው ከቃጠሎው በፊት በእስር ቤቱ የተኩስ ድምፅ ይሰማ እንደነበርና እስረኞቹ በዚሁ የተኩስ አደጋ መሞታቸውን ለመገናኛ ብዙሃን ሲገልፅ እንደነበር የሚታወስ ነው።


0 comments:

Post a Comment