Monday, 28 November 2016

አቶ ዮናታን ተስፋዬ የቀረበበትን ክስ ለመከላከል ታዋቂና በከፍተኛ ኃላፊነት ላይ ያሉ ሰዎች በምስክርነት ተጠርተዋል

*አቶ በቀለ ገርባና ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ ከማ/ቤት ቀርበዋል፤ ጦማሪና ጋዜጠኛ በፍቃዱ ኃይሉን ያሰረው አካል ሳያቀርበው ቀርቷል፡፡

የሰማያዊ ፓርቲ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ የነበረውና የሰብዓዊ መብት ተሟጋቹ አቶ ዮናታን ተስፋዬ በፌደራል አቃቤ ህግ የቀረበበትን ሽብር ክስ እንዲከላከል የተወሰነበትን ክስ ለመከላከል የኦፌኮ ፕሬዚደንትና ም/ፕሬዚደንትን ጨምሮ ከፍተኛ ኃላፊነት ያላቸውና ታዋቂ ሰዎች በምስክርነት ተጠርተዋል፡፡


አቶ ዮናታን ተስፋዬ ዛሬ ህዳር 19/2009 ዓ.ም መከላከያ ምስክሮችን ለማስደመጥ በተያዘለት ቀጠሮ መሰረት የፌደራሉ ከፍተኛ ፍ/ቤት ልደታ ምድብ 4ኛ ወንጀል ችሎት ቀርቧል፡፡ አቶ ዮናታን በጠበቃው አማካኝነት የምስክሮችን ዝርዝር ለፍ/ቤት ያስረዳ ሲሆን፣ ከምስክሮቹ መካከል አብዛኞቹ ሲገኙ ሦስቱ ብቻ ሳይቀርቡ ቀርተዋል፡፡

አቶ ዮናታን ተስፋዬ ተከላከል የተባልሁበትን ክስ በመከላከያ ምስክርነት ቀርበው ያስረዱልኛል ያላቸውን 10 ምስክሮች ዘርዝሮ አቅርቧል፡፡ እነዚህም ወላጅ አባቱ ቀሲስ ተስፋዬ ረጋሳ፣ ታናሽ እህቱ ገዳምነሽ ተስፋዬ፣ የቅርብ ጓደኛው ኤፍሬም ታያቸው፣ የኦፌኮ ፕሬዚዳንት ዶ/ር መረራ ጉዲና፣ አቶ በቀለ ገርባ፣ የህግ ምሁሩ ዶ/ር ያዕቆብ ኃ/ማርያም፣ በእስር ላይ የሚገኘው ታዋቂው ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ፣ የፍልስፍና መምህሩ ዶ/ር ዳኛቸው አሰፋ፣ ጋዜጠኛና ጦማሪ በፍቃዱ ኃይሉ እና አቶ ሙላቱ ገመቹ ናቸው፡፡
ከእነዚህ መከላከያ ምስክሮች መካከል ዶ/ር መረራ ጉዲና፣ ዶ/ር ዳኛቸው አሰፋና ጋዜጠኛና ጦማሪ በፍቃዱ ኃይሉ በዛሬው ቀጠሮ አልቀረቡም፡፡ በእስር ላይ የሚገኘው በፍቃዱ ኃይሉን ጨምሮ ዛሬ ያልቀረቡት እንዲቀርቡ፣ የቀረቡትም ተጨማሪ መጥሪያ ሳያስፈልጋቸው በቀጣይ ቀጠሮ እንዲቀርቡ ታዝዟል፡፡

ተከሳሹ በዚህ መሰረት አብዛኞቹ ምስክሮቹ መገኘታቸውን ችሎት ፊት አቅርቦ በማስረዳት፣ ምስክሮቹን አግኝቶ ስለሚመሰክሩበት ጉዳይ ለመነጋገር ጊዜ እንደሚፈልግ በመግለጽ ተለዋጭ ቀጠሮ ጠይቋል፡፡ ከምስክሮች መካከል ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ ‹‹የፍ/ቤት መጥሪያ በእጄ አልደረሰኝም፡፡ ጠዋት ትፈለጋለህ ተብዬ በጽ/ቤት ተጠርቼ ነው የመጣሁት፡፡ ስለምመሰክርበት ጉዳይ አሁን ገና ነው የሰማሁት፡፡ የሙያ ምስክርነት እንድሰጥ ስለተጠራሁ ትንሽ የዝግጅት ጊዜ እንዲኖረኝ በተለዋጭ ቀጠሮ ምስክርነቴን እንድሰጥ ይፈቀድልኝ›› ሲል ከተከሳሹ አቤቱታ ጋር የተጣጣመ ማሳሰቢያ ለችሎቱ አሰምቷል፡፡

አቃቤ ህግ በበኩሉ ዛሬ የቀረቡት ምስክሮች እንዲመሰክሩ እንዲደረግለት ጠይቋል፡፡ ሆኖም ፍ/ቤቱ በተከሳሽ የቀረበውን ማሳሰቢያ በመቀበል ምስከሮቹ ተሟልተውና ስለሚመሰክሩበት ጉዳይ ተረድተው ሲቀርቡ ምስክርነታቸውን ለመስማት በሚል ለታህሳስ 26 እና 27/2009 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ተሰጥቷል፡፡

አቶ ዮናታን ተስፋዬ ከሰው ምስክሮች በተጨማሪ ሦስት የሰነድ ማስረጃዎችን ዘርዝሮ አቅርቧል፡፡

በዛሬው ዕለት ለምስክርነት ከቃሊቲ እስር ቤት የቀረበው የ18 አመት ፍርደኛ ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ ሙሉ ጥቁር ሱፍ ከጥቁር መነጽር ጋር ለብሶ እጆቹ በካቴና ታስረው በከፍተኛ ጥበቃ ፍ/ቤት ሊቀርብ ችሏል፡፡ በቃሊቲም ሆነ በቂሊንጦ የሚገኙ እስረኞች የእስረኛ ዩኒፎርም ለብሰው የቀረቡ ቢሆንም እስክንድር ነጋ ብቻ በተለየ በሱፍ ልብስ መቅረቡን ለመመልከት ተችሏል፡፡ ጋዜጠኛ እስክንድር ከፍ/ቤት ግቢ በመኪና ሊጫኑ ሲወሰዱ በካቴና የታሰሩ እጆቹን ከፍ በማድረግ በፈገግታ ታጅቦ ‹‹አይዞን እንበርታ!›› የሚል ቃል ሰላምታ ላቀረቡለት ሁሉ ተናግሯል፡፡

ምንጭ:- የኢትዮጲያ ሰዕባዊ መብቶች ፕሮጀክት

0 comments:

Post a Comment