Wednesday, 26 October 2016

የቂሊንጦ ተወካይ “አቶ ዮናታን ተስፋዬ የት እንዳለ አላውቅም” አለ

የቀድሞ የሰማያዊ ፓርቲ የህዝብ ግንኙነት ኃለፊ አቶ ዮናታን ተስፋዬ ትላንት ፍርድ ቤት ቀጠሮ የነበረው ቢሆንም ሳይቀረብ ቀርቷል፡፡ አቶ ዮናታን ትላንት ቀርቦ የመከላከያ ምስክሮቹን ማሰማት የነበረበት ቢሆንም፣ ታስሮ የሚገኝበት ቂሊንጦ ወህኒ ቤት ሳያቀርበው መቅረቱ ተነግሯል፡፡ አቶ ዮናታን ለምን ፍርድ ቤት እንዳልቀረበ ጥያቄ የቀረበላቸው የወህኒ ቤቱ ተወካይ፣ ተጠርጣሪው ፍርድ ቤት መቅረቡንም ሆነ አለመቅረቡን አንደማያውቁ ገልጸዋል፡፡ አክለውም ቂሊንጦ ይኑር አይኑርም እንደማያውቁ ለፍርድ ቤቱ ተናግረዋል፡፡

የተከሳሽ ጠበቃ አቶ ሽብሩ በለጠ በበኩላቸው ወህኒ ቤቱ ከደምበኛቸው ጋር እንዳይገናኙ እንዳደረጋቸው ገልጸዋል፡፡ ተከሳሹ ለምን ፍርድ ቤት እንዳልቀረበ ወህኒ ቤቱ የጽሁፍ ማብራሪያ እንዲያመጣ የጠየቀው ፍርድ ቤቱ፣ ለህዳር 19 ቀን 2009 ተለወጭ ቀጠሮ በመስጠት፣ ወህኒ ቤቱ በዕለቱ ተከሳሹን ችሎት እንዲያቀርበው ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡

የኦሮሚያ ተቃውሞ እየተጋጋለ በነበረበት ወቅት ማለትም ያለፈው ዓመት አጋማሽ ላይ በፖሊስ ቁጥጥር ስር የዋለው አቶ ዮናታን፣ ለክሱ በማስረጃነት ከቀረቡበት ነጥቦች በፌስ ቡክ ገጹ የጻፋቸው ፖለቲካዊ ጽሁፎች እንደሆኑ ሲነገር ቆይቷል፡፡ መንግስት ሆን ብሎ ባስነሳው እና ብዙዎችን በጥይት ደብድቦ በገደለበት የቂሊንጦ እሳት አደጋ ወቅት ወደ ሌላ ማቆያ ተወስደው ከነበሩት ተጠርጣሪዎች አንዱ ዮናታን ተስፋዬ ነው፡፡ ንቁ የፖለቲካ ተሳትፎ ከሚያደርጉ ወጣት ፖለቲኮኞች አንዱ የሆነው አቶ ዮናታን ተስፋዬ በዓቃቤ ህግ የሽብር ወንጀል ክስ እንደተመሰረተበት ይታወቃል፡


0 comments:

Post a Comment