" ከዚህ በኋላ የፍትህና የነፃነት ኃይሎች ዋና ተግባር ያላቸውን አቅም ሁሉ አስተባብረውና ነፃነት የራበውንና የጠማውን ሕዝባቸውን ከጎናቸው አሰልፈው፤ ጊዜውና ሁኔታው የሚፈቅደውን ተለዋዋጭና ተለማጭ የትግል ስልት እየተጠቀሙ ይህ አዋጅ በፍጹም ተግባራዊ እንዳይሆንና እንዳይሳካ ማድረግ ነው። ይህን የባርነት አዋጅ ለማስፈጸም በመሪነትና በዋና አስፈጻሚነት የሚንቀሳቀሱት ኃይሎች፤ ይህ የባርነት አዋጅ በኢትዮጵያ ሕዝብ ጫንቃ ላይ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ እንዲተገበርና እንዲሳካ ለማድረግ የሚሞክሩ ወይንም ከዚህ ዘራፊ ሥርዓት ጋር በጥቅም ተሳስረው ከዚህ የባርነት አዋጅ ጋር የሚተባበሩ ማናቸውም ኃይሎች ሁሉ ከአሁን ጀምሮ የሕዝባዊ ትግሉ ቀንደኛ ዒላማዎች መሆናቸውን ግልጽ አድርጎ መንቀሳቀስ ይገባል። በዚህ ሕዝባዊ ትግል ላይ የሚሳተፉ የሕዝብ ወገኖችም ሆነ ይህንን ዘራፊ ሥርዓት የሚያግዙ ኃይሎች በደንብ እንዲረዱት የሚያስፈልገው ይህን አዋጅ አከሸፍነው ማለት የወያኔ ሥርዓት አከተመለት ማለት እንደሆነ ነው። ይህ አዋጅ ተሳካ ማለት ደግሞ የኢትዮጵያ ሕዝብ ላልተወሰነ ጊዜ በባርነት መቀመቅ ውስጥ ሊኖር ተፈረደበት ማለት ነው። ለዚህ ነው አሁን የገባንበት ትግል የመጨረሻው የሞት ሽረት ትግል ነው የምንለው።"
"በዚህ የመጨረሻ የፍልሚያ ወቅት ጥቂቶቻችን ልናልፍ እንችላለን። ለነፃነታችን ስንል ሕይወታችንን ብንሰጥ
ፈጣሪያችን በአምሳሉ ሲፈጥረን የሰጠንን የሰውነት ማንነት እውን ለማድረግ በምናደርገው ትግል ነውና የምናልፈው፤
የፈጣሪያችንን ፈቃድ ለማስፈጸም የገበርነው ሕይወታችን ነውና በደስታ የምንጠጣው ጽዋችን ነው። ይልቅስ ፈጣሪያችን
ለምንግዜውም ይቅር የማይለን ከሌላው እንሰሳ ለይቶ የሰጠንን ይህን በነፃነት የታጀበ የሰው ልጅነት፤ እንደ እንሰሳ
ለሚበላና ለሚጠጣ ቁሳዊ ጥቅም ሸጠን፤ ሰው መሆንን በእንሰሳዊ የባርነት ሕይወት ቀይረን እኛ ባርነትን ተቀብለን
ከራሳችን አልፎ ባርነትን ለልጆቻችን ያስተላለፍን እንደሆነ ነው። የዛሬ ትውልድ ኢትዮጵያውያን የባርነትን ኑሮ ከኛ
እንዳያልፍና ወደ ልጆቻችን እንዳይጋባ ማስቆም ታሪክ የጣለብንና በእርግጠኛነት የምንፈጽመው ተግባራችን እንደሆነ
ከቶውንም አልጠራጠርም።"
0 comments:
Post a Comment