Monday 31 October 2016

ጋዜጠኛ ጌታቸው ሺፈራው ለ3ኛ ጊዜ ለብይን ተቀጥሯል

‹ፌስቡክን ጨምሮ በተለያዩ መገናኛ ዘዴዎች ግንቦት ሰባት ከተባለው አሸባሪ ቡድን አመራሮች ጋር ግንኙነት አድርገሃል› በሚል የሽብር ክስ ተመስርቶበት ጉዳዩ በፍርድ ቤት እየታየ የሚገኘው የነገረ ኢትዮጵያ ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ ጋዜጠኛ ጌታቸው ሺፈራው ለ3ኛ ጊዜ ለብይን ቀጠሮ ተሰጥቶበታል፡፡

ዛሬ ጥቅምት 21/2009 ዓ.ም የፌደራል ከፍተኛ ፍ/ቤት ልደታ ምድብ 4ኛ ወንጀል ችሎት ዳኞች ጉዳዩን በጽ/ቤት የተመለከቱት ሲሆን፣ ዳኞቹ መዝገቡን መርምሮ ብይን ለመስጠት ጊዜ እንደሚያስፈልጋቸው በመግለጽ ለህዳር 28/2009 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥተዋል፡፡

በሌሎች መዝገቦች ከዛሬ ቀደም ቀጠሮ የነበራቸውን ተከሳሾች ሳያቀርብ የቆየው የቂሊንጦ ማ/ቤት ዛሬ ጋዜጠኛ ጌታቸውን ጨምሮ ሌሎች በዕለቱ ቀጠሮ ያላቸውን ተከሳሾች ፍ/ቤት አቅርቧል፡፡

ተከሳሹ ጌታቸው ሺፈራው ጉዳዩ ሲታይ የቆየው 14ኛ ወንጀል ችሎት እንደነበር የሚታወስ ሲሆን፣ አሁን ላይ ጉዳዩን የሚያየው ችሎት 4ኛ ወንጀል ችሎት እንደሆነ ለማወቅ ተችሏል፡፡ ይህም ቀደም ሲል በነበረው ችሎት በአንድ ዳኛ ይታይ የነበረው የክስ ጉዳዩ በአሁኑ ችሎት በሦስት ዳኞች የሚታይ ይሆናል ማለት ነው፡፡

ጋዜጠኛ ጌታቸው ሺፈራው የቀረበበትን ክስ መከላከል ይገባዋል ወይስ መከላከል ሳያስፈልገው በነጻ ይሰናበት የሚለውን ብይን ለመስማት ፍ/ቤት ቀጠሮ ሲሰጥ ይህ ለሦስተኛ ጊዜ ነው፡፡ ተከሳሹ ላይ አቃቤ ህግ ከሰነድ ማስረጃዎች ሌላ የሰው ምስክር አላቀረበበትም፡፡

ጌታቸው ታህሳስ 15/2008 ዓ.ም ለእስር ከተዳረገበት ዕለት ጀምሮ እስካሁን ጉዳዩን በእስር ቤት ሆኖ እየተከታተለ ይገኛል፡፡

0 comments:

Post a Comment