በዚህ መዝገብ ይግባኝ የተጠየቀባቸውና ሰብሳቢ ዳኛው፣ ዳኛ ዳኜ መላኩ ከችሎት እንዲነሱ የጠየቁት ተከሳሾች አቶ ሀብታሙ አያሌው፣ አቶ የሺዋስ አሰፋ፣ አቶ አብርሃ ደስታ፣ አቶ ዳንኤል ሺበሽ እና አቶ አብርሃም ሰለሞን ናቸው፡፡
የይግባኝ መልስ ሰጭዎቹ ሰብሳቢ ዳኛው ከችሎት እንዲነሱላቸው ለመጠየቃቸው ምክንያታቸውን ዘርዝረው በጽሁፍ ያቀረቡ ሲሆን በዋናነት ዳኛው ‹‹…ችሎቱን እየመሩበት ካለው አግባብ አንጻርም ሆነ በህግ ከሚጠበቅባቸው ገለልተኝነት አንጻር እርሳቸው እንደ አንድ ዳኛም ሆነ እንደ ሰብሳቢ በሚሳተፉበት ችሎት ትክክለኛ ፍትህ እናገኛለን ብለን ስለማናምን›› የሚል ነው፡፡
እነ ሀብታሙ አያሌው ነሀሴ 15/2007 ዓ.ም የፌደራሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ተረኛ ችሎት በጻፈው እግድ ምክንያት እስካሁን በእስር ላይ ይገኛሉ፡፡
በሌላ በኩል ቃሊቲ ማረሚያ ቤት በእስር ላይ የሚገኘውና በዚሁ መዝገብ የተካተተው የቀድሞው የአንድነት ፓርቲ ምክትል የድርጅት ጉዳይ ኃላፊ አቶ ዳንኤል ሺበሽ በእስር በሚገኝበት ቃሊቲ ማረሚያ ቤት አስተዳደር በደል እየተፈጸመበት እንደሆነ ለችሎቱ ገልጾዋል፡፡ አቶ ዳንኤል ለፍርድ ቤት ክርክር ያዘጋጀው ወረቀት ተቀምቶ እንደተቀዳደደበትና በአስተዳደሩ ከፍተኛ ዛቻም እየተፈጸመበት መሆኑን ለችሎቱ ተናግሯል፡፡ ‹‹እዚህ ቤት አስክሬንህ ነው የሚወጣው›› እያሉ ይዝቱብኛል ያለው አቶ ዳንኤል፣ ‹‹ከሌላው እስረኛ እኩል የማልታየው ለምንድነው? እኔስ ዜጋ አይደለሁምን?›› ሲል ጠይቋል፡፡
ፍርድ ቤቱ መልስ ሰጭዎቹ ባቀረቡት የሰብሳቢው ዳኛ ይነሳልን አቤቱታ ላይ ብይን ለመስጠት ለታህሳስ 15/2008 ዓ.ም ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡
0 comments:
Post a Comment