ምርጫ ቦርድ በሰማያዊ ፓርቲ ምልክትና ስም የተመዘገቡትን ዕጩ ተወዳዳሪዎች እንዲታገዱ በየክልሉ ለሚገኙ
የምርጫ ቦርድ ቅርንጫፍ በላከው ደብዳቤ ገለጸ፡፡ ምርጫ ቦርድ ለደቡብ ክልል የምርጫ ጣቢያ በላከው ደብዳቤ
‹‹ሰማያዊ ፓርቲ ትብብር የሚባል መስርቻለሁ፣ እያስተባበርኩ ነው በማለት እንዲሁም ሌሎች የህግ ጥሰቶችን
በመፈጸሙ›› በሚል ማስጠንቀቂያ እንደተሰጠው በመግለጽ በፓርቲው ምልክት ሊወዳደሩ የተመዘገቡትን አባላት ህገ ወጥ ናቸው ብሏል፡፡
ምርጫ ቦርድ በደብዳቤው ‹‹ሰማያዊ ፓርቲ የራሱ አባል ያልሆኑ ፓርቲውን የማይወክሉ ግለሰቦችን ዕጩ አድርጎ
በፓርቲው ምልክት በከፍተኛ አመራር ፊርማና ማህተም አረጋግጦ ለምርጫ ክልል ጽ/ቤቶች አሳውቆ ከሆነ የምርጫ ሂደት
የሚያሰናክል የህግ ጥሰት በመሆኑ….›› በሚል እንዳይመዘገቡ ትዕዛዝ አስተላልፏል፡፡ የሌሎች ፓርቲ አባላት በሰማያዊ
ተጠቃልለው ምርጫውን በሰማያዊ ምልክት መወዳራቸውም የሚያስጠይቅ ነው ሲል ገልጾአል፡፡
በተመሳሳይ በደቡብ ጎንደር ዞን ሁሉም ወረዳዎች ከሌሎች ፓርቲዎች ወደ ሰማያዊ በመጠቃለል በሰማያዊ ምልክት
ለመወዳደር የተመዘገቡ ዕጩ ተወዳዳሪዎች ከዕጩነት እንዲሰረዙ ምርጫ ቦርድ ለአማራ ክልል ምርጫ ቦርድ ቅርንጫፍ
ደብዳቤ መጻፉን ለማወቅ ተችሏል፡፡
ይህ ምርጫ ቦርድ የሰማያዊ ፓርቲ አባላትን ከዕጩነት ለመሰረዝ የሚያስተላልፈው ትዕዛዝ ህገወጥና የፖለቲካ ውሳኔ
ነው ያሉት የፓርቲው ም/ሊቀመንበርና የምርጫ ጉዳይ ኃላፊ አቶ ስለሽ ፈይሳ ‹‹ችግር ካለ በየምርጫ ጣቢያው ይፈታል
እንጅ ምርጫ ቦርድ ይህን መዝግብ አትመዝግብ ብሎ ለየምርጫ ጣቢያው ትዕዛዝ ሊሰጥ አይችልም፡፡›› ብለዋል፡፡ ምርጫ
ቦርድ ለየክልል ቅርንጫፎቹ ደብዳቤውን የጻፈው የምዝገባ ጊዜው ካለቀ በኋላ ሲሆን ይህም የሆነው ፓርቲው በአካባቢው
ተለዋጭ ዕጩ እንዳይኖረው ታስቦበት ነው ሲሉ ኃላፊው ቅሬታቸውን ገልጸዋል፡፡
በተመሳሳይ የፓርቲው የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ዮናታን ተስፋዬ የምርጫ ቦርድ ውሳኔ የትኛውም የተቃዋሚ ፓርቲ
ጠንክሮ እንዳይወጣ የታለመ በተለይ ሰማያዊ ፓርቲ የሌሎች ፓርቲ አባላትን በማሰባሰብ የህዝብን ስልጣን ለማረጋገጥ
የሚያደርገውን ጠንካራ ትግል ለማደናቀፍ ነው ብሏል፡፡ የህዝብ ግንኙነቱ ኃላፊው አክሎም ‹‹የሌሎች ፓርቲዎች ወደ
ሰማያዊ ፓርቲ መቀላቀላቸውን ተከትሎ ስርዓቱ ከፍተኛ ስጋት ተፈጥሮበታል፡፡ ይህ የምርጫ ቦርድ ተግባርም ህጋዊ
ሳይሆን ከስርዓቱ ፍርሃት የመነጨ የፖለቲካ ውሳኔ ነው›› ብለዋል፡፡ ምርጫ ቦርድና ኢህአዴግ በፓርቲው ላይ እያደረጉ
የሚገኘውን ህገ ወጥ ተግባር ሰማያዊ ፓርቲ እንደማይቀበለውና ትግሉን እናዳክማለን ብለው የሚወስዱት ውሳኔ ይበልጡኑ
ትግሉን ያጠናክረዋል ብሏል፡፡
በሌላ በኩል በወላይታ ዞን ቦሎሶሶሬ በሚባል ምርጫ ጣቢያ ሰማያዊ ፓርቲን ወክለው ለተወካዮች ምክር በዕጩነት
የቀረቡት አቶ ከበደ ካምፔሶ በዕጩነት መቅረባቸውን ተከትሎ የንግድ ቤታቸው መታሸጉ ታውቋል፡፡ ‹‹ዕጩ እንዳልሆን
በሰው ለማግባባትና በማስፈራራት ሊያስቆሙኝ ሳይችሉ ሲቀሩ የንግድ ተቋሜን ዘግተዋል፡፡ ጥያቄያቸው ከፓርቲው
እንድወጣና ዕጩነቴን እንድተውነው፡፡›› ሲሉም አቶ ከበደ ለነገረ ኢትዮጵያ ገልጸዋል፡፡
0 comments:
Post a Comment