Tuesday, 10 February 2015

የሰማያዊ አባላት በእጩነት እንዳይመዘገቡ ምርጫ ቦርድ እንቅፋት እየፈጠረ ነው


የምርጫ ቦርድ አባላት የሰማያዊ ፓርቲ አባላት ለእጩነት እንዳይመገቡ እንቅፋት እየፈጠሩ መሆኑን ፓርቲውን ወክለው በእጩነት ለመመዝገብ የቀረቡት የፓርቲው አባላት  ገልጸዋል፡፡ የቀድሞ አንድነት የወጣቶች ጉዳይ ኃላፊ የነበረውና በቅርቡ ሰማያዊ ፓርቲን የተቀላቀለው አቶ ስንታየሁ ቸኮል የትውልድ ቦታው በሆነው ምስራቅ ጎጃም ዞን ደብረ ኤልያስ በእጩነት እንዳይመዘገብ የምርጫ ቦርድ ተወካዮች እንቅፋት እንደፈጠሩበት ለነገረ ኢትዮጵያ ገልጾአል፡፡

በእጩነት ለመቅረብ በአካባቢው ለሁለት አመት መኖር ወይንም ተወላጅ መሆን የሚጠበቅ ሲሆን አቶ ስንታየሁ በቦታው ተወላጅ በመሆኑ መመዝገብ የሚችል ቢሆንም ‹‹ምስክር አምጣ›› መባሉን ገልጾል፡፡ ‹‹ምንም እንኳ ተወላጅ በመሆኑ መመዝገብ እችል የነበር ቢሆንም ምስክር ስወስድም ምስክሮቹን ‹ችግር ከተፈጠረ እናንተ ናችሁ ተጠያቂ የምትሆኑት› እያሉ ምስክሮቹን እያሸሹ› እንዳልመዘገብ እንቅፋት ፈጥረውብኛል›› ሲል ለነገረ ኢትዮጵያ ገልጾአል፡፡

ከዚህም በተጨማሪ በሞጣ፣ በፍኖተ ሰላም፣ በባሌ የሚገኙ የሰማያዊ ፓርቲ አባላት በተቀመጠው ጊዜ እንዳይመዘገቡ እንቅፋት እየተፈጠረባቸው ነው ተብሏል፡፡ አባላቱ ‹‹መረጃ አቅርቡ፣ ምስክር አቅርቡ›› ተብለው መረጃና ምስክር ይዘው ወደ ምዝገባ ጣቢያዎች ሲሄዱ ቢሮዎች ዝግ እንደሚሆኑና ‹‹አሁን ጥቆማ ነው፡፡ ምዝገባ አይደለም፡፡›› እያሉ እንደሚመልሷቸው ለነገረ ኢትዮጵያ ገልጸዋል፡፡

በሌላ በኩል የጋራ ምክር ቤት አባል የሆኑ ፓርቲዎችን እጩዎች በስልክም ሳይቀር እየጠሩ እንደሚመዘግቡ፣ የሰማያዊ ፓርቲ እጩዎች ምዝገባ ጣቢያ ድረስ ሄደው ለመመዝገብ ሲያመለክቱ እንቅፋት ሲፈጥሩባቸው የብአዴን እጩዎች በአንድ ሰው ተወካይነት እንደሚመዘግቡ የሰማያዊ ፓርቲ የምስራቅ ጎጃም ዞን የሰማያዊ ፓርቲ ፀኃፊ አቶ ሳሙኤል አወቀ ለነገረ ኢትዮጵያ ገልጸዋል፡፡

0 comments:

Post a Comment