“በማሪያም መንገድ ከተከለከለ ፣በገብርኤል መንገድ የሚመጣ ይኖራል”- አቶ አስራት አብርሃም
አቶ አስራት አብርሃም በአቶ በላይ ፍቃዱ ይመራ በነበረው አንድነት ፓርቲ ተ/ህዝብ ግንኙነት ኃላፊ ነበር::ሰሞኑን በአንድነት ፓርቲ ላይ በተፈጸመው ድርጊት ዙሪያ አዲስ አበባ ከምትታተመው ፍቱን መጽሔት ጋር ቃለ ምልልስ አድርጓል፡፡ ሙሉ ቃለ ምልልሱን ያንበቡ
ፍቱን፡- በሰላማዊ ትግል ለውጥ ለማምጣት የሚታገልን እንደ አንድነት ያለ ፓርቲ በዚህ ደረጃ ለማጥፋት መወሰን እጅግ ግራ አጋቢ ነው የሚሉ አስተያየቶች አሉ?
አቶ አስራት፡- አዲስ ነገር ጋዜጣን ለማጥፋት የወሰነ መንግስት ሌሎች ሚዲያዎችን ለመታገስ እንደሚከብደውግልጽ ነው፣ ምክንያቱም አዲስ ነገር በሃሳብ የሚሞግት ሚዲያ ነበር::አንድነትም ከሌሎች በተሻለ ሁኔታ ከጥላቻ ፖለቲካ እየወጣ ነበር፣ ለኢአዴግ አመራሮችም ቢሆን ያን ያህል የከፋ አመለካከት አልነበረውም::እንዲያውም እነሱ ሣይጠይቁ የሚያልፉበትን መንገድ ለማመቻቸት ፍላጐት ነበረው::የዴሞክራሲውን ግንባታ ከገዢው ፓርቲ ጋር በመሆን አብሮ ለመስራት፣ የዴሞክራሲውን ሥርዓት ለማስፋት ፣ ሰጥቶ ለመቀበል የተዘጋጀ አመራርና ፓርቲ ነበር::ስለዚህ አንድነትን መታገስ ያልቻለ መስርዓት የትኛውንም ፓርቲ ይታገሣል ብሎ ማሰብ አይቻልም::ምክንያቱም ቲ.ፒ.ኤል.ኤፍ ከተመሰረተ ጊዜ ጀምሮ የማፍረስ እና የማጥፋት ታሪክ ነው ያለው::ሁሌ የማጥፋት ስትራቴጂ አዋጭ አይደለም::ለአገር የሚያስብ ፓርቲ እና መንግስት ቢሆን ኖሮ 24 ዓመት በስልጣን ተቀምጦዋል ከዚህ በኋላ ሰላማዊ ሽግግር ስለሚመጣበት ነገር ነበር ማሰብ የሚገባቸው::ኃላፊነት የሚሰማው ፓርቲ እንዲፈጠር የበኩላቸውን አስተዋጽኦ የማድረጉን ነገር ነበር ማሰብ የነበረባቸው እንጂ እንደ አንድነት ከብሔርም የተሻገረ በጣም አስተማማኝ ቅርጽና መዋቅር ያለው፣ ሃገር ሊመሩ የሚችሉ አመራር ያሉት ፓርቲ ለማፍረስ እንዲህ አይነት አሳፋሪ ሥራ መስራት አልነበረበትም::ይሄ ሥርዓቱ ውስጥ ያሉ ሰዎች ነገ ስለሚሆነው ነገር ምንም ደንታ እንደሌላቸው የሚያሳይ ነው::ነገ ይሄ አገር እርስ በእርስ ቢጨፋጨፍ አገሩ ቢፈርስ ግድ የላቸውም ማለት ነው::እነሱ በስልጣን ላይ እስካሉ ድረስ ብቻ ነው የሚያስቡት እንጂ ከዚያ የዘለለ የሃገር ራዕይ እንደሌላቸው ያሳየ አሳዛኝ ክስተት ነው::
ፍቱን፡- ኢ/ር ግዛቸው በቀደዱት ተገብቶ ነው አንድነት የፈረሰው የሚሉ አስተያየት ሰጭዎች አሉ?
አቶ አስራት፡- ለኢአዴግ ትልቁን ብትር አቀባይ የምላቸው ኢ/ር ግዛቸው ናቸው::ምክንያቱም ስርዓቱ በአንድነት ነባራዊ ሁኔታ ላይ በጥራሽ ሌለ ከፍተኛ ስጋት እንዲያድርበት ያደረጉት ኢ/ር ግዛቸው ናቸው:: አንድነት በውጭ ነው የሚመራው፣ በውጭ ባለው ኃይል የሚገዛ አመራር መጥቷል::የውጭውን ጉዳይ የሚያስፈጽም አመራር መጥቷል የሚለው ነገር ስርዓቱ ከፓርቲው ሊቀመንበር ከነበረ ሰው ሲሰማ ለማፍረሱ ትልቅ ሰበብ ሰጥተውታል::ሲጀመር ስርዓቱ በአንድነት ላይ ጥርጣሬ ነበረው፣ የፓርቲው መሪ ራሳቸው ይሄንን ሲናገሩ ደግሞ ለማፍረሽ ከዚህ በላይ ማረጋገጫ አይፈልግም::ሰውዬው፣ስርዓቱ ይሄንን ፓርቲ እንደምንም ብዬ ማጥፋት አለብኝ የሚለውን አቋም እንዲወስድ አድርገውታል ብዬ ነው የማስበው::ሁለተኛ ደግሞ ያደረግናቸው ጉባዔዎች ነበሩ፣ እነዚህ ጉባዔዎች ስርዓቱን የበለጠ እንዲደነግጥ ምክንያት ሆኗል ብዬ ነው የማስበው::የመጀመሪያው ጉባዔ የፓርቲ ጉባዔ አይመስልም ነበር::በመንግስት ደረጃ ያለ ፓርቲ የሚያደርገው ደማቅ እና በሁሉም መልኩ በጣም የሰለጠነ ጉባዔ ነበር::ያ ጉባዔ ውሳኔውን ማስቀየር ባንችል የማፍረስ ሂደቱን አፋጥኖታል ብዬ አስባለሁ::ጥር 3 ቀን 2ዐዐ7 ዓ.ም የተደረገው ሁለተኛው አስቸኳይ ጉባዔም ደግሞ ጥርጣሬውን ነፍስ ዘርቶበት በህግ ሽፋን ማስወሰኑን እንኳን ትቶ በኃይል እንዲያፈርሰው ምክንያት ሆኗል ብዬም አስባለሁ::
በአጠቃላይ ኢ/ር ግዛቸው አንድነት እንዲፈርስ በሩን የከፈቱ ናቸው::ይህም ስራቸው በታሪክም የሚያስጠይቃቸው ነው የሚመስለኝ::
ፍቱን፡-በኢ/ሩ ላይ ያላችሁ አረዳድ ይህ ከሆነ፣ ለሁለት ጊዜ የመሩትን ፓርቲ ለማስፈረስ ይህንን ያህል መንገድ የሄዱት ለምንድን ነው?
አቶ አስራት፡- እንደሚታወቀው በባህላችን የእኛ ሰው ቂመኛ ነው:: ልክ እግዚአብሔር አንድ ኢትዮጵያዊ አግኝቶ ፣‹‹የምትፈልገውን አፈጽምልሃለሁነገር ግን ለአንተ የማደርግልህን ለጓደኛህ በእጥፍ አደርግለታለሁ ሲለው እንደዚያማ ከሆነ አንድ ዓይኔን አጥፋልነኝ::አለው እንደተባለው፣ ለእሱ የሚሰጠው መልካም ስጦታ ከሚያስደስተው ይልቅ ጐረቤቱ የሚያገኘውን የበዛ ስጦታ ነበር ያስጨነቀው:: ራሴንም ጐድቼ ሌላውን የበለጠ መጉዳት የሚለው ሳይኮሎጂ በእኛ ማህበረሰብ አለ ብዬ ነው የማስበው::በፖለቲካው አካባቢም ያለው ይኸው ነው::ከሆነ ግሩፕ ጋር ትጣላና እነሱን ለመጉዳት በማሰብ ረጅም ርቀት ሂዶ ጉዳት ማድረስ ፣በተለይ ከ6ዐዎቹ ጀምሮ ያለው መጠፋፋት እና በቂም በቀል የተሞላ ማንነት ነው:: እነ ኢ/ር ግዛቸውም የዚያ ትውልድ ሰዎች ናቸው::ስለዚህ በዚያ የመጠፋፋትና የመበቃቀል ባህል ነው ራሳቸውን አዋርደው ለመገኘት ያስወሰናቸው፡፡ የሚገርመው እኛ ያደረጉትን ነገር ይቅር ብለን ዋናው ነገር እንኳን ፓርቲውን ለቀቁ ብለን የእሳቸውን ስም ከፍ አድርገን ስልጣናቸውን በፈቃዳቸው መልቀቃቸውን መልካም ነገር ነው ብለን ክብር ለመስጠት በጣም ነበር የሞከርነው::እሳቸው ግን የታያቸው ስልጣኑን መልቀቃቸው ነው::ስልጣን እንዲለቁ የተደረገው ደግሞ ፓርቲው ላይ ተኝተውበት ስለነበር ነው::ዩኒቨርሲቲ ያስተምራሉ፣ ደሞዝ ከዚያ ይቀበላሉ፣ እዚህ የፓርቲው ሊቀመንበር ነኝ ብለው ከፓርቲው ተጨማሪ ደሞዝ ይቀበላሉ፣ ከዚያ የሚሰሩት ነገር የለም::ዝም ብለው የሰዎችን ወሬና ሃሜት ሲቀበሉ ነበር ነው የሚባለው::ፓርቲው እየተዳከመ ነበር:: ጽ/ቤቶቹ እየተዘጉ ነበሩ::ባህርዳር፣ መቀሌ፣ አዳማ፣ አዋሣ ዋና ዋና ከተሞች ሳይቀር ተዘግተው እንቅስቃሴ ቆሞ ነበር::የተለይ አብሯቸው ይሰራ የነበረው ስራ አስፈፃሚው ከለቀቀ በኋላ ከፍተኛ መዳከም ነበር የነበረው::አመራር እየሰጡ ነበር ብዬ አላስብም::
ለዚህ ነው ስልጣን እንዲለቁ የተፈለው እንጂ ሌላ አልነበረም::አንድነት መሰረታዊ የስትራቴጂ ስህተት ሰርቷል የምለው ዶ/ር ነጋሶ ሲወርዱ ወጣቶቹ ስልጣን ሊቀበሉ ሲገባ ኢ/ር ግዛቸውን ድጋሚ መልሶ ማውጣቱ ነው::ያንን ያደረጉ ሰዎች አሁን ይፀፅታቸዋል ብዬ አስባለሁ::ያ ውሳኔያቸው ፓርቲውን አሁን ያለበት ደረጃ እንዲደርስ ያደረገ ስህተት ነበር እላለሁ፡፡አንደኛ ሰውዬው በ2ዐዐ2 ምርጫ ላይ ከባድ ስህተት የፈፀሙ ናቸው::ጠዋት ምርጫው ተጭበርብሯል ብለው፣ ሰውን እንዳይመርጥ ካደረጉ በኋላ እንደገና ከሰዓት ቀርበው ጠዋት የተናገርኩት ስህተት ነው ብለው የተናገሩ ሰው ናቸው:: የሰውዬው ፖለቲካ ማብቃት የነበረበት በዚያው ቀን ነበር::ይሄንን እያወቁ ተመልሰው ወደ ስልጣን እንዲመጡ ያደረጉ ሰዎች ስለፖለቲካ ማወቃቸውንም እጠራጠራለሁ::ኢ/ሩ ፓርቲውን ለስርዓቱ ሸጠው ከተሾሙት እነ አቶ ትግስቱ የማይተናነስ ኪሳራ እና ክህደት ነው በፓርቲው ላይ አድርሰዋል ብዬ የማስበው::
ፍቱን፡- ስለ አቶ ትግስቱ ምን አስተያየት አለህ?
አቶ አስራት፡- እነዚህ ሰዎች የተባረረም ያልተባረረም ተደምረው 5 ወይም 7 ሰዎች ቢሆኑ ነው::ሌላው ከየት እንደመጣ አይታወቅም::ከወጣት ሊግ ይሁን ወይም ከጥቃቅንና አነስተኛ ከየት እንደመጡ የምናውቀው ነገር የለም:: ከዚህ በኋላም ፓርቲውን ያስቀጥሉታል ብዬም አላስብም::አመራርርም ይሰጣሉ ብዬ አላስብም::ሊሆን የሚችለው ያሉትን የማተሚያ ማሽኖችና ምናምኖች ሸጠው ወደ መጡበት ይሄዳሉ እንጂ ፓርቲ አቋቁመው ፓርቲውን በአግባቡ ያስቀጥላሉ ብዬ የማስባቸው ሰዎች አይደሉም፡፡እነዚህ ሰዎች አይደለም አንድነትን አንድ ትንሽ እድርም በአግባቡ መርተው ያሳካሉ ብዬ አላስብም::አቶ ትግስቱን የተወሰነ ጊዜ ነው የማውቀው፡፡አቶ በላይ ወደ አመራር ሲመጣ ልወዳደር ብሎ ቀርቦ የራሱን ድምጽ ብቻ ያገኘ ሰው ነው::አንድ ሰው እንኳን እንዲመራ ያልተቀበለው ሰው ነው::ይህ ሲሆን በወቅቱ እኔ በጣም shock ሆኜ ስለነበር ማታ ደውዬለት አይዞህ ፖለቲካ ውስጥ ያጋጥማል ብዬ እንዳይሰማው ለምጽናናት ሞከርኩኝ::ራሴን በእሱ ቦታ አስቀምጬ ሳየው ለምንድን ነው ፖለቲካ ውስጥ የምቀጥለው ብዬ ራሴን እጠይቃለሁ::ምክንያቱም ፖለቲካ ቢያንስ ሃሳብህን የሚቀበልህ አንድ ሰው መኖር አለበት::ተራ አባል ከሆንክ ችግር የለም::ግን አመራር እሆናለሁ ብሎ ለሚያስብ ሰው ቢያንስ አንድ ሁለት ሰው ድምጽ ሊሰጠው ይገባል::በወቅቱ እንዴት አይነት ሰው ቢሆን ነው አንድ ሰው እንኳን ሊመርጠው ያልቻለው?፣በላይ እና ኢ/ር ግዛቸው ሊወዳደሩ ሲሉም 3ተኛ ተወዳዳሪ ነበር::ለኢ/ር እና በላይ የሚቀሰቅሱ በጣም ብዙ ሰዎች ነበሩ::ለትግስቱ ግን አንድም አልነበረም::አሁን ከተመረጠም በኋላ ትዕግስቱ መሪያችን ብሎ አንድም የሚቀሰቅስ ሰው አይታይም::በጣም የሚገርመኝ ሰው ነው::ኢህአዴግ ይሄንን አይነት ሰው ከየት ፈልጐ እንደሚያገኝ እንዴት አድርጐ እንደሚመለምላቸው በጣም ነው የሚገርመኝ::እንደ ግለሰብ ያሳዝንሃል::እንደዚህ ዓይነት የይሁዳን ታሪክ ለመሸከም ፈቃደኛ የሚሆን ሰው የሆነ የተጐዳበት ነገር ቢኖር ነው ብለህ ነው እንጂ የምታስበው ሌላ የምትለው ነገር የለም::በጣም ያሳዝናል::ትልቅ ሰው ነው፣ የተማረ ነው ይሉታል፣ በዚህ ዕድሜው እንዲህ መሆኑ በጣም ይገርመኛል::የእነ አንዱዓለም፣ የእነ ሃብታሙ ዶ/ር ኃይሉ አርአያ የብዙዎቹኢትዮጵያዊያን ፓርቲ በዚህ ሁኔታ ለመረከብ ፈቃደኛ መሆኑ በጣም የሚዘገንን ነው::ህሊናና ሞራል ላለው ሰው ለታሪኩ ለሚጨነቅ ሰው በጣም ከባድ ነው፡፡
ፍቱን፡- በምን እናጠቃል?
አቶ አስራት፡- እኔ በውሃ አጠምቃችኋለሁ::ከእኔ ከፍ ያለ ይመጣል::በእሣት ያጠምቃችኋል ያለው መጥምቁ ዮሐንስ ይመስለኛል፡፡
እኛ ሃሣብ ይዘን በሰላማዊ እና በሕጋዊ መንገድ ለመታገል ጥረት አድርገናል::ይህ በስርዓቱ ስላልተወደደ በኃይል እንድንፈርስና እንድንዘጋ ሆነናል::ይህ መንገድ ሲዘጋ ከዚያ በኋላ የሚሆነው ምንድን ነው? ከዚያ በኂላ በሰይፍ የሚመጡ ይኖራሉ::አቤ ቶክቻው ባለፈው ያለው ነገር ነበር::የማርያም መንገድ ስጡን ተብለው እንቢ ካሉ በገብርኤል መንገድ የሚመጡ ይከተላሉ ያለው በጣም ትክክለኛ እና ተገቢ አባባል ነው፡፡ እኛ በማርያም መንገድ ከተከለከልን በገብርኤል መንገድ የሚመጣ ይኖራል::በዚህ አገር ሰላም እንዲሆን እንፈልጋለን::ሰላም እንዲመጣ እንፈልጋለን::ሁሉንም ነገር በሰላም የማሸጋገር ባህል በእኛ እድሜ ቢጀመር ደስ ይለኛል፡፡ ይህቺ አገር 3 ሺህ ዘመን አላት ይባላል አንደም ታሪክ ላይ ግን ሰላማዊ የሆነ ተቋም ላይ የተመሠረተ አንዴም የስልጣን ሽግግር አድርጋለች ብሎ አላሰበም::ሁሉም በሃይልና በነውጥ የመጀመሪያውን ያፈርሱና ከዜሮ የመጀመር እንጂ ባለበት እየገነባ፣ የመጀመሪያውን ስህተት እያረመ የመጣ የመንግሥት ሲስተም የለም::ይህን አይነት የስርዓት አልበኝነት መንገድ አንድ ቦታ ላይ ማቆም ነበረብን::የእኔ እምነት እንደዚያ ነበር::ስልጣንን በካርድ የምንቀይርበት ዘመን መምጣት ነበረበት:: በዚህ አገር ዴሞክራሲን ለማስፈን ብዙ ህይወት ጠፍቷል::ብዙ ወጣቶች አልቀዋል::ያ ማብቃት ነበረበት፣ አላበቃም::
0 comments:
Post a Comment