Wednesday, 16 September 2015

ድንበርን አቋርጠው ሽብርተኛ ድርጅትን ሊቀላቀሉ ሲሄዱ ተይዘዋል በሚል የተከሰሱ ለህዳር 21 ተቀጠሩ

እነ ብርሃኑ ተ/ያሬድ ለህዳር 21 ተቀጠሩ
‹‹የሽብር ተከሳሽ በመሆናችን ህክምና ተከልክለናል›› ተከሳሾቹ
በነገረ ኢትዮጵያ ሪፖርተር

ነገረ ኢትዮጵያ / Negere Ethiopia's photo.
የኢትዮ-ኤርትራ ድንበርን አቋርጠው ኤርትራ የሚገኘውን ግንቦት ሰባት የተባለ በተወካዮች ም/ቤት ሽብርተኛ የተባለ ድርጅትን ሊቀላቀሉ ሲሄዱ ተይዘዋል በሚል የሽብር ክስ የተመሰረተባቸው እነ ብርሃኑ ተ/ያሬድ በድጋሜ ለብይን ቀጠሮ ተሰጥቶባቸዋል፡፡
ዛሬ መስከረም 5/2008 ዓ.ም የፌደራሉ ከፍተኛው ፍርድ ቤት የቀረቡት ብርሃኑ ተ/ያሬድ፣ እየሩሳሌም ተስፋው፣ ፍቅረማርያም አስማማው እና ደሴ ካህሳይ በድጋሜ ለህዳር 21/2008 ዓ.ም ብይን ለመስማት ተቀጥረዋል፡፡ ፍርድ ቤቱ ዛሬ የአቃቤ ህግን ምስክርና የሰነድ ማስረጃ መርምሮ ብይን ይሰጣል ተብሎ ይጠበቅ ነበር፡፡

ተከሳሾቹ በማረሚያ ቤት እየደረሰብን ነው ያሉትን አቤቱታ ለፍርድ ቤት ያሰሙ ሲሆን፣ በተለይ ‹‹የሽብር ተከሳሽ ስለሆንን ብቻ ህክምና ተከልክለናል፤ በማንነታችን ጥቃት እየተፈጸመብን ነው›› ሲሉ ችሎት ፊት ተናግረዋል፡፡ በመሆኑም ፍርድ ቤቱ እነዚህን ችግሮች በተመለከተ ለማረሚያ ቤቱ ትዕዛዝ እንዲሰጥላቸው ጠይቀዋል፡፡ ፍርድ ቤቱ የማረሚያ ቤት ተወካይ ያለውን በማስጠራት ‹‹ማስታወሻ ያዝና አጣራ›› በማለት አልፎታል፡፡

በሌላ መዝገብ የሽብር ተከሳሽ የሆነው በአርባ ምንጭ የሰማያዊ ፓርቲ አስተባባሪ በፍቃዱ አበበ በበኩሉ ቀሪ የመከላከያ ምስክሮቹን ለማሰማት ለህዳር 16/2008 ዓ.ም ተቀጥሯል፡፡

0 comments:

Post a Comment