• ኢቢሲ፣ ይሄን ዘገባ ሰሞኑን ያሰራጨው የት ከርሞ ነው?
1. ወጪው ከ1 ቢ. ብር በታች ነው የተባለው ግንባታ፣ ከ5 ቢ. ብር በላይ ፈጅቶም አላለቀም።
2. ቢበዛ በ3 ዓመት ውስጥ ግንባታው ይጠናቀቃል የተባለው ግድብ፣ 10 ዓመት አልበቃውም።
3. ግድቡ እየተጓተተ ወጪው እንደናረ፣ ከ2001 ዓ.ም ጀምሮ በአዲስ አድማስ ሲዘገብ ቆይቷል።
4. በ2006 ዓ.ም፣ የፌደራል ዋና ኦዲተር፣ ግንባታው መዝረክረኩን ገልጿል – (አዲስ አድማስ)።
5. ነገሩ ሲባባስም፣ አምና፣ የገንዘብ ሚ.ር፣ ለግድብ በጀት አልመድብም ብሏል። (አዲስ አድማስ)።
6. የመንግስት ሚዲያ (ኢቢሲ) እና የመሳሰሉ፣ እነዚህን ዘገባዎች፣ “ጨለምተኛ” ሲሏቸው ነበር።
ከአንድ ቢሊዮን ብር በታች ይፈጃል ተብሎ በ1997 ዓ.ም የተጀመረው የተንዳሆ ግድብ ፕሮጀክት፣ በሁለት ወይም
በሦስት ዓመት እንዲጠናቀቅ ነበር የታሰበው። ምን ዋጋ አለው? ወጪው ከ5 ቢሊዮን ብር በላይ ሆኗል። አስር አመትም
ሞላው። ግን ግንባታው አላለቀም። የሚያሳዝንና የሚያስቆጭ ትልቅ ኪሳራ ነው።
በዚህ መሃል…ኢቢሲ፣ ድንገት ተነስቶ፣ ይህንን የኪሳራ መረጃ ዘንድሮ የሚነግረን፣ የት ከርሞ ነው? ላለፉት ስድስት
አመታት የት ነበር? “የግድቡ ግንባታ፣ በተያዘለት እቅድ፣ እየተከናወነ ነው” የሚል… ከእውነት የራቀ፣ ‘የሌለ’
ዜና ለመስራት ሲተጋ ነበር፡፡ ለዚያውም ለበርካታ አመታት።
እና፣ አሁን ምን አዲስ ነገር ተፈጠረና ነው፣ ‘ግንባታው ተጓተተ፤ ወጪው ሸመጠጠ’ የሚል ዜና የሚያቀርብልን?
ምናልባት፣ በአዲስ መንፈስ፣ ‘ከእንግዲህ ትክክለኛ ዜና እሰራለሁ’ የሚል፣ የአዲስ አመት እቅድ አውጥቶ ይሆን?
ቢሆንማ፣ ጥሩ ነበር።
ግን አይደለም። “ትክክለኛ ዜና የመስራት እቅዱ፣ ለተንዳሆ ግድብ ብቻ ነው” ካልተባለ በቀር ማለቴ ነው። እንዴት
ካላችሁ፣… ኢቢሲ፣ ከተንዳሆ ዜና ጎን ለጎን፣ ስለ ህዳሴ ግድብ ያቀረበውን ዜና መመልከት ትችላላችሁ።
ኢቢሲን ስትከፍቱ፣ “የሕዳሴ ግድብ ግንባታ፣ በተያዘለት እቅድ በጊዜው እየተከናወነ ነው” የሚል ዜና መስማታችሁ
አይቀርም። ለሕዳሴ ግድብ፣ ከፍተኛ ክብር ያላቸው ብዙ ኢትዮጵያዊያን፣ ዜናውን በትኩረት አዳምጠውት ይሆናል።
በእርግጥ፣ በየጊዜው የሚደጋገም ዜና ስለሆነ፣ ‘ሳልሰማው አመለጠኝ’ የምንለው አይነት ዜና አይደለም። ባለፈው
ሳምንት ቢያመልጣችሁ፣ ከዚያ በፊት በወዲያኛው ሳምንት፣ ተመሳሳይ ዜና ሰምታችሁ ሊሆን ይችላል። ካልሆነም፣ በያዝነው
ሳምንት ትሰሙታላችሁ፤… ወይም በሚቀጥለው ሳምንት።
የሕዳሴ ግድብን የሚመለከት፣ የግንባታ ዜና እየተደጋገመ መምጣቱ አይደለም ችግሩ። የሕዳሴ ግድብ፣ እንደ ትልቅነቱ፣
በየጊዜው ከግንባታው ሂደት ጋር ብዙ አዳዲስ መረጃዎች ይኖራሉ። በዚህም ምክንያት፣ የሕዳሴ ግድብ፣ በተደጋጋሚ የዜና
ርዕስ ሲሆን ብንሰማ፣ ችግር የለውም። ችግሩ ሌላ ነው። የተሳሳተ መረጃና የውሸት ዜና፣ (ለዚያውም እየተደጋገመ)
መምጣቱ ነው ችግሩ።
ኢቢሲ፣ እንደተለመደው፣ “የሕዳሴ ግድብ ግንባታ፣ በተያዘለት እቅድ፣ በጊዜው እየተከናወነ ነው” ካለ በኋላ፤ የግድቡ
ግንባታ፣ 47% ላይ መድረሱን ገልጿል። ከምር ለመናገር፣ በትልቅነቱ የሚጠቀስ ግድብ፣ የዚህን ያህል ተገንብቶ
ማየት፣ ቀላል ነገር አይደለም። ብዙ ተሰርቷል። ኢቢሲ፣ ይህችን እውነተኛ ዜና ብቻ መግለፅ እየቻለ፣ “በተያዘለት
እቅድ፣ በጊዜ እየተከናወነ ነው” የሚል ውሸት ለምን ይጨምርበታል? ግራ ያጋባል።
‘ከተያዘለት እቅድ ዘግይቷል። ግንባታው ግን 47% ደርሷል’ ብሎ እንዲዘግብ መጠበቅ ያስቸግራል። ቢያደርገውማ፣
“the truth, the whole truth, nothing but the truth” እንደሚባለው፣ እውነተኛ መረጃ…
የተሟላ እውነተኛ መረጃ፣… ሌላ ነገር (ውሸት) ያልተቀላቀለበት እውነተኛ መረጃ… ይሆን ነበር።
ግን፣ እሺ… ይቅር። እውነተኛ መረጃን አሟልቶ ለመናገር ፈቃደኛ አይሁን። ግንባታው መዘግየቱን ሳይገልፅ ይተወው።
ጎደሎ መረጃ መናገር ይችል ነበር – ግንባታው፣ ምን ደረጃ ላይ እንደደረሰ ብቻ መግለፅ! ያው፣ ‘የተሟላ እውነት’
አይደለም። ግን፣ ቢያንስ ቢያንስ… ውሸት አልተቀላቀለበትም። አይደለም?
ለነገሩ ይህንን እንተወው። ኢቢሲ፣ ‘እንዲህ ቢያደርግ’፣ ‘እንዲያ ቢያደርግ’ እያልን ለምን በከንቱ እንደክማለን።
ኢቢሲ፣ ለዚህ ሁሉ ደንታ ያለው አይመስልም። ደንታ ቢኖረው ኖሮ፣ በየጊዜው እየደጋገመ በድፍረት፣ የሃሰት መረጃ
ይናገር ነበር? አገር ምድሩ የሚያውቀው የሕዳሴ ግድብ ጉዳይ ላይ፣ የሃሰት መረጃ መናገር… ሌላ ምን ትርጉም
ይኖረዋል? በጣም ቀላል ጉዳይ ነዋ።
የግድቡ ግንባታ፣ “በአምስት አመት ውስጥ ይጠናቀቃል” ተብሎ እንደነበር ማስታወስ ያቅተናል? አሁን፣ አራት አመት
ተኩል ሆኖታል። ግንባታው ግን፣ ወደ ማጠናቀቂያው ሳይሆን፣ ወደ ግማሽ ነው እየተጠጋ ያለው። ቢያንስ፣ ተጨማሪ አራት
አመታት ያስፈልጉታል ማለት ነው። ኢቢሲ፣ ይህንን ሳይገነዘብ ቀርቶ ይሆን፣ ቀን ከሌት የተሳሳተ መረጃ
የሚያሰራጨው? እንዴት ሊሆን ይችላል?
አሁን አይደለም፣… ከአመት ከሁለት አመት በፊትም፣ የግንባታ ሂደቱንና አዝማሚያውን ለመገንዘብ ከባድ አልነበረም።
ከሦስት ዓመት በፊት፣ መስከረም 12 ቀን 2005 ዓ.ም፣ በአዲስ አድማስ የወጣውን ዘገባ ማየት ይቻላል።
የመንግስት ፕሮጀክቶችን በሚዳስሰው በዚሁ ዘገባ ላይ፣ የሕዳሴ ግድብ ተጠቅሷል። የሕዳሴ ግድብ የግንባታ ሂደት፣
የታቀደለትን ያህል እየፈጠነ እንዳልሆነ ዘገባው ገልፆ፤ በዚያ አያያዙ፣ ግንባታው ከስምንት እስከ አስር አመት ሊፈጅ
እንደሚችል ይጠቁማል። ይሄ ከሦስት ዓመት በፊት የወጣ ዘገባ ነው። በእርግጥም፣ አሁን እንደሚታየው፣ ግድቡ
በተያዘለት ጊዜ (ማለትም ዘንድሮ) ሊያልቅ አይችልም። ግማሽ ያህል ይቀራል።
ይሄ፣ መንግስትን የመተቸት ወይም የማወደስ፣ የመደገፍ ወይም የመቃወም ጉዳይ አይደለም። ጥሬ መረጃ ነው። ችግሩ፣
ኢቢሲ፣ ለእንዲህ አይነት መረጃ፣ “ፊት የሚሰጥ” አልሆነም። ግን፣ አስቡት። ችግሮችን በመደበቅ፣ ማስተካከል
አይቻልም። “ችግር አለ” ብለን ካልተናገርን፣ “ችግር ብን ብሎ የሚጠፋ” ይመስል! “በተያዘላቸው እቅድ እየተከናወኑ
ነው” ብሎ መናገር ብቻውን፤ “የእቅድ ክንውን” ሆኖ ይመዘገባል ካልተባለ በቀር።
ለእውነተኛ መረጃ፣ “ፊት የማንሰጥ” ከሆነ፣ የመጓተትና የመዘግየት ችግሮች ሲያጋጥሙ፣ ተገቢውን ያህል ትኩረት የሚያገኙበትም ሆነ የሚስተካከሉበት እድል እንዴት ይፈጠራል?
በተንዳሆ እና በሌሎች የስኳር ፕሮጀክት ላይ ያየነው ኪሳራ፣ ሳይስተካከልና መፍትሄ ሳያገኝ ለአመታት እየተባባሰ
የመጣውም በዚሁ ምክንያት ነው። ስለ ተንዳሆ ግድብም ሆነ ስለሌሎቹ ፕሮጀክቶች፣ ኢቢሲ መረጃ ሳያገኝ ወይም ችግሩን
ሳይገነዘብ ቀርቶ ነው?
እሺ፣ አላወቀም፤ አልተገነዘበም እንበል። ግን፣ ለማወቅና ለመገንዘብ ፈቃደኛ እስከሆነ ድረስ፣ ቀላል ዘዴዎችን
አያጣም ነበር። በአዲስ አድማስ ጋዜጣ ላይ የወጡ ዘገባዎችን ማንበብ፣ ያን ያህል ከባድ ስራ አይደለም።
ሌሎች የስኳር ፕሮጀክቶች፣ የተንዳሆ ስኳር ፕሮጀክትም ጭምር፣ በ1997 ዓ.ም በወጣላቸው እቅድ እየሄዱ እንዳልሆነ፣ በ2001 ዓ.ም በአዲስ አድማስ ሲዘገብ አስታውሳለሁ።
የተንዳሆ ግድብ፣ በ98 ዓ.ም፣ ከዚያም በ99 ዓ.ም ይጠናቀቃል ተብሎ፣ በገንዘብ ሚኒስቴር በጀት ተመድቦለት
በፓርላማ ከፀደቀ በኋላ፣ ምን እንደተከሰተ የሚዘረዝር ሌላ ሰፊ ዘገባም በዚሁ ጋዜጣ ቀርቧል። በሰፊው መቅረቡ
አለምክንያት አይደለም። በየአመቱ የሚመደበው ገንዘብ ቀላል አይደለም። ከመቶ ሚሊዮን ብሮች እስከ ቢሊዮን ብር
ይደርሳል። ግን፣ ግድቡ ተገንብቶ አላለቀም። እንደገና፣ የ2000 ዓም. በጀት ሲዘጋጅም፣ ገንዘብ ተመደበለት –
የግድብ ግንባታውን ዘንድሮ ለማጠናቀቅ በሚል። ግን አልተጠናቀቀም።
በቀጣዮቹ አመታትም… በ2003፣ ከዚያም በ2004… ምንም የተቀየረ ነገር የለም። የበጀት ሰነዶቹ ላይ፣ አረፍተ
ነገሮቹ እንኳ አይቀየሩም። “የተንዳሆ ግድብ ግንባታን ለማጠናቀቀ…” የሚለው ፅሁፍ “ኮፒ ፔስት” እየተደረገ
በየአመቱ ይደጋገማል – ዓመተ ምህረቱ ብቻ እየተቀየረ።
የመንግስት ቴሌቪዢን ግን፣ እውነታውን ከመዘገብ ይልቅ (እናም መፍትሄ እንዲበጅለት ከማሳሰብ ይልቅ)፣ የአዲስ
አድማስ አይነት ዘገባዎችን ለማስተባበል ነበር የሚተጋው – ፕሮጀክቶቹ፣ በተያዘላቸው እቅድ በጊዜ እየተገነቡ ነው’
እያለ።
ለዚህ ምላሽ እንዲሆንም ይመስላል፣ “እንደ ተንዳሆ ስኳር ፋብሪካ የመሳሰሉ ትልልቆቹ እቅዶች’ኮ ለአመታት እየተጓተቱ
እስከ ዛሬ መዝለቃቸውን ራሱ መንግስት አይክደውም” የሚል ፅሁፍ በአዲስ አድማስ የታተመው (ሰኔ 2 ቀን 2004
ዓ.ም)። “መቼ ነው መንግስት፣ የማይሳኩትን እቅዶች በግልፅ የሚነግረን” በሚል ርዕስ የቀረበ ትንታኔ ላይ
ከተጠቀሱት ፕሮጀክቶች መካከል አንዱ፣ የተንዳሆው ፕሮጀክት ነው። አዲስ አድማስ እንዲህ፣ እውነተኛ መረጃዎችን
በመስከረም 2005 ዓ.ም ሲዘግብ፣ የመንግስት ሚዲያ በዚያ ሰሞን ምን ዘገበ?
መስከረም 3 ቀን 2005 ዓ.ም የኢዜአ ርዕስ እንዲህ ይላል – “የተንዳሆ ስኳር ፋብሪካ በቀጣዩ ጥር ወር በከፊል ወደ ሥራ ይገባል”።
ለነገሩ፣ የመንግስት ሚዲያ፣ በቀላሉ ለእውነተኛ መረጃ “ፊት ይሰጣሉ” ብሎ መጠበቅ አስቸጋሪ እንደሆነ ለመረዳት
ከፈለጋችሁ፣ የፌደራል ዋና ኦዲተርን ሪፖርት መመልከት ትችላላችሁ። የተንዳሆ ፕሮጀክት፣ እጅጉን እንደተጓተተና
በከፍተኛ የሃብት ብክነት እንደተዝረከረከ፣ ዋናው ኦዲተር ሰፊ ዝርዝር ሪፖርት ያቀረበው በ2006 ዓ.ም ነው። አዲስ
አድማስ ይህንን ዘግቧል። በመንግስት ሚዲያ ግን አልተዘገበም።
ሰሞኑን ድንገት ተነስቶ ግን ፕሮጀክቱ ለዓመታት መጓተቱን የሚገልጽ ዘገባ አሰራጨ፡፡ ለዓመታት ለተጓተተ ፕሮጀክት ለዓመታት የተጓተተ ዘገባ !!
0 comments:
Post a Comment