Thursday, 4 June 2015

የአለም ሀገራት ባሰፈኑት የህግና ፍትህ ስርአት ምዘና ኢትዮጵያ ከ102 የአለም ሀገራት 94ተኛ ደረጃ ተሰጥቷታል



ዎርልድ ጀስቲስ ፕሮጀክት የተባለው በአለም ላይ ፍትህና የህግ የበላይነት እንዲረጋገጥ እሰራለሁ የሚል ተቋም የ 102 የአለም ሀገራትን የፍትህና ህግ ስርአት ደረጃ ይፋ አድርጓል፡፡ ከተለያዩ ሀገራት ከ 100 ሺህ የማያንሱ ህዝቦችን መጠይቅ በማድረግ ጭምር የተጠናቀረው ይህ የተቋሙ ሪፖርት በዚህ ረገድ የኢትዮጵያችንንም ደረጃ ይፋ አድርጓል፡፡ …
የፍትህና ህግ የበላይነት ጉዳይ ብዙ ጊዜ የህግ ሰዎች ስራ ብቻ ተደርጎ ሊታይ ይችላል ነገር ግን ሁላችንንም በየእለቱ የሚያጋጥም የእለት ተእለት ጉዳይ ነው ያለው ተቋሙ የአለም መንግስታት ለዜጎቻቸው ያላቸው ግልጽነትና ተጠያቂነት የሚለካውም በዚሁ መስፈርት እንደሆነ ነው ያስቀመጠው፡፡

ሪፖርቱ በዋናነት የአለም መንግስታት ለዜጎቻቸው የቱን ያክል ግልጽነትና ተጠያቂነት አስፍነዋል የሚለውን ሲያስቀምጥም በአራት መስፈርቶች እንደመዘናቸው ነው የገለጸው፡፡ መንግስታቱ በተጻፉ ህጎችና መረጃዎች ነው ወይ ህዝባቸውን የሚያስተዳድሩት የሚለው ቀዳሚው መስፈርት ሲሆን፣ የዜጎች መረጃ የማግኘት መብት፣ የሲቪክ ማህበራት ተሳትፎ፣ እንዲሁም ቅሬታና አቤቱታ አፈታት በሚሉ አራት መመዘኛዎች ሀገራቱ መገምገማቸው ታውቋል፡፡

በዚህም መሰረት ከአጠቃላይ 102 ሀገራት ውስጥ ስዊድን፣ ኒውዚላንድና ኖርዌይ እጅግ ግልጽ የሆኑ የመንግስት ስርአት የሰፈነባቸው ተብለው የህግና ፍትህ ስርአታቸው ሲወደስ እንደ ማይናማር፣ ኡዝቤኪስታንና ዚምባብዌ ያሉ ሀገራት ደግሞ መንግስታቶቻቸው ዝግ በሆነና ፍትህና ህግ ባልሰፈነበት ሁኔታ ህዝባቸውን የሚያስተዳድሩ ተብለው በመጨረሻዎቹ እርከኖች ላይ ሰፍረዋል፡፡
የኢትዮጵያችንንም ደረጃ ያስቀመጠው ይህ ሪፖርት በአራቱም መስፈርቶች መልካም የሚባል ውጤት እንዳላገነች ነው ይፋ ያደረገው፡፡

በተጻፉ ህጎችና መንግስታዊ መረጃዎች 73ተኛ፣ በመረጃ ማግኘት መብት 79ኛ፣ በዜጎች ተሳትፎ 97ተኛ፣ እንዲሁም በቅሬታ አፈታት ስርአት 89ኛ ደረጃዎችን ያገኘችው ኢትዮጵያችን ይህ ደግሞ በዚህ ሪፖርት በአጠቃላይ ውጤት ከ 102 ሀገራት በ 94ኛ ደረጃ ላይ እንድትሰለፍ እንዳደረጋት ነው የተነገረው፡፡

0 comments:

Post a Comment