የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ) እና የኢትዮጵያ ራዕይ ፓርቲ (ኢራፓ) ግንቦት 16 ቀን 2007 ዓ.ም. የተካሄደውን ጠቅላላ ምርጫ ውጤት እንደማይቀበሉት፣ ግንቦት 25 ቀን 2007 ዓ.ም. በየጽሕፈት ቤታቸው በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ አስታወቁ፡፡
‹‹ባለፉት አራት ምርጫዎች በተከሰቱ ችግሮች ዙሪያ መፍትሔ አስቀምጦ ሙሉ በሙሉ ተሻሽሎ ይካሄዳል የሚል ዕምነት ቢኖረንም፣ ራሱን ሙሉ በሙሉ ወደ አምባገነንነት በቀየረው ገዥ ፓርቲ አፈና፣ ወከባ፣ እስራትና ግድያ የተነሳ ምርጫው ሳይሳካ ቀርቷል፤›› በማለት መኢአድ አስታውቋል፡፡
መኢአድ በምርጫው ዕለትና ከዚያ ቀደም ብሎ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ደረሰብኝ ያላቸውን ችግሮች ዘርዝሯል፡፡ ከአዲስ አበባ በስተቀር ኦሮሚያ፣ አማራና ደቡብ ክልሎችን ጨምሮ አባላቱ መታሰራቸውንና ታዛቢዎቹ ከምርጫ ጣቢያ መባረራቸውን ገልጿል፡፡
‹‹ምርጫው ነፃ፣ ፍትሐዊና፣ ሰላማዊ እንደሆነ ይገለጽ እንጂ በተግባር የታየው ግን የዚህ ተቃራኒ ነው፤›› ብሏል፡፡ ‹‹ሰው እየደበደቡ፣ እያሰሩ፣ እያንገላቱ፣ ከመኖሪያ እያፈናቀሉና የግድ ንብን ምረጡ ብለው ለማስፈራራታቸው ተጨባጭ መረጃ ባለበት ሁኔታ እንዴት ብሎ ነፃ፣ ፍትሐዊና ሰላማዊ ምርጫ እንደተካሄደ የሚያውቀው አፋኙ ሥርዓት ብቻ ነው፤›› በማለት መኢአድ በመግለጫው አስታውቋል፡፡
በምርጫው ምክንያት የታሰሩ የፓርቲ አባላትና ሌሎች የፖለቲካ እስረኞች በአስቸኳይ እንዲፈቱ ጠይቋል፡፡ ‹‹ምርጫው ታዋቂ የሆኑ ዓለም አቀፍ ታዛቢዎችና ከፖለቲካ ገለልተኛ የሆኑ የሲቪክ ማኅበራት ባልተገኙበት ኢሕአዴግ ባደራጃቸው የሲቪክ ማኅበራትና አባብሎ ወደ ታዛቢነት ያሰማራቸው የምርጫ ታዛቢዎች በተገኙበት የተካሄደ በመሆኑ፣ ይህንን የፖለቲካ ድራማ የተከናወነበት ምርጫ የማንቀበለው መሆኑን እናስታውቃለን፤›› በማለት መኢአድ መግለጫውን አጠቃሏል፡፡
የፓርቲውን የወደፊት አቅጣጫ በተመለከተ የፓርቲው ፕሬዚዳንት አቶ አበባው ሲገልጹም፣ ‹‹ከሌሎች ፓርቲዎች ጋር መክረን ዘክረን ወደፊት የምናሳውቀው ይሆናል፤›› ብለዋል፡፡
በተመሳሳይም በዋና ጽሕፈት ቤቱ መግለጫ የሰጠው የኢትዮጵያ ራዕይ ፓርቲ (ኢራፓ)፣ የዘንድሮው ምርጫ በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ መካሄዱን ያስረዱልኛል ያላቸውን የተለያዩ ክስተቶች በማንሳት አስረድቷል፡፡ በፓርቲው ፕሬዚዳንት አቶ ተሻለ ሰብሮና በሌሎች ኃላፊዎች በተሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ እንደተገለጸው፣ ለምርጫ ቦርድ ፓርቲው ያቀረባቸው ዕጩዎች ቁጥራቸው ያለምንም አሳማኝ ምክንያት ተቀንሶ ፓርቲው በተወሰኑለት ዕጩዎች ብቻ እንዲወዳደር መደረጉ ከፍተኛ ጫና ፈጥሮበታል፡፡
እንዲሁም በአማራ፣ በደቡብና በኦሮሚያ ክልሎችና በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በዕጩ ምዝገባ ወቅት፣ በቅስቀሳና በምርጫው ዕለት አጋጠሙኝ ያሏቸውን ችግሮች በባለ 6 ገጽ መግለጫው አስታውቋል፡፡ አብዛኛዎቹ ችግሮችም ከዕጩዎች አለመመዝገብ፣ ከአባላት መዋከብና መታሰር እንዲሁም የታዛቢዎች በሥፍራው ተገኝተው መታዘብ ከመከልከላቸው ጋር የሚያያዙ ናቸው፡፡
‹‹ጠጣር ግድፈቶች በተንፀባረቁበትና በተስተዋሉበት ሁኔታ የሕግ የበላይነት ተሟልቷል ተብሎ ከነጉድፉ መቀበል የፖለቲካ ቃር የሚያስይዝ ከመሆኑም በላይ፣ ከቀደምቶቹ ምርጫዎች 2002 እና 2005 (ማሟያና አካባቢያዊ) ባልተለየ መልኩ በአንድ ቅርጫት የተቀመጠ የቅድመ ምርጫ ሒደትና ውጤት በመሆኑ ፓርቲው አልተቀበለውም፤›› በማለት አስታውቋል፡፡
ቀጣይ አቅጣጫቸውን በተመለከተ ከሪፖርተር ለቀረበላቸውም ጥያቄ፣ ‹‹በትግል ደክመን ሳይሆን በመንግሥት ጫና ምክንያት መፈናፈን ባለመቻላችን ምንም እንኳን ዛሬ በዝረራ ብንወጣም፤ ዝረራው ግን ለነገው ቁጭት ጭሮብናል፤›› በማለት መልሰዋል፡፡
ፓርቲው ለወደፊቱ ሁለት አቅጣጫዎች ማዘጋጀቱን ገልጿል፡፡ አንደኛው ብሔራዊ መግባባትን ማስገኘት የሚል ሲሆን፣ ሁለተኛው ደግሞ ከሌሎች ፓርቲዎች ጋር አብሮ መሥራት የሚሉ ናቸው፡፡
0 comments:
Post a Comment