Sunday, 17 May 2015

ትግሉ – ከሰላማዊ ወደ ትጥቅ ትግል እየተሸጋገረ ነው!

አንዳንድ ወጣቶች የሰላማዊውን ትግል በመተው፤ ወያኔን በትጥቅ ትግል ለመታገል ቆርጠዋል። ከነዚህ ወጣቶች መካከል ተስፋሁን እና ጓደኞቹ ተጠቃሾች ናቸው። የቀድሞ የመኢአድ አመራር አባል የነበረው ተስፋሁን የኢህአዴግ እመቃ ስለሰለቸው፤ ድንበር አቋርጦ ኤርትራ ገብቶ የግንቦት ሰባት አርበኞች ግንባርን ተቀላቅሏል። በዚህ ምክንያት አዎንታዊ እና አሉታዊ አስተያየቶች ከዚህም ከዚያም ሲነበቡ እና ሲደመጡ ቆይተዋል። በእርግጥም አሁን ያለው የፍትህ እጦት እና አፈና ሰላማዊውን ትግል የሚያስተው አይነት ነው። እናም ሁኔታውን ለሚቃኝ ሰው… ትግሉ – ከሰላማዊ ወደ ትጥቅ ትግል እያመራ መሆኑን ለመታዘብ ይችላል። ዳዊት ሰለሞን ግራ እና ቀኙን ከተመለከተ በኋላ ተስፋሁንን ለሚያወግዙት የሚከተለውን ምላሽ ሰጥቷል። መልካም ንባብ።

እርግጥ ነው ስልጡን በሆነው በዚህ ክፍለ ዘመን ገዳይ መሳሪያ ተሸክሞ የአእምሮ ጭማቂ በሆነው ሶሻል ሚዲያ ብቅ ማለት አያስሞግስ ይሆናል፡፡ክፋቱ ግን ዘመኑ ይሰልጥን እንጂ ከዘመኑ ጋ መሰልጠን የተሳናቸው የኢትዮጵያ መሪዎች ዛሬም በድንጋይ ዳቦ ዘመን አስተሳሰብ ‹‹በላ ልበልሃ››ን መምረጣቸው በሰላማዊ የፖለቲካ አስተሳሰብና በአእምሮ ጨዋታ ሊፋለማቸው ዘምኖ የነበረውን ተስፋሁንን ወደ ድንጋይ ዳቦ ዘመን መልሰውታል፡፡


ተስፋሁን ከሰላማዊ ትግል - ወደ ትጥቅ ትግል።
ተስፋሁን ከሰላማዊ ትግል – ወደ ትጥቅ ትግል።

‹‹ሌጋሲህን እናስቀጥላለን››የሚሉ መፈክሮችን ክንዳቸው እስኪዝል እየዘረጉ የሚጮሁለት መለስ ዜናዊ ተቃዋሚዎቹን ‹‹በፈለጉት ቋንቋ እናናግራቸዋለን››ማለቱም ሰዎቹ በሁሉም መንገድ ለመጋጠም መዘጋጀታቸውን ያሳያል፡፡ተስፋሁን ከመኢአድ ጋ በመሆን ህወሓትን ለመታገል ‹‹ጠመንጃ ጠል››ሆኖ ቀርቦ ነበር፡፡መረራ እንደሚሉት ግን ህወሓቶች አንደኛውን ምርኩዛቸውን በመጠቀም በመሳሪያ ሐይል የተስፋሁንን ህልም አጨነገፉት፡፡

እናም ተስፋሁን በሚገባቸው ቋንቋ ሊያናግራቸው በረሃ ወረደ፡፡አንዷለም አራጌ እንደሚለው ግን በምትፈልጉት ቋንቋ እናናግራችኋለን የሚሉት የህወሓት አመራሮች በረሃ ወርደው ተስፋሁንን ሊያናግሩት ቀርቶ ‹‹ከመኪናቸው እንኳን የሚወርዱት በሰው ድጋፍ ነው››፡፡ግን ቢሆንም ተስፋሁንን እንዲያናግርላቸው ‹‹የደሃይቱን ልጅ ›› መሳሪያ አስታጥቀው በአገር ዳር ድንበር ማስከበር ስም መላካቸው አይቀርም፡፡

መለስ ዜናዊና የቀድሞ ጓደኞቹ የዩኒቨርስቲ ትምህርታቸውን በማቋረጥ ደደቢት በረሃ በመግባት ደርግን መታገላቸው አሸናፊ ከሆኑበት ግዜ ጀምሮ እንደ ጀግንነት እየተቆጠረላቸው ይነገራል፡፡በቅርቡም ‹‹አርቲስቶች››የትግሉ የመጀመሪያ ጥይት የተተኮሰበትን ስፍራ በመጎብኘት አድናቆታቸውን ሲገልጹ ተመልክተናል፡፡

ተስፋሁንስ ? አሸናፊ ሆኖ ሲመጣ ‹‹አርቲስቶች›› የትግሉን የመጀመሪያ ቦታ በመጎብኘት ውዳሴ ሊያቀርቡለት ነው? እስከዛው ግን ሊወገዝ?
እውነት ነው ዛሬ ላይ መሳሪያ ማነገት የጀግንነት ምልክት ላይሆን ይችላል፡፡ይህ ወጣት ግን መሳሪያ የያዘውን ሕወሓትን ባዶ እጁን ሲታገል የከረመ ጀግና ነው፡፡እምነቱ ሰላማዊነት የነበረ ቢሆንም ያልሰለጠኑት ህወሓቶች ከእምነቱ ውጪ ገፍተው አውጥተውታል፡፡
ተስፋሁንና መሰሎቹን ወደዚህ ሜዳ የገፉ ህወሓቶች ማፈር ይኖርባቸዋል፡፡ሽብርተኛው ተስፋሁን ሳይሆን በሰላማዊ መንገድ በአገሪቱ ለውጥ ለማምጣት የሚሰሩ ዜጎችን እየገፉ ወደዚህ ጠርዝ የወሰዱ ሁሉ ሊወገዙ ይገባቸዋል፡፡

0 comments:

Post a Comment