Thursday, 7 May 2015

ፍ/ቤቱ በ‹‹በሁከትና ብጥብጥ›› ለተጠረጠሩ 17 ሰዎች ዋስትና ሲፈቅድ፣ በሰማያዊ አባላት ላይ ተጨማሪ ቀጠሮ ሰጥቶባቸዋል


ሚያዝያ 14 ቀን 2007 ዓ.ም መንግስት አይ.ኤስ.አይ.ኤስ ሊቢያ በሚገኙ ንጹሃን ኢትዮጵያውያን ላይ የፈጸመውን አሰቃቂ የሽብር ድርጊት ለማውገዝ ጠርቶት በነበረው ሰልፍ ላይ ‹‹ሁከትና ብጥብጥ አስነስታችኋል፤ ተካፍላችኋልም›› በሚል ፖሊስ ካሰራቸው ሰዎች መካከል ፍርድ ቤት 17ቱን በ3000 ብር የሰው ዋስ እንዲለቀቁ ሲወስን የሰማያዊ ፓርቲ አባላት ላይ ደግሞ ተጨማሪ ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡

ዛሬ ሚያዝያ 28 ቀን 2007 ዓ.ም በቄራ የፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት የቀረቡ የሰማያዊ ፓርቲ አባላትና ሌሎች በዕለቱ የተያዙ ሰዎችን በተመለከተ ፖሊስ ተጠርጣሪዎችን በሦስት መዝገቦች ስር እንደየተሳትፏቸው አደራጅቻለሁ ማለቱ የሚታወስ ሲሆን፣ ከአሁን በፊት በሦስተኛው መዝገብ ላይ የተካተቱትን ሙሉ ለሙሉ መልቀቁን መግለጹ ይታወቃል፡፡ በሁለተኛው መዝገብ ላይ የተካተቱት 17 ሰዎች ደግሞ ዛሬ ፍርድ ቤት ቀርበው በዋስ እንዲወጡ ተወስኗል፡፡


አንደኛው መዝገብ ላይ በእነ ወይንሸት ሞላ መዝገብ 5 ሰዎች የተካተቱ ሲሆን አራቱ የሰማያዊ ፓርቲ አባላት የሆኑት ወይንሸት ሞላ፣ ዳንኤል ተስፋዬ፣ ኤርሚያስ ጸጋየ እና ማስተዋል ፈቃዱ ናቸው፡፡ በዚሁ መዝገብ ላይ ፖሊስ የፓርቲው አባል እንደሆነች የሚገልጸው፣ እሷ ግን አባል አለመሆኗን የገለጸች ቤተልሄም አቃለወርቅ ተካትታለች፡፡ በዚሁ በአንደኛው መዝገብ ላይ የተካተቱት 5ቱም ተጠርጣሪዎች ዛሬ በዋለው ችሎት ተጨማሪ 3 ቀናት ቀጠሮ ተሰጥቶባቸዋል፡፡


5ቱም ተጠርጣሪዎች ፖሊስ እስካሁን የተሰጠው የምርመራ ጊዜ በቂ መሆኑንና ቋሚ አድራሻ ያላቸው መሆኑን በመግለጽ የዋስትና መብታቸው እንዲከበር ፍርድ ቤቱን የጠየቁ ሲሆን፣ ፖሊስ በበኩሉ ተጠርጣሪዎች ምስክሮችን ያሸሹብናል፣ ያስፈራሩብናል በሚል ዋስትናውን ተቃውሟል፡፡ ፖሊስ ዋስትና ሲቃወም ‹‹ተጨማሪ አባላትን መያዝ ይቀረናል›› ሲል የገለጸ ሲሆን፣ ‹አባላት› ሲል ምን ለማለት እንደፈለገ ለፍርድ ቤቱ ግልጽ አላደረገም፡፡


በሌላ በኩል አሁን የነገረ ኢትዮጵያ ምንጮች እንደገለጹት ጠዋት ፍርድ ቤት የ3000 ብር የሰው ዋስ የፈቀደላቸው 17 ሰዎች በፖሊስ ይግባኝ እንደተጠየቀባቸውና  ወደ ፍርድ ቤት መወሰዳቸው ታውቋል፡፡

0 comments:

Post a Comment