Monday, 12 January 2015

ትብብሩ ምርጫ ቦርድ የመድብለ ፓርቲ ስርዓትን በር ለመዝጋት እየተጋ መሆኑን አስታወቀ


• ‹‹ምርጫ ቦርድ ለገዥው ፓርቲ በአጥቂነት ቦታ ተሰልፎ እየተጫወተ ነው››

የ9ኙ የተቃዋሚ ፓርቲዎች ትብብር ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ የመድብለ ፓርቲ ስርዓትን በር ለመዝጋት እየተንቀሳቀሰ ነው ሲል ቅሬታውን ገለጸ፡፡ ትብብሩ ጥር 4 ቀን 2007 ዓ.ም በሰማያዊ ፓርቲ ጽ/ቤት በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ እንዳስታወቀው ምርጫ ቦርድ ከህግ አግባብ ውጭ በሆነ መልኩ የፓርቲዎችን ትብብር ‹ህገ-ወጥ› በማለትና በአባል ፓርቲዎቹ መካከል ‹አሰባሳቢና ተሰባሳቢ› እንዳለ በማስመሰል አለመተማመን ለመፍጠር የሚያደርገው እንቅስቃሴ ተቀባይነት የሌለው ነው ብሏል፡፡

ትብብሩ የትብብሩ አባል ፓርቲ የሆነው ሰማያዊ ፓርቲ ከምርጫ ቦርድ ‹‹ትብብር በሚል ማሰባሰብን›› እንደ ጥፋት ቆጥሮ ይቅርታ እንዲጠይቅ ደብዳቤ መጻፉ ተገቢነት የሌለውና ትብብሩ የሚያወግዘው መሆኑን አስታውቋል፡፡


ቦርዱ በአደባባይ ‹‹ፓርቲዎችን በእኩል ዓይን ነው የምመለከተው፣ በሆደ ሰፊነት እያስተናገድኩ ነው›› ቢልም፣ በፓርቲዎች መካከል አድሎ እንደሚፈጽም በማስረጃ ማስረዳት እንደሚችል የገለጸው ትብብሩ፣ የሚከተሉትን ነጥቦች በዋቢነት አንስቷል፡፡


1. ገዥው ፓርቲ/መንግስት ‹‹ነጻነት ለፍትሓዊ ምርጫ›› በሚለው ፕሮግራማችን ህገ-መንግስታዊ መብታችን ተጠቅመን የጠራናቸው የአደባባይ ስብሰባዎችና ሰልፍ በማፈን ህገ-ወጥ እርምጃ ሲወስድ ቦርዱ ‹‹ህገ ወጥና እኔ የማላውቀው ትብብር ነው›› በሚል ክስ ማቅረቡ፣


2. ለሰማያዊ ፓርቲ በጻፈው ደብዳቤ የትብብሩን አባል ፓርቲዎች በማበላለጥ አሰባሳቢና ተሰብሳቢ፣ የሁከት ጠንሳሽና ጀሌ፣ በማለት ያለ መተማመን ስሜት በመፍጠር ለመከፋፈል ያደረገው ሙከራን መጥቀስ ይቻላል ብሏል በመግለጫው፡፡


ፓርቲዎች በትብብር የጋራ አቋም ለመውሰድም ሆነ የጋራ ተግባር ለመፈፀም የቦርዱ እውቅና እንደማያስፈልግ፣ ከዚህ በፊት ለበርካታ ጊዜያት ፓርቲዎች በጋራ የጠሯቸውን ሰላማዊ ሰልፎች፣ በህጋዊ ሰውነታቸው የመሰረቷቸውን ግንኙነቶች (የኢተፓዴኀ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት፣ መኢአድ፣ ኦብኮ፣ ደቡብ ህብረት ኀብረትና አማራጭ የመሰረቱትን ‹ትዲኢ›› እና 33ቱ) አውቀው መርሳታቸው፣ ገዥው ፓርቲ አምስት ክልሎችን ከሚመሩ ፓርቲዎች ጋር አጋር በሚል የሚያደርገው ግንኙነት ከእኛ ትብብር ቀርቶ በግንባር ከተደራጁ ያለፈና የጠነከረ መሆኑ የአደባባይ ምስጢር ሆኖ ለዘመናት በዘለቀበትና አንድም ቀን ጥያቄ ባላነሳበት፤ ቦርዱ በአዋጅ ባልተሰጠው ሥልጣን ለገዥው ፓርቲ ‹አጋር መልማይ› ወይንም የህወሓት/ኢህአዴግ ‹‹ገንዘብ አዳይ ሆኖ ለተለዩ ፓርቲዎች ዳረጎት በሚሰፍርበት እውነታ ውስጥ ሆኖ ትብብሩ ላይ ጣት መቀሰሩን በማሳያነት አንስቷል፡፡
 

በመሆኑም ‹‹ትብብራችን በገዥው ፓርቲ ላይ የፈጠረውን የፍርሃት ስሜት የትብብራችን የጋራ እንቅስቃሴም ለገዥው ፓርቲ ሥጋት መፍጠሩን ለዚህም ምርጫ ቦርድ ይህን አይነቱን ህገ-ወጥ ፖለቲካዊ ድጋፍ በመገናኛ ብዙሃን በማሰራጨት ህዝቡ የሚሰጠንን ሁለንተናዊ ድጋፍ ለመግታት ወይንም ፈሪ ከተገኘ ለማስፈራራትና ለማሸማቀቅ የሚደረግ ተራ ፕሮፖጋንዳ ነው›› ብሏል፡፡
 

በአጠቃላይ ቦርዱ እየፈጸማቸው ያሉትን ተግባራት በህገ-መንግስቱና የምርጫ ህጉንና ሌሎች የአገሪቱ ህጎች ከተጣለበት ከባድ የዳኝነት ኃላፊነት ወጥቶ ለገዥው ፓርቲ በአጥቂነት ቦታ ተሰልፎ የሚጫወት መሆኑንና ይህም በሕገ-መንግሥት የተቀመጠውን የመድብለ ፓርቲ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ሂደት ከደረሰበት ወደኋላ የሚመልስ አካሄድ ነው ሲል ገልጹዋል፡፡ 

በመጨረሻም ትብብሩ ህገ-መንግስቱን አክብሮ እስከተንቀሳቀሰ ድረስ በትብብር ከመስራትና የጋራ ህጋዊና ሰላማዊ ትግል ከማድረግ ለአፍታ እንደማያቆም አስታውቋል፡፡

0 comments:

Post a Comment