Friday, 26 December 2014

የህዝብ ታዛቢዎች ምርጫ ተካሄዷል ብለን አናምንም! ሲል አንድነት ፓርቲ መግለጫ ሰጠ



ከአንድነት ፓርቲ የተሰጠ መግለጫ

ከአንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትሕ ፓርቲ (አንድነት) የተሰጠ መግለጫ

አንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ (አንድነት) ምርጫ ቦርድ ነፃና ገለልተኛ እንዳልሆነ የሚገነዘብ ቢሆንም ባለፈው ታህሳስ 12/04/2007 ዓ.ም የተካሄደው የህዝብ ታዛቢዎች ምርጫ በሀገራችን የምርጫ ቦርድ አለ ወይ?! እንዲል አድርጎታል።
የታህሳሱ 12/04/2007 ዓ.ም የህዝብ ታዛቢዎች ምርጫ ነፃና ገልልተኛ አልነበረም ብቻ ሳይሆን በአጠቃላይ የምርጫ ህጉን ተከተሎ ያልተካሄደ ሌላው ይቅርና የራሱ የምርጫ ቦርድ መመሪያን እንኳን ያልተከተለ ከመሆኑ አንፃር ተካሄዷል ብለን አናምንም። እንዲህ ዓይነቱ ድምዳሜ እንድንደርስ ያደረጉን ምክንያቶች ብዙ ቢሆኑም በዋናነት የሚከተሉት ነጥቦች ከግምት ውስጥ አስገብተናል።

ካገኘናቸው በርካታ ችግሮች ቀዳሚው ህዝቡ በምርጫ ቦርድ በእኩል በይፋ የስብሰባ ጥሪ ያልተደረገለት መሆኑ ነው። ፓርቲው ባሰማረባቸው የምርጫ ጣቢያ ቦታዎች ከሞላ ጎደል በአንድ ለአምስት ስርዓቱ ካደራጃቸው የራሱ አባላትና ደጋፊዎች በስተቀር ሌላው ህዝብ ሳያውቅ ነው የተካሄደው ማለት ይቻላል። ይሄ ደግሞ ከአስር ሺዎች በላይ ነዋሪ ያለባቸው አከባቢዎች ሀምሳ እና መቶ ሰው የተገኘባቸው አዳራሾች ነበሩ። የምርጫ ቦርድ መመሪያ ቁጥር 3/2001 አንቀጽ 9/3/ሀ ህዝቡ በይፋ በምርጫ ቦርድ በእኩል መጠራት አለበት ይላል፤ ይሄ ህግ በዘንድሮው የህዝብ ታዛቢዎች ምርጫ ላይ ተፈፃሚ አልሆነም።

ሌላው በመመሪያው አንቀፅ 7/3 የህዝብ ታዛቢዎች ሲመረጡ ተወዳዳሪ የፖለቲካ ድርጅቶች በምርጫ ቦርድ በይፋ መጋበዝ አለባቸው ቢልም ፅድቁ ቀርቶብኝ በቅጡ በኮነነኝ እንደሚባለው በመላ ሀገሪቱ ምርጫው ሂደት ለመታዘብ የተሰማሩ አባላቶቻችን በፀጥታ ኃይሎች ለእስርና እንግልት ተፈፅሞባቸዋል፤ በዚህ ምክንያት በዕለቱ በተለያዩ አከባቢዎች ከአንድነት ፓርቲ ብቻ ከአስራ ስድት አባላት በላይ በፖሊስ ለሰዓታት ታግተዋል። ከዚህ የምንረዳው ተወዳዳሪ የፖለቲካ ድርጅቶች በህዝብ ታዛቢ ምርጫ ላይ እንዳይገኙ ተፈልጓል ማለት ነው፤ ይህ ደግሞ በዕለቱ የተፈፀሙትን እጅግ በጣም አሳፋሪና ህገወጥ ተግባራት በቦታው ተገኝተው እንዳይታዘቡ ለማድረግ ነው ካልሆነ ሌላ ምክንያት ሊኖረው አይችልም።

ከሁሉም ነገር በላይ የህዝብ ታዛቢ ምርጫው አሳሳቢ የሚያደርገው ደግሞ በበርካታ አከባቢዎች ምንም ዓይነት ምርጫ ያልተካሄደ መሆኑ ነው፤ በ2002 ምርጫ ታዛቢ የነበሩ ሰዎች እንዳሉ ለዘንድሮው የ2007 ምርጫም ታዛቢ እንዲሆኑ በጅምላ እንዲፀድቅላቸው የማደረጉ ጉዳይ ነው፤ በዚህ ምክንያትም በአሁኑ ሰዓት በአከባቢው የሌሉና የሞቱ ሰዎችም ጭምር የህዝብ ታዛቢ ሆነው የተመረጡበት ሁኔታ ተፈጥሯል። ለምሳሌ በአዲስ አበባ በአቃቂ ቃሊቲ ወረዳ 6 ምርጫ ሳይደረግ የቀድሞ የምርጫ ታዛቢዎች ነው በንባብ ስም ዝርዝራቸው የተገለፀው። ምርጫ እንዳዲስ በተካሄደባቸው ቦታዎችም ቢሆኑ በመመሪያው መሰረት አስር አስር እጩዎች ለእያንዳንዱ የምርጫ ጣቢያ መቅረብ ሲገባው አምስት ሰው ዝም ብሎ በቀጥታ እየተጠቆሙ እንዲያልፉ መደረጉ ይሄም የቦርዱን መመሪያ አንቀጽ 9/4መ የሚጥስ ሆኖ አግኝተነዋል። በእነዚህ የምርጫ አዳራሾች የነበረው ምርጫ ሁኔታ ጠቋሚውም፤ ተጠቋሚውም አንድ ለአምስት በቀበሌና በጎጥ ከተደራጁት ውስጥ መሆኑ ሂደቱ እጅግ አሳፋሪና ተስፋ አስቆራጭ እንዲሆን አድርጎታል።

በአንዳንድ አከባቢዎች የምርጫ ቦርዱ ሰዎች በሌሉበት በቀበሌ አመራሮች የህዝብ ታዛቢ ምርጫው የተካሄደበትም ሁኔታ አጋጥሞናል፤ ለዚህ ጥሩ ማሳያ የሚሆነን በአዳማ ቀበሌ 01 የተካሄደው ነው። የታዛቢዎች ምርጫ ያስፈፀሙት አቶ በዳዳ የተባሉ የቀበሌው ሊቀመንበር ናቸው። እንደዚሁም በደብረ ሲና ከተማ ምርጫውን ያስፈፀሙት የከተማው አፈ-ጉባዔ አቶ ፍቃዱ ሙላት ናቸው።

በሌሎች አከባቢዎች ደግሞ ጭራሽ ምርጫው ያልተካሄደባቸው ቦታዎችም እንደነበሩ የደረሱን ሪፖርቶች ያመለክታሉ። ለምሳሌ በደቡብ ክልል በአማሮ ወረዳ ምንም ዓይነት የህዝብ ታዛቢ ምርጫ አልተካሄደም። እንደዚሁም በዕለቱ እሁድ ወደ ቀበሌ የሄዱ ሰዎች ምርጫው ትናንት ታህሳስ አስር ነው የተካሄደው ተብለው የተመለሱ ነዋሪዎችችም አጋጥሞናል። ለምሳሌ በአዳማ ቀበሌ 06 የህዝብ ታዛቢዎች ምርጫ ተካሂዷል የተባለው በታህሳስ 11/04/2007 ዓ.ም. ነው። እንደዚያም ሆኖ ምርጫው ተካሄዷል በተባለው በዕለት ይካሄድ አይካሄድ ማረጋገጥ አልተቻለም።

በዘንድሮ የተካሄደው የህዝብ ታዛቢዎች ምርጫ ጠቅለል አድርገን ስናየው፤ የህዝብ ታዛቢ ምርጫ ተካሄዷል ማለት የሚቻል አይደለም። ይሄ ሁኔታ በዘንድሮ የሚካሄደው የ2007 ሀገራዊ ምርጫ ነፃ፣ ገለልተኛና ተኣማኒ እንደማይሆን ከወዲሁ የሚያረጋግጥ ነው። አንድነት ቀድሞም ቢሆን ምርጫ ቦርድን ተማምኖ አይደለም ወደ ምርጫው ለምግባት የወሰነው፤ በመሆኑም ኢህአዴግና ምርጫ ቦርድ እያጋለጠ በህዝባዊ ንቅናቄ ህዝቡን አደራጅቶ ትግሉን በቆራጥነት ለመምራት ያለው ቁርጠኝነት ለማረጋገጥ ይወዳል። አሁንም ቢሆን አንድነት ነፃና ፍትሀዊ ምርጫ እንዲደረግ ህዝቡ ተገቢውን ተፅዕኖ ያደርግ ዘንድ ከፓርቲው ጎን እንዲቆምና ተደራጅቶ ለለውጥ እንዲታገል ጥሪያችንን እናቀርባለን።

አንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትሕ ፓርቲ (አንድነት)
ታህሣሥ 16 ቀን 2ዐዐ7 ዓም
አዲስ አበባ

0 comments:

Post a Comment