የትብብሩ አመራሮች በሰማያዊ ጽ/ቤት በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ እንዳስታወቁት በሁለተኛ ዙር የትብብሩ መርሃ ግብር መሰረት የካቲት 15 ቀን 2007 ዓ.ም በተመሳሳይ ሰዓት በ15 የሀገሪቱ ትላልቅ ከተሞች ላይ ህዝባዊ የተቃውሞ ሰልፎች ይደረጋሉ፤ በአዲስ አበባ፣ በሀዋሳ፣ በባህር ዳርና በአዳማ ደግሞ ህዝባዊ ስብሰባዎች እንደሚደረጉ የትብብሩና የሰማያዊ ፓርቲ ሊቀመንበር ይልቃል ጌትነት (ኢ/ር) በመግለጫው ወቅት ተናግረዋል፡፡
‹‹የመግባቢያ ሰነዳችንና የጥናት ሪፖርታችንን እንዲሁም ከመጀመሪያው ዙር ያገኘውን ተሞክሮ በሠረት በማድረግ ይህን የሁለተኛ ዙር የሁለት ወር ዕቅድ (ከታህሳስ 16 እስከ የካቲት 15 /2007) አውጥቶ በቀዳሚነት ለዋነኛ ባለቤቶቹና ፈጻሚዎቹ ኢትዮጵያዊያን ሲያቀርብ እንደመጀመሪያው ዙር ከጎኑ እንደሚቆሙ ሙሉ እምነት በማሳደር ነው›› ያለው መግለጫው፣ በትብብሩ በኩል በአመራር ከፊት ቆመው ትግሉን ለመምራት ዝግጁነትና ቁርጠኝነት መኖሩን አስረድተዋል፡፡
‹‹የያዝነው የትግል መንገድ ሠላማዊና ህገ-መንግሥታዊ ብቻና ብቻ፣ መጓጓዣችን ዴሞክራሲያዊ ምርጫ፣ መድረሻችን መድብለ ፓርቲ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት፣ እንዲሁም በጉዞኣችን ላይ የቱንም ያህል አረመኔያዊ የኃይል እርምጃ ይወሰድብን፣ ትግሉ የቱንም ዓይነት ዋጋና መስዋዕትነት ይጠይቅ ከጅምሩ ያለመስዋዕትነት ድል የለም ብለን ተነስተናልና ከያዝነው ዓላማ ኢንች የማናፈገፍግና ለቃላችን በጽናት የምንቆም መሆኑን ዳግም እናረጋግጣለን›› ብሏል ትብብሩ በመግለጫው፡፡
እቅዱ የመጀመሪያው ዙር ቀጣይ መሆኑን ያተተው የትብብሩ መግለጫ፣ ‹‹ዓላማችን የምርጫ ሁኔታዎች ባልተሟሉበትና የመራጩ ህዝብ ነጻነት በሌለበት ስለምርጫ መናገር አስቸጋሪ ነው፣ እነዚህ በሌሉበት አማራጭ የምርጫ ኃሳቦች በህዝብ ውስጥ ሊንሸራሸሩም ሆነ አማራጭ ኃሳባችንን ከህዝብ ማድረስ አይቻልም፣ ሚናችንም የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታው አማራጭ ሆኖ መቅረብ ሣይሆን የህወኃት/ኢህአዴግ አጃቢነትና የሀገር ሃብት በአላስፈላጊ መንገድ የማባከን ሥራ ተባባሪነት የዘለለ አይሆንም ከሚል የመነጨ ነው›› ሲል አቋሙን አሳውቋል፡፡ ነጻነት በሌለበት ተጨባጭ ሁኔታ ምርጫ ቧልት ነው ሲልም አክሏል መግለጫው፡፡
ሁለተኛ ዙር ፕሮግራም ዕቅዱ እንደባለፈው ተደጋጋፊ፣ ተመጋጋቢና ተከታታይ ሦስት ዋና ዋና ተግባራትና በሥራቸው አስራ አራት ዝርዝር ተግባራት ማካተቱም ተመልክቷል፡፡ እነዚህ በትብብሩ አስተባባሪ ኮሚቴ ጥልቅና ዝርዝር ውይይት ተደርጎባቸው የጸደቁ ዋና ዋና ተግባራትም፡-
1. የአባላትና የትብብሩ አቅም ግንባታ፡- የትብብሩን አባላት አብሮነት ማጠናከርና የጋራ ዓላማውን የማስፈጸም አቅም ማጎልበት፤
2. የህዝብ ግንኙነት ተግባራት፡- የህዝብ ተደራሽነት ማስፋትና ዓላማ ማስተዋወቅ፣
3. የህዝብ ንቅናቄ መድረኮች ማመቻቸት፡- በአዲስ አበባና የተመረጡ ከተሞች አራት የአዳራሽ/አደባባይ የህዝብ ውይይት፤ በአዲስ አበባና በተመረጡ አስራ አምስት የክልል ከተሞች በተመሳሳይ ቀንና ሰዓት ሰላማዊ ሰልፍ ማድረግን፤ የሚያጠቃልሉ ናቸው፡፡
2. የህዝብ ግንኙነት ተግባራት፡- የህዝብ ተደራሽነት ማስፋትና ዓላማ ማስተዋወቅ፣
3. የህዝብ ንቅናቄ መድረኮች ማመቻቸት፡- በአዲስ አበባና የተመረጡ ከተሞች አራት የአዳራሽ/አደባባይ የህዝብ ውይይት፤ በአዲስ አበባና በተመረጡ አስራ አምስት የክልል ከተሞች በተመሳሳይ ቀንና ሰዓት ሰላማዊ ሰልፍ ማድረግን፤ የሚያጠቃልሉ ናቸው፡፡
በነገረ ኢትዮጵያ ሪፖርተር
0 comments:
Post a Comment