ፓርቲ (መኢዴፓ) አመራር፣ አቶ ክንፈ ሚካኤል ደበበ (አበበ ቀስቶ) ለፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት ያቀረቡት አቤቱታ ውድቅ ተደርጐ፣ የሥር ፍርድ ቤት ውሳኔ ፀናባቸው፡፡
ሰበር ሰሚ ችሎቱ አቤቱታውን ውድቅ አድርጐ የሥር ፍርድ ቤቶችን ውሳኔ ያፀናው፣ በግንቦት ወር 2006 ዓ.ም. ፍርደኞቹ ያቀረቡትን አቤቱታ ሲመረምር ከርሞ ኅዳር 22 ቀን 2007 ዓ.ም. ነው፡፡
ፍርደኞቹ በተጠረጠሩበት የሽብርተኝነት ወንጀል፣ የፌዴራል ከፍተኛ ዓቃቤ ሕግ ኅዳር 10 ቀን 2004 ዓ.ም. ሦስት ክሶችን በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ችሎት መሥርቶባቸው ነበር፡፡ የፀረ ሽብርተኝነት አዋጅ ቁጥር 652/2001 አንቀጽ አራትን በመተላለፍ፣ የሽብርተኝነት ድርጊት ለመፈጸም ማቀድ፣ መዘጋጀት፣ ማሴርና ማነሳሳት፣ በሽብርተኛ ድርጅት ውስጥ መሳተፍና የአገር ክህደት የሚሉ ክሶች እንደተመሠረተባቸው ይታወሳል፡፡
ፍርድ ቤቱ፣ ዓቃቤ ሕግ በሰውና በሰነድ ማስረጃ ድርጊቱን አረጋግጧል በማለት፣ የእነሱን የመከላከያ ማስረጃ ውድቅ በማድረግ ጥፋተኛ ብሎአቸው፣ አቶ አንዱዓለም አራጌን በዕድሜ ልክ ጽኑ እስራት፣ አቶ ናትናኤል መኰንንን በ18 ዓመታት ጽኑ እስራትና አቶ ክንፈ ሚካኤል ደበበ (አበበ ቀስቶ)ን በ25 ዓመታት ጽኑ እስራት ቀጥቷቸው ነበር፡፡
የሥር ፍርድ ቤት የቅጣት ውሳኔን በመቃወም፣ ሦስቱም ፍርደኞች ለፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ማለታቸው ይታወሳል፡፡ ይግባኙን ያስቀርባል ያለው ጠቅላይ ፍርድ ቤት፣ የሥር ፍርድ ቤትን የቅጣት መዝገብ ሲመረምር፣ ‹‹በሽብርተኛ ድርጅት ውስጥ መሳተፍ›› የሚለውን ሁለተኛ ክስ፣ የሽብርተኝነት ድርጊት ለመፈጸም ማቀድ፣ መዘጋጀት፣ ማሴርና ማነሳሳት በሚለው ውስጥ እንደሚጠቃለል በመግለጽ ሰርዞታል፡፡
ሁለተኛውን ክስ የሰረዘው ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ፣ የአቶ ክንፈሚካኤል ደበበን (አበበ ቀስቶ) የ25 ዓመታት ጽኑ እስራት ቅጣት ወደ 16 ዓመታት ጽኑ እስራት ዝቅ ከማድረግ ውጪ፣ የአቶ አንዱዓለምንና የአቶ ናትናኤልን ቅጣት አጽንቶታል፡፡
የሥር ፍርድ ቤት (ከፍተኛው ፍርድ ቤት) የቅጣት አካል ያደረገውን ሁለተኛ ክስ ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ከሰረዘው፣ ቅጣቱም ሊቀንስላቸው እንደሚገባ አቶ አንዱዓለምና አቶ ናትናኤል አቤቱታ ሲያቀርቡ አቶ ክንፈ ሚካኤልም የተቀነሰለት ቅጣት በቂ አለመሆኑን በመግለጽ የአቤቱታ ማመልከቻቸውን አቅርበው ነበር፡፡
የሥር ፍርድ ቤቶች መሠረታዊ የሕግ ስህተት ፈጽመዋል በሚል የቀረበለትን የሦስቱን ፍርደኞች አቤቱታ ተቀብሎ የመረመረው ሰበር ችሎቱ፣ ‹‹ሁለተኛው ክስ ተሰርዞ ቅጣት አልተቀነሰልንም፤›› የሚለውን በመቀበል ያስቀርባል አለ፡፡
ሰበር ችሎቱ መዝገቡን አቅርቦ ሲመለከት፣ የተሰረዘው ክስ ‹‹ወንጀሉን ያቋቁማል ወይስ አያቋቁምም?›› የሚለውን የፍሬ ጉዳይ የሚመለከት መሆኑን ገልጾ፣ ሰበር ሰሚ ችሎቱ የፍሬ ጉዳይ ክርክር እንደማያይና በአቤቱታው መሠረት መሠረታዊ የሕግ ስህተት ተፈጽሟል ማለት እንደማይቻል በመግለጽ አቤቱታውን ውድቅ አድርጐታል፡፡
ቅጣት አልተቀነሰም በሚል ያቀረቡትን አቤቱታ እውነት መሆኑን የገለጸው ሰበር ሰሚ ችሎቱ፣ በወንጀል ሕግ መሠረት ፍርደኞቹ ጥፋተኛ የተባሉበት የወንጀል ድርጊት፣ ከ25 ዓመታት በላይ እንደማያስቀጣ ገልጿል፡፡ በኢትዮጵያ ሕግ የቅጣት ጣሪያው 25 ዓመታት እንደሆነም ጠቁሟል፡፡ ሁለተኛው ክስ ቢሰረዝም፣ የሌሎቹ ክሶች ቅጣት ሲደመር ከ25 ዓመታት በላይ መሆኑንም አክሏል፡፡
ቅጣት አልተቀነሰም ለተባለው አቤቱታ ማየት የሚገባው፣ ተከሳሾቹ ያቀረቡትን የቅጣት ማቅለያ አስተያየትና ከሳሽ ዓቃቤ ሕግ ያቀረበውን የቅጣት ማክበጃ አስተያየት መሆኑንም ሰበር ችሎቱ ተናግሯል፡፡ በዚህ ቅጣትም ዕድሜ ልክ መባሉ ተገቢ መሆኑን ተናግሯል፡፡ ናትናኤልና ክንፈሚካኤል የተቀነሰላቸው በመሆኑ የሥር ፍርድ ቤቶች ውሳኔ የሚነቀፍ አለመሆኑን በማስረዳት አጽንቶታል፡፡
0 comments:
Post a Comment