ሀና
ላይ በተፈጠረው ነገር እጅግ አዝኛለሁ ፣ ሃና ላይ የደረሰው ነገር ሀገሬ ላይ እየደረሰ ያለውን ነገር እንዳስታውስ
ነው ያረገኝ ። ሃናስ ታክሲ ውስጥ ነው የተደፈረችው ፣ ሀገሬ ግን በየጎዳናው ፣ ህገ ወጥ በሆነ የመሬት ንግድ ፣
ህገ ወጥ በሆነ እስር ፣ ህገ ወጥ በሆኑ ሕጋዊ ሌቦች ፣ ህገ ወጥ በሆነ ዶዘር ፣ ህገ ወጥ በሆነ ዱርዬ ቡድን
እዚም እዛም ( ጭኑዋም ተረከዙዋም ፣ እጁዋም ወገቡዋም ተደፍሮዋል ) ።
እንድ ነገር ለማከል ብዙ ሰዎች ” እኔም ሀና ነኝ ” ማለት ጀምረዋል ፣ ያዝልቅላችሁ ፣ ታዲያ በነካ
እኔነታችሁ ” እኔም ራሴ እኔ ነኝ !” በሉኝ ። ክርስቶስ ተመልሶ ቢመጣ ” ሰው ራሱን ሳይሆን ሌላ ሰው መሆን
እንደምን ይቻለው ይሆን ?” ብሎ ያስተምር ነበር ። ለነገሩ ድጋሚ ክርስቶስ መጥቶ ለኛ ቢሰቀል፣ ለምን ተሰቀለ
ብለን ከስቅለቱ እና ከደሙ ተምሳሌተ ትምህርት በመውሰድ ፈንታ ” እኔም ክርስቶስ ነኝ !” የምንል ይመስለኛል ።
ከቻልን ያልሆነውን አንሁን ፣ ወይ ደሞ ነን ስንል ሆነን ብቻ ከሆነ ይሁን ።
አንድ ጥያቄ አለኝ ። የሃና ጉዳይ ያገባኛል ያሉ ድህረ ገጾች ” የሀገሬ ጉዳይ ያገባኛል ማለት እንዴት
ተሳናቸው ?” በሃና ስቃይ የተቆጡ እና ያነቡ አይኖች እንዴት ስለ ህጻን ነብዩ ለመናገር ፈሩ ? ሀና ፍትህ
ያስፈልጋታል ያሉ አንደበቶች እንዴት የሽብሬ ወይም የ በቀለ ገርባ ወይም የእስክንድር መታሰር ብሎም የእስሩ ኢ
ፍትሃዊነት አልታይ አላቸው ? ከሀናነት በፊት እንዴት ራሳቸው ፍትህ እንደሚያስፈልጋቸው መጠየቅ አቃታቸው ። ሃናን
ነኝ ስንልስ ምን ማለታችን ነው ? ሃና ላይ የደረሰው እኔ ላይ እንደደረሰ ያህል ነው ማለት መሰለኝ ? ይደለም ?
ከሆነ ዘንዳ ታዲያ “ታላቁ” ( በትምህርተ ጥቅስ ውስጥ ይሁን ታላቁ የሚለው ቃል ) አዎ ታላቁ የገነት
ሰይጣን ክርስቶስን ” እስኪ ይሄን ድንጋይ ዳቦ አድርገው?” ሲለው ክስቶስ ” ሰው በእሕል ብቻ እንደማይኖር ! ”
ያስረዳዋል ! እኔ ከክርቶስ የተማርኩት ይህንን ነው፣ ነጻነት እኔም አከሌን ነኝ በማለት አይገኝም ፣ በመሆን
ብቻ !!! አንዳንድ ሰዎች ከክርስቶስ ተማርን ብለው የሚሉት ስለ ገነት ማሰብን ነው ። ሰው ሆይ አጠገብህ ያለውን
ገሀነም የሙጥኝ ብለህ እንዴት ስለ ገነት ታወራልህ ? ሰው ሆይ ለኢትዮጵያም እንደ ሃና እንጮኸላት ዘንድ
ኢትዮጵያስ ሀገርህ ታክሲ ውስጥ ትደፈር ወይ ? አደጋ የማያደርስብንን ነገር ብቻ እየመረጥን የነጻነት እና የመብት
ተሙዋጋች መምሰል ማስመሰሉን እናቁም ። አዎ የሃና ቁስል ፣ በተደፈረችበት ሰዓት ያሰማችው ጩኸት ፣ የፈሰሰው ደሟ
ሁሉም ያማል ፣ ያስቆጫል ፣ ያበሳጫል ። ግን ታዲያ እኮ ፍትህ ላንድ ሰው ከተጉዋደለ ለሁሉም እንደተጉዋደለ ነው
። እኔ ሃናን ነኝ ስትል ” በእውነት ግን ነኝ ወይ ብለህ ራስህን ለመጠየቅ አንድ ሰከንድ ይኑርህ ” እኔ
ክርስቲያን ነኝ ስትልም እንዲሁ ፣ እኔ ሙስሊም ነኝ ስትልም እንዲሁ ። እያሳሰበን ያለው የፍትህ መጉዋደል ሳይሆን
የተጉዋደለው ፍትህ ለመጮህ ይመቻል ወይስ አይመችም የሚለው ስለመሰለኝ ነው ። አጠገብህ ያለውን ወንድምህን ሳትወድ
እኔን ያላየከውን እንዴት ልትወድስ ትችላለህ ያለው አሁንም ክርስቶስ ነው ! በ ፌስ ቡክ ገጾቻችን ላይ የለጠፍናት
ሃና አሁን የኢትዮጵያ ሕዝብ ያለበትን የ ሞራል ውድቀት እና የስርዓቱን ዋልጌነት ያሳያል ብላችሁ መቼም ተሯሩጣችሁ
እንደማታነሱት ነው፣ የሃና ደም የስርዓቱ ጭፍግግ የሞራል ድቀት ያፈሰሰው ድንግልና ነው፣ ሃና የተደፈረችው
ሳትወለድ ነው ፣ ሃና የተደፈርችው የዛሬ 23 ዓመት ነው ፣ ሃና ክብሩዋ የተዋረደው ፣ ጭኑዋ በጉልበት የተፈለቀቀው
ዛሬ አይደለም ፣ ትናንት ነው ፣ አጉራ ዘለል ፣ ጥራዝ ነጠቅ ፣ እና ቦዘኔ ስርዓት እና መሪ ኢትዮጵያን መምራት
የጀመሩ ቀን ነው ፣ የሃና ቀሚስ የላላው ። የሃና እናት መቀነት የተፈታው ፣ በ ሬዲዮና በቴሌቪዥን ሕዝቡን
የሚሳደብ መሪ የተፈጠረ ለት ነው ፣ ሃና ከተደፈረች ቆይታለች ። ሃናን የሚደፍር ስብእና ያለው ትውልድ ሲፈጠር ፣
እንደዛ አይነት ትውልድ ኮትኩቶ ያሳደገ ስርዓት ሲፈጠር ሃና ተደፍራለች ። ዛሬ ብዙ ሀናዎች ታስረዋል ፣ ብዙ
ሃናዎች ተገድለዋል ፣ ብዙ ሃናዎች ገና ይታሰራሉ። ወይንሸት ማን መሰለች ሃና እኮ ነች ፣ ርዮት ማን መሰለች ሃና
ራሷ ነች ። እና ሃና ነን ስንል የሚያሳስር እና የማያሳስር እየመረጥን ሳይሆን የሆነውን እና የሆ—ነውን መሆን
አለበት ። ነጻነታችንን ካላስመለስን ሀገር ሃና ትሆናለች መርዎቹዋ ደፍሪዎቹዋ !!!!
አትርሱት ሕዝብ በቁጥርም በመንፈስም ከመንግስት ይበልጣል ስለዚህ ሕዝብ ከቆረጠ ያሸንፋል ። ጊዜ
የመከራ መለኪያ ቁና ቢሆን እንጂ ያለመቻላችን መገለጫ አይሆንም ! እንበርታ !!!! ከ ጨቁዋኞቹ ሳይሆን
ከተጨቁዋኞቹ ጎን መቆም ነው ሃናነት ፣ ሀናነት ትግል ነው ፣ እምቢ ማለት ነው ፣ ውስጡ ሞት ቢኖርበትም ! እኔ
ሃናን ነኝ ስንል ፣ በሞት ጥላ ስር እንኩዋ ብሄድ ሞትን አልፈራም ብሎ ማለት ነው ። አንድ ወዳጄ እንዳለው ”
ኢትዮጵያና ህዝቦቿ ተደፍሯል! ዴሞክራስ፣ መልካም አሥተዳደር፣ ፍትህ፣ ነፃ ምርጭ እና የህግ የበላይነት
ያልተከበረበት አገር አገርቷም ህዝቧም በግዳጅ የተደፍሩ ናቸው።”
0 comments:
Post a Comment