Sunday 16 November 2014

9ኙ ፓርቲዎች የጠሩት የአደባባይ ህዝባዊ ስብሰባ በኃይል ተበተነ-የተወሰደው እርምጃ የስርዓቱን ፍርሃት ደረጃ እንደሚያሳይ ኢ/ር ይልቃል ገለጹ


ዛሬ ህዳር 7/2007 ዓ.ም 9ኙ ፓርቲዎች በትብብር የጠሩት የአደባባይ ህዝባዊ ስብሰባ በፖሊስና በደህንነት ኃይሎች ተበትኗል፡፡ ፓርቲዎቹ ለሰላማዊ ሰልፍና ስብሰባ ማሳወቂያ ክፍል ያሳወቁ ሲሆን የፓርቲዎቹ አመራሮች ለፖሊስና ደህንነቶች ቢያሳዩም ‹‹የምናውቀው ነገር የለም፣ እኛ ታዘን ነው፡፡ ከፈለጋችሁ አለቆቻችን ሂዳችሁ አናግሩ፡፡›› በማለት ለስብሰባው የተዘጋጁትን ቁሳቁሶች ስብሰባው ሊደረግበት ከታሰበው ሜዳ እንዲነሱ አድርገዋል፡፡

የፓርቲዎቹ አመራሮችና በስብሰባው ለመሳተፍ ወደቦታው ያቀኑ አካላት ለማሳመን ጥረት ቢያደርጉም ፖሊስ ግን ህዝቡን በኃይል በትኗል፡፡

9ኙ ፓርቲዎች በትብብር የጠሩትን የአደባባይ ህዝባዊ ስብሰባ በኃይል መበተኑ የስርዓቱ የፍርሃት ደረጃ ጫፍ መድረሱን ያሳያል ሲሉ የትብብሩ ሊቀመንበር ኢ/ር ይልቃል ጌትነት ገለጹ፡፡

ኢንጅነር ይልቃል በተለይ ሰማያዊ ፓርቲ ከአሁን ቀደም እንደሚያደርገው ለምን እስከመጨረሻው አንበተንም አላላችሁም? ተብለው ተጠይቀው  ‹‹የአንድ ወር መርሃ ግብር አውጥተናል፡፡ ምርጫው ነጻና ፍትሓዊ እስኪሆን ድረስ የነጻነት ትግሉ የሚቀጥል ነው፡፡ በአራት ኪሎ አካባቢ የሚኖሩ ዜጎችን ጠርተን ልናነጋግር በሞከርንበት ወቅት ብዙ እስርና ደብደባ ተፈጽሟል፡፡ ከዚህ የስርዓቱ ፍርሃት አንጻር ገና በመጀመሪያው ስራችን ወደኃይል እንዲገባ አልፈለግንም፡፡ ለሚቀጥሉት ስራዎቻችን ስንል ነው፡፡ ለሚቀጥለው ያንን በሚመጥን ደረጃ መዘጋጀት አለብን፡፡›› ብለዋል፡፡

ኢንጅነር ይልቃል ጌትነት አክለውም ‹‹እኛ ዛሬ የአራት ኪሎን አካባቢ ሰዎች ነው የጠራነው፡፡ በዚህ ደረጃ ፈርተው ይህን ስብሰባ ያግዳሉ ብሎ ለመገመት ይከብዳል፡፡ ድሮውንም የሌላቸው የህዝብ ድጋፍ ጭራሹን እንደተሟጠ ነው የሚያሳየው፡፡ ትንሹም ነገር ለስልጣናቸው አስጊ ነው ብለው ማሰባቸው የፍርሃት ደረጃቸው ጫፍ እንደደረሰ ያሳያል፡፡›› ብለዋል፡፡


0 comments:

Post a Comment