Saturday, 15 November 2014

የ 9ኙ ፓርቲዎች ‹‹ነጻነት ለፍትሓዊ ምርጫ›› መርሃ ግብር የመጀመሪያ ክፍል በታሰበለት ጊዜና ቦታ ይካሄዳል


10359898_1498367410433215_3013403061198377504_n

• የሰማያዊ ፓርቲ ሁለቱ ከፍተኛ አመራሮች ተፈትተዋል

9ኙ ፓርቲዎች ለአንድ ወር ያዘጋጁት ‹‹ነጻነት ለፍትሓዊ ምርጫ›› መርሃ ግብር የመጀመሪያ አካል የሆነው ነገ እሁድ ህዳር 7/2007 ዓ.ም የሚካሄደው የአደባባይ ህዝባዊ ስብሰባ በታሰበለት ጊዜና ቦታ እንደሚካሄድ የሰማያዊ ፓርቲ የህዝብ ግንኙነት ገልጸዋል፡፡
የህዝብ ግንኙነቱ አቶ ዮናታን ተስፋዬ ለነገረ ኢትዮጵያ እንደገለጸው የአደባባይ ስብሰባውን ለማደናቀፍ ከገዥው ፓርቲ ከፍተኛ ጫና የተደረገ ቢሆንም በፓርቲዎቹ ትብብርና በአባላቱ ቆራጥነት ስብሰባው በታቀደለት ጊዜ ይካሄዳል ብለዋል፡፡
በሌላ በኩል የታሰሩትን የሰማያዊ ፓርቲ አባላትና አመራሮች ለመጠየቅ ወደ ፖሊስ ጣቢያ ባቀኑበት ወቅት የታሰሩት አቶ ወሮታው ዋሴና አቶ ብርሃኑ ተክለያሬድም በምሽት የተለቀቁ ሲሆን ስብሰባውን ውጤታማ ለማድረግ የበኩላቸውን አስተዋጽኦ በማድረግ ላይ መሆናቸው ታውቋል፡፡

በነገው ዕለት የሰማዊ፣ መኢአድ፣ መኢዴፓ፣ የኦሞ ህዝቦች ዴሞክራሲያዊ ድርጅት፣ የከንባታ ህዝቦች ኮንግረንስና ሌሎች የ9ኙ ፓርቲዎች አመራሮች ተገኝተው ንግግር እንደሚያደርጉ ይጠበቃል፡፡

የነገው የአደባባይ ስብሰባ አስተባባሪ የሆነው የሰማያዊ ፓርቲ የህዝብ ግንኙነት አቶ ዮናታን ተስፋዬ በትብብሩ ሂደት የነበሩና በተለያዩ ምክንያት እስካሁን ያልፈረሙ እንዲሁም ሌሎች ፓርቲዎች በስብሰባው በመገኘት ለትግሉ የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

በተጨማሪም በአገር ውስጥ በተለይም አዲስ አበባ ውስጥ የሚገኘው ህዝብ በማለዳ በመገኘት የትግሉ አንድ አካል እንዲሆን፣ እንዲሁም በአካል ተገኝቶ ትግሉን መቀላቀል የማይችለው በውጭ የሚገኘው ኢትዮጵያዊ በተለያዩ መንገዶች ለህዝቡ ጥሪውን በማስተላለፍና በመቀስቀስ፣ በሞራል፣ በፋይናንስና በሌሎችም ጉዳዮች ትግሉን እንዲደግፍ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ነገረ ኢትዬጲያ

0 comments:

Post a Comment