Friday, 14 July 2017

የአቶ በቀለ ገርባ የሽብር ክስ ዉድቅ ተደረገ

በኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግረስ ተቀዳሚ ምክትል ሊቀ-መንበር በአቶ በቀለ ገርባ ላይ ከሽብር ጋር ተያይዞ የቀረበባቸዉ ክስ ውድቅ ተደረገ። ዛሬ ያስቻለው አራተኛ ወንጀል ችሎት ልደታ ምድብ አቶ በቀለ የተከሰሱበት ጉዳይ በመደበኛ የወንጀል ክስ እንዲታይ መበየኑን ጠበቃ አመኃ መኮንን ለዶይቼ ቬለ ገልፀዋል።


በፀረ-ሽብር አዋጁ አንቀፅ 3 የሽብር ድርጊት ፈፅመዋል የሚል ክስ ቀርቦባቸው የነበሩት አቶ ጉርሜሳ አያኖ፤ አቶ ደጀኔ ጣፋና አቶ አዲሱ ቡላላም ክሳቸው በሽብርተኛ ቡድን ውስጥ መሳተፍ ወደሚል ተቀይሮ ተከላከሉ ተብለዋል። ከነዚህ ሌላ አምስት ተከሳሾች ሰባተኛ ዘጠነኛ አስረኛ አስራ ሦስተኛ 22ተኛ ተከሳሾች ምንም መከላከል ሳያስፈልጋቸዉ በነፃ እንዲሰናበቱ የሚል ዉሳኔ ተላልፎአል። 

ቀሪ ተከሳሾች ከፀረ ሽብር ድርጅቶች ግንኙነት በማድረግና በመሳተፍ የሚል ሲሆን ይህንን የሚያስረዳ መረጃ በመኖሩ በዚሁ በቀረበባቸዉ ክስ እንዲከላከሉ መወሰኑን ችሎቱን የተከታተለዉ ዘጋቢያችን ዮሐንስ ገብረ እግዚአብሔር ገልጾልናል። ከችሎቱ በኋላ የአዲስ አበባዉን ወኪላችንን ዮሐንስ ገብረ እግዚአብሔርን እና ጠበቃ አመኃ መኮንን በስልክ አነጋግረናል።

0 comments:

Post a Comment