Friday 14 July 2017

«ማእከላዊ ውስጥ ሴትነቴን ተመስርተው ጥቃት ፈጽመውብኛል» አክቲቪስት ንግስት ይርጋ

በይፋ የተመሰረተብኝ የክስ አይነት፡- የሽብር ክስ ሲሆን (‹‹ህዝባዊ አመጾችን››) በማደራጀትና በሰልፎቹም በመሳተፍ ‹‹የሽብር ቡድኖችን ተልዕኮ በመቀበል ለማስፈጽም መንቀሳቀስ›› የሚል ነው፡፡ የተጠቀሰው የህግ ክፍል ደግሞ የጸረ-ሽብር አዋጅ ቁጥር 652/2001 አንቀጽ 3 4 እና 6 ላይ የተመለከቱትን ድርጊቶች በመተላለፍ ወንጀል ከሌሎች አምስት ሰዎች ጋር በአንደኛ ተከሳሽነት ነው የተከሰስሁት፡፡

የክስ ሂደቱን የሚያየው የፌደራል ከፍተኛ /ቤት ልድታ ምድብ 4 ወንጀል ችሎት ነው፡፡
በእስር በምገኝበት ወቅት የሚከተሉት የመብት ጥሰቶች ተፈጽመውብኛል፡፡

1. በማዕከላዊ ወንጀል ምርመራ እስር ቤት በቀዝቃዛና በጨለማ ክፍል ውስጥ ለረጅም ቀናት አስረውኛል፡፡
2. ያለማንም ጠያቂ፣ ያለሁበት ሁኔታ ሳይታወቅ ታፍኜ ለሳምታት እንድቆይ ተደርጌያለሁ፡፡
3. በማታ ለምርመራ በሚል ከታሰርሁበት ክፍል እያስወጡ ሰብዓዊ ክብሬን በሚያዋርዱ ተግባራትና ማሰቃየት ተፈጽሞብኛል፡፡
4. ክብሬን የሚነኩ፣ በማንነቴ ላይ የተመሰረቱ ስድቦች ተሰድቤያለሁ፡፡
5. ሴትነቴን ተመስርተው ጥቃት ፈጽመውብኛል፤ ሴት ሁኜ መፈጠሬን እንድትጠላ የሚያደርጉ ተግባራትን ፈጽመውብኛል፡፡
6. እርቃኔን አቁመው ተሳልቀውብኛል፡፡
7. የእግር ጥፍሮቼን መርማሪዎቼ ነቃቅለዋቸዋል፡፡ ጥፍሮቼን ከነቀሉ በኋላም ጥፍሮቼ የነበሩበትን ቦታ ቁስል እየነካኩ አሰቃይተውኛል፡፡
8. ጸጉሬን በመንቀልም የኢ-ሰብዓዊ ተግባር ሰለባ አድርገውኛል፡፡
9. ክስ ተመስርቶብኝ ቃሊቲ ከተዛወርሁም በኋላ የሰብዓዊ መብት ጥሰቱ አልቆመም፡፡ ጠያቂ ገደብ ተጥሎብኛል፡፡ እኔን መጠየቅ የሚችለው ቀድሞ ስም ዝርዝራቸው ለእስር ቤቱ አስተዳደር የታወቁ የቤተሰብ አባላት ብቻ ናቸው፡፡ ያም ሆኖ የቤተሰብ አባላትም ቢሆን ከምዝገባ ዝርዝሩ ውስጥ የተካተቱ ካልሆኑ መጠየቅ አይፈቀድም፡፡ በማነኛውም የስራ ሰዓት ሳይሆን ከስድስ ሰዓት እስከ ስድስት ሰዓት ተኩል ለሰላሳ ደቂቃ ብቻ ነው የምጠየቀው፡፡ ይህ ገደብ እንዲሻሻልልኝ ለፍርድ ቤት በተደጋጋሚ አቤት ብልም መሻሻል አልቻለም፡፡

0 comments:

Post a Comment