Saturday 9 August 2014

መኢአድና አንድነት ህዝቡ ለትግል እንዲነሳ ጥሪ አቀረቡ

                                          10599505_765562700169148_8550786573985435458_n

የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ) እና ከአንድነት ለዲሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ (አንድነት) በጋራ ባወጡት መግለጫ “በህውሓት/ኢህአዴግ አባላት የሚመራው የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ በሰላማዊ ትግሉ ላይ ከፍተኛ መሰናክሎችን በመፍጠር ከዚህ ቀደም የተደረጉ ምርጫዎች እንዲቀሙ፣ እንዲዘረፉና ኮሮጆ እየተገለበጠ ለገዢው ፓርቲ እንዲሰጥ ከፍተኛ ሚና ሲጫወት መቆየቱ” አንሶ ፣ “ዛሬ በግልጽ ፓርቲዎችን ለመዝጋት መሞከሩ በኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ እየፈፀመው ያለው ከድፍረቶች ሁሉ ድፍረት ነው ” ብሎአል፡፡
” የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ከዚህ አድራጐቱ ተቆጥቦ ትክክለኛ የሆነ የምርጫ ሜዳ የማያዘጋጅ ከሆነ በሰላማዊ ሰልፍና ማንኛውንም የሰላማዊ ትግል ስልቶችን ሁሉ በመጠቀም የምንታገል መሆኑን እናሳውቃለን፡፡” የሚለው መግለጫው፣ ይህን ስናደርግ ሊያስሩን፣ ሊያሳድዱንና ሊገድሉን እንደሚሞክሩ ብናውቅም፣ በሕዝባችን ላይ እየደረሰ ካለው መከራና የሰቆቃ ኑሮ ስለማይብስ የሚደርስብንን ሁሉ ለመሸከም ዝግጁዎች ስንሆን ሕዝባችንም ከጐናችን እንደሚቆም በመተማመን ነው፡፡ ” ብለዋል።
ወጣቱና አዛውንቱ በሚደረገው ማንኛውም የሰላማዊ ትግል እንቅስቃሴ ሁሉ፣ በተግባር ከጐናቸው እንዲቆም፣ በእድሜ የገፉ አባቶችና እናቶች ደግሞ በፀሎታቸው እንዲያግዙ ፓርቲዎቹ ጥሪ አቅርበዋል።
ምርጫ ቦርድ ውህደት ለመፈፀም ያጠናቀቁትን መኢአድና አንደነትን የተለያዩ መሰናክሎችን እንዳይዋሃዱ ለማድረግ እየሞከረ መሆኑንም ፓርቲዎቹ ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ህዝብ ሁኔታውን በጥሞናና በእርጋታ በመከታተል የዜጎችን መብት ለማስከበር በሚደረገው ጥረት ሁሉ ከታጋዩች ጐን እንዲቆም ፓርቲዎቹ ጠይቀዋል።
ለ ደህንነት፣ የፖሊስ እና የመከላከያ ሠራዊቱ አባላት ባቀረቡት ጥሪ ደግሞ ” ጥቂቶቹን በሥልጣን ላይ ለማቆየት አንተ መሰቃየትና መሞት የለብህም፡፡ ጥቂቶቹ ጠንካራ የፖለቲካ ፓርቲዎችን በማጥፋት በሥልጣን ላይ ለመቆየት በሚደረገው አድማና ሴራ የተነሳ ዜጎች ለመብታቸው መከበር ሲንቀሳቀሱ አንተ ዜጎችን ማሰቃየትና መግደል የለብህም፣ አንተም በተመሳሳይ ሁኔታ ለማይጠቅም ነገር መሰዋዕት መሆን የለብህም፡፡ስለዚህ የመንግሥት ሥልጣን ዲሞክራሲያዊና ሰላማዊ በሆነ መንገድ መሸጋገር ይችል ዘንድ በምናደርገው እንቅስቃሴ ሁሉ ለመግደል ሳይሆን ከጎናችን ለመቆም መዘጋጀት አለብህ፡፡ ” ብለዋል።
ፓርቲዎቹ በመጨረሻም ” ዛሬ የህውሓት/ኢህአደግ መንግሥት እየጨቆነህ፣ እያሳደደህ፣ እያሰረህና እየገደለህ ያለው በዘርና በቋንቋ በመከፋፈል ለነፃነትህ በአንድነት እንዳትቆም በማድረግ፣ የኒው ኮሎኒያሊስቶች እንደሚያደርጉት ሁሉ እንደ እድገት የሚቆጠር ብልጭልጭ የሆነና እድገት መሰል ህንፃዎችን በዋና ዋና መንገዶች ዳር በማሳየት ነው፡፡” ካሉ በሁዋላ፣ የአገርህ ባለቤት ሳትሆን የእድገቱም ባለቤት መሆን ስለማትችል በአንድነት በመነሳት ከዚህ አስከፊ የጭቆናና የብዝበዛ ቀንበር ለመውጣት ከጎናችን እንድትቆም ጥሪያችንን እናስተላልፉለን፡፡” ብለዋል።

0 comments:

Post a Comment