Tuesday, 19 August 2014

ጠብ-መንጃ አናነሳም! (ተመስገን ደሳለኝ)

Journalist Temesgen Desalegn
Journalist Temesgen Desalegn
“ብሶት የወለደው” ኢህአዴግ ከሁለት አስርታት በፊት በሰሜን ተራሮች ላይ ከኢትዮጵያ መንግስት ወታደሮች ጋር ያደረገውን የጎሬላ ውጊያ “አጃኢብ” በሚያሰኝ ቆራጥነት በድል መወጣቱ የማይታበል እውነትነው፤ ሥልጣን ከተቆናጠጠ በኋላም ለሚሰነዘርበት ማንኛውም አይነት የኃይል ጥቃት፣ ያውም ማቸነፍ አለማሸነፉን ሳያሰላ በፍጥነት ዘሎ ለመዘፈቅ ሲያንገራግር የተስተዋለበት ጊዜም አልነበረም፤ አሀዱ ብሎ የአመፅ ትግል ከጀመረበት ዕለት አንስቶ ላለፉት አርባ ዓመታት ከጀብሃ እስከ ኢህአፓ፤ ከኦነግ እስከ ኦብነግ፤ ከትህዴን እስከ አርበኞች ግንባር፤ ከሻዕቢያ እስከ አልሸባብ… በስም ተዘርዝረው ከማያልቁ ብረት-ነካሽ ድርጅቶች ጋር ወደ ፍልሚያ ለመግባት ከመወሰኑ በፊት ሰላማዊ መፍትሄዎችን ግራና ቀኝ የመፈተሽ ትዕግስትም ሆነ ልባዊ ፍላጎት እንዳልነበረው የራሱ የታሪክ ድርሳናት ሳይቀሩ በግላጭ ይናገራሉ፡፡ በተለይም ሀገር በቀሎቹ ተቃዋሚ ድርጅቶች በእንዲህ አይነቱ አስገዳጅ ሁኔታ ነፍጥ አንግበው የመገኘታቸው ምስጢር በቀጥታም ሆነ በዘወርዋራው የሥርዓቱ እጅ ስላለበት መሆኑን የሚያስረዱ ማሳያዎች የበዙ ናቸው፡፡ ከነዚህ መሀል አንዱና ዋነኛው በርሱ አጋፋሪነት የፀደቀውን ሕገ-መንግስት፤ በፕሮፍ መስፍን ወልደማርያም አገላለፅ “በሕገ-አራዊት”ነት ቀይሮ በአደባባይ መብቶቻቸውን መጨፍለቁ ነው፤ ከሁሉም በላይ ደግሞ በነፃ ምርጫ ማሸነፍም ሆነ ሥልጣን መጋራትን ‹ግመል በመርፌ ቀዳዳ…›ን ያህል ማጥበቡ እና “መንገዱን ጨርቅ ያድርግላችሁ” የምትለዋ የከረምች እብሪት ድርጅቶቹ “ዱር ቤቴ” እንዲሉ ያስገደዷቸው ገፊ-ምክንያቶች ስለመሆናቸው ቅንጣት ያህል አያጠራጥርም፡፡
በግልባጩ በበርካታ ድርሳናት ስለጀብዱውና ተጋድሎው የተተረከለት አብዮታዊ-ግንባሩ፣ ለሕዝባዊ እምቢተኝነት ፈሪ እና ድንጉጥ የመሆኑ ነገር ተደጋግሞ መወሳቱ ሌላ እውነት ነው፡፡ ብረት ያነሱ ተቀናቃኞቹን በብረት ለመጋፈጥ ካለው ወኔ ይልቅ፣ ሰላማዊ ትግልን በተመሳሳይ ቋንቋ የማስተናገድ ፍርሃቱ እጥፍ ድርብ እንደሚልቅ በተጨባጭ የተረጋገጠ ጉዳይ ነው፡፡ በተለያየ አጋጣሚ በድንጋጤ ሲርበተበት፣ እንቅልፍ ሲያጣ፣ ግብታዊ እርምጃ ሲወስድ… የተስተዋለውም በሕግ የደነገገውን መብት ተንተርሰው የተቀሰቀሱየተቃውሞ ትግሎች የተጠናከሩበት ጊዜያት ላይ ብቻ ነው ብዬ አምናለሁ፡፡ የሰሞኑም ዘመቻ ነፃ-ፕሬስ ግባት ከዚሁ የሚመደብ ነው፡፡
በሰላማዊ የትግል ስልቶች ማዕቀፍ ስር የሚገኙ መብቶታቸውን የተጠቀሙ ቆራጦች ለተቃውሞ በወጡ ቁጥር፣ ቅጥ-ባጣ መልኩ መፍረክረኩን እና የእውር-ድንብር እርምጃ የመውሰዱን እውነታ ለማስረገጥ በተለያየ ጊዜ የተመለከትናቸው ማሳያዎችን እየጠቀሱ መሟገቱ አስቸጋሪ አይደለምና ጥቂቶቹን በአዲስ መስመር ላስታውስ፡-
በ1993 ዓ.ም በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ተማሪዎች የተነሳውንና የአካዳሚያዊ ነፃነትን የጠየቀውን ሰላማዊ ተቃውሞ ተከትሎ በመዲናይቱ የተከሰተው ሕዝባዊ ንቅናቄ ምን ያህል የሚይዝ የሚጨብጠውን አሳጥቶት እንደነበረ ለመረዳት፣ በሃያና ሰላሳ ሺዎች የሚቆጠሩ የከተማይቱን ኗሪዎች (አብዛኛዎቹ በተቃውሞ ያልተሳተፉ) ከየቤታቸው እንዴት አፋፍሶ ለግፍ እስር እንደዳረጋቸው ማስታወሱ በቂ ነው፡፡ በወቅቱ ክስተቱ አገሪቱን ለሁለት ቀናት መንግስት-አልባ አስመስሏት እንደነበረ በተሳታፊነትም በታዛቢነትም ሁኔታውን የተከታተልን ዜጎች ሁሉ አንዘነጋውም፡፡

በ1995 ዓ.ም የሲዳማ ተወላጆች፣ ክልላዊነትን እና የሀዋሳ ከተማ ዕጣ-ፈንታን በሚመለከት ጥያቄ አንስተው በደቡብ ክልል ርዕሰ- መዲና ለተቃውሞ አደባባይ የወጡ ጊዜም፣ አብዮታዊ-ግንባሩ ምን ያህል ፈታኝ ሁኔታ ውስጥ ወድቆ እንደነበረ ማስታወሱ ለዛሬው ጠ/ሚንስትርም ሆነ ለብዙዎቻችን የሚከብድ አይሆንም፤ ሥርዓቱ ያዘመታቸው የመከላከያና የፌደራል ፖሊስ ሠራዊት አባላት ሕጋዊውን የሲዳማ ተወላጆች ጥያቄ ለመቀልበስ፣ ጎዳናዎቹን በደም-አባላ በማጥለቅለቅ የፈፀሙት አሳዛኝ ጅምላ ጭፍጨፋ (ዘር ማጥፋት) በታሪክ መዝገብ ጥቁር ገፅ ላይ በማይፋቅ መልኩ ተከትቦ አልፏል፡፡ ይህም ሆኖ የዚህ ሰላማዊ ተቃውሞ ውጤት፣ ለፌደራል መንግስቱ፣ ክልሉን በኃላፊነት ሲመራ የነበረውን ኃይለማርያም ደሳለኝን፣ በሽፈራው ሽጉጤ እንዲተካ ያስገደደ የሽንፈት ፅዋ ማስጎንጨቱ ይታወሳል፡፡

በምርጫ 97 ዋዜማ ሚያዝያ 30 ‹‹ዴሞክራሲን እናወድስ›› በሚል መሪሕ-ቃል ‹‹ቅንጅት›› በጠራው ስብሰባ ላይ ተገኝቶ መስቀል አደባባይን ያጥለቀለቀው የሕዝብ ‹‹ሱናሜ››፣ ሥርዓቱን ለከባድ ድንጋጤ አጋልጦ፣ በሀፍረት አኮራምቶ፣ ለከፋ ስቃይ ዳርጎት እንደነበረስ ከቶ ማን ሊዘነጋው ይቻለዋል? ያኔ የተመለከትነው ገዥው-ፓርቲን ከፍተኛ ፍርሃት ላይ የጣለ አስደንጋጭ ትዕይንት፣ ዛሬም ድረስ ለሚተገብረው የቅድመ-ምርጫ አደን መስዋዕት እየዳረገን እንደሆነ ሁላችንንም የሚያስማማ እውነታ ነው (በዕለቱ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ‹ምን አልባት ሕዝቡ በቁጣ የቤተ-መንግስቱን አጥር ገርስሶ ሊገባ ይችል ይሆናል› በሚል ፍርሃት ከእነ ቤተሰቡ ደብረዘይት አየር ኃይል ግቢ ተሸሽጎ አሳልፏል የሚለው ወሬ ከሹክሹክታም በዘለለ በከተማዋ በስፋት ተናፍሶ ነበር)፡፡

ሕዝበ-ሙስሊሙ ያቀጣጠለው ከሁለት ዓመት በላይ ያስቆጠረው የተቃውሞ ትግልም፣ አገዛዙን እንዴት በፍርሃት እንዳራደው ለመረዳት በጉዳዩ ዙሪያ በየጊዜው የሚወጡ እርስ-በርስ የተምታቱ መግለጫዎችን እና ረብ-የለሽ ‹‹ዘጋቢ›› ፊልሞቹን መመልከቱ በቂ ነው፡፡ ይህንን ፍፁም ሰላማዊና ስልጡን የተቃውሞ ንቅናቄን ለማፈን የተወሰዱት የኃይል እርምጃዎችም፣ የእነ አባይ ፀሀዬን የይስሙላ ዲሞክራሲያዊ ባህሪ ለዓለም አቀፉ ማሕበረሰብ ከማጋለጡ ባለፈ፣ ድርጅታቸው-ኢህአዴግን ለሳልሳዊ የውስጥ ክፍፍል መዳረጉን የመረጃ ምንጮች ያወሳሉ፡፡
በአናቱም ግንባሩ፣ በተቃውሞ ጎራ በተሰለፉ ሕጋዊ የፖለቲካ ድርጅቶች ውስጥ ነውረኝነቱን በግላጭ በሚያሳይ መልኩ የራሱን ሰዎች አስርጎ በማስገባት ለመከፋፈል ከሚሞክርበት ማኪያቬሊያዊ ሴራ በተጨማሪ፣ አመራሩን እና የነቃ ተሳትፎ የሚያደርጉ አባሎቻቸውን በጥቅማ ጥቅም በመደለል፣ ከሀገር በማሳደድ፣ ከፖለቲካ ተሳትፎ ራሳቸውን አግልለው በፍርሃት ‹‹ጎመን በጤና››ን እያጉረመረሙ የበይ-ተመልካች ሆነው አርፈው እንዲቀመጡ የብረት መዳፉን ለመጫን እና ለመሰል ሕገ-ወጥ ድርጊቶቹ ማስፈፀሚያነት በቢሊዮን የሚቆጠር የአገር ሀብት አፍስሶ ጠንክሮ የመስራቱ (እየሰራም የመሆኑ) ጉዳይ አከራካሪ አይደለም፡፡ ይህንን ኩነት በምኩንያዊነት ለማስረገጥ በኮሙኒኬሽን ጽ/ቤት የአቶ በረከት ስምዖን ምክትል የነበረውና ሀገር ጥሎ የተሰደደውን የቀድሞ ሚኒስቴር ዲኤታን የአቶ ኤርምያስ ለገሰን ምስክርነት መጥቀስ ተገቢ በመሆኑ፣ በቅርቡ ‹‹የመለስ ትሩፋቶች›› በሚል ርዕስ ለንባብ ካበቃው መጽሐፉ አንድ ማሳያ ላቅርብ፡-
‹‹በምርጫ 92 ኢህአዴግ መሸነፉን አስቀድሞ ካረጋገጠ በኋላ የተከተለው ስትራቴጂ የሕዝቡን ውሳኔ ባይቀይረውም ለማጭበርበር ጠቅሞታል፡፡ …የምርጫውን ዴሞክራሲያዊነት የሚያጠፉ ሶስት እርስ በእርስ የሚመጋገቡ ስትራቴጂዎችን ነደፈ፡፡ ስትራቴጂዎቹ እንደሚከተለው ነበሩ፤ በእጩ ምዝገባ ወቅት በተቃዋሚ ፓርቲ እጩዎች ውስጥ ለኢህአዴግ የሚሰራ አስርጎ ማስገባት፤ በየወረዳው ምርጫ ቦርድ በሚፈቅደው መሰረት የተፎካካሪ እጩዎችን ከተቻለ በማሳመን ካልተቻለ በመደለልና በማስገደድ ራሳቸውን እንዲያገሉ ማድረግ የሚሉ ነበሩ፡፡›› (ገጽ 58-59)
በነገራችን ላይ ኤርሚያስ ለገሰ በዚህ መጽሐፉ ለእንዲህ አይነቱ እኩይ ሴራ ስላልተበገረ አንድ ያልተዘመረለት ጀግና በዝርዝር አስፍሮልናል፡፡ ሰውየው በቅፅል ስሙ ‹‹አበበ ቀስቶ›› ተብሎ የሚታወቀው እና በምርጫ 92 በአዲስ አበባ ከተማ በወረዳ 24 ኢዴፓን ወክሎ ለውድድር የቀረበው ክንፈ ሚካኤል ደበበ ነው፡፡ የአገዛዙ ካድሬዎች ክንፈ በአካባቢው ጠንካራ ድጋፍ እንዳለው ጠንቅቀው ያውቁ ስለነበረ ብርቱ ስጋት ላይ ይወድቃሉ፤ በዚህም ‹‹ምርጥ›› የሆነ አደናቃፊ ስልት ተነድፎ ለመተግበር መሞከሩን አቶ ኤርሚያስ እንደሚከተለው ይነግረናል፡-
‹‹(ክንፈ) ከምርጫው ፉክክር ገለል የሚልበት አማራጮች ታሰቡ፡፡ እሱን ማስፈራራቱ የሚታሰብ አልነበረም፡፡ ምድር ቢንቀጠቀጥም የሚፈራ ሰው አይደለም፡፡ በቁጥጥር ስር ለማዋል ደግሞ ወንጀል ሲሰራ እጅ ከፈንጅ መያዝ አለበት፡፡ ስለዚህ የቀረው የመጨረሻ አማራጭ በገንዘብ መደለል ሆነ፡፡›› (ገጽ 65)
ተራኪው ይቀጥላል፤ ለድለላው 50 ሺ ብር ወጪ ይደረጋል፤ በደላይነት ደግሞ ዳኛ ልዑል ገ/ማሪያም (ይህ ሰው የወቅቱ የፍትህ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዲኤታ መሆኑን ልብ ይሏል) እና ኪሮስ የተባሉ የህወሓት አባላት ይመደባሉ፤ አቤም ሊያግባቡት ቤቱ ድረስ በመጡ ግለሰቦች ሃሳብ በመስማማቱ፣ ልዑልና ግብረ-አበሩ 35 ሺውን ለራሳቸው አስቀርተው 15ሺ ብር ይሰጡታል፤ የወረዳው የኢህአዴግ አመራርም በተከተለው ‹‹እፁብ-ድንቅ›› መፍትሔ ለጊዜው ከስጋት ነፃ ይሆናል፤ ግና፣ ይህ ሁኔታ ብዙ አልቆየም፡፡
ከሳምንታት በኋላ፣ ምርጫው ሊካሄድ ጥቂት ቀናት ሲቀሩት ሸገር ተወልዶ፣ ሸገር ያደገው የአራዳ ልጅ አበበ ቀስቶም በታሪክ ሲዘከር የሚኖርበት ውሳኔውን እንዲህ ሲል አረዳቸው፡‹‹የተጋበዝኩትና ብራችሁን የተጠቀምኩት እናንተ ጋር የማይነጥፍ የብር ማምረቻ ስላለ ነው፡፡ ምርጫ የምወዳደረው ግን ለገንዘብ ሳይሆን ይህን አስከፊ ሥርዓት ለመጣልና ለነፃነቴ ነው፡፡ በዚህ ላይ ለመደራደር ህሊናዬ አይፈቅድም፡፡›› (ገጽ 65-66)
ዛሬ ‹‹አሸባሪ›› በሚል ክስ ተወንጅሎ፣ የሃያ አመት የእስር ቅጣት ተላልፎበት፣ በአሰቃቂው የቃሊቲ ወህኒ ተጥሎ የሚገኘው አበበ ቀስቶ እንዲህ ያለ ድፍረትና ቁርጠኝነት የነበረው ጀግና ስለመሆኑ አብዮታዊ ግንባሩን አደግድገው ያገለገሉት ካድሬዎች ጭምር እየመሰከሩለት ይገኛሉ፡፡
ከግል ገጠመኜ ደግሞ አንድ ልመርቅ፤
የ‹‹ፍትሕ›› ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ ሆኜ በምሰራበት ወቅት፣ አቤ በ‹‹አሸባሪ››ነት ተከሶ ፍርድ ቤት ይመላለስ ነበር፤ ከዕለታት በአንዱ ቀንም እጅግ የሚያሳዝንና የግፉአን እናቶችን የሀዘን እንባ የሚወክል ጽሑፍ ከወህኒ ቤት ይልክና በጋዜጣችን ላይ ይታተማል፡፡ ቀደም ብሎ እስክንድር ነጋ፣ አንዱአለም አራጌ እና ናትናኤል መኮንንም በተመሳሳይ መልኩ የላኳቸው ጽሑፎች ተስተናግደዋል፤ ይህ ከሆነ ሁለት ሳምንት በኋላ ‹‹የተከበረው›› ፍርድ ቤት እነዚህን ጽሑፎች እንዲታተሙ በመፍቀዴ ‹‹ችሎት መድፈር›› የሚል ክስ መስርቶብኝ ዳኞች ፊት ቀረብኩ፤ ከአራቱ ታሳሪዎች መካከልም አቤ ተለይቶ ተጠርቷል፤ የመሀል ዳኛውም አንድ ጥያቄ ጠየቀው፡-
‹‹ይህንን ጽሑፍ አንተ ነህ የጻፍከው?››
አበበ ቀስቶ መልስ ለመስጠት አልተቻኮለም፤ ዳኞቹ፣ ዓቃቢ-ሕግጋን እና የችሎቱ ታዳሚዎች በሙሉ ምን ሊል ይችላ ይሆናል? በሚል ጉጉት እየጠበቁት ነው፤ የእኔ አይደለም ቢልስ? ማን ያውቃል? …ጥቂት ሰከንዶች በአስጨናቂ ዝምታ ካለፉ በኋላም፣ ልበ-ሙሉ ፖለቲከኛ ፈገግ ብሎ መናገር ጀመረ፡-
‹‹አዎ፣ እኔነኝ የጻፍኩት! ፍላጎቴም እዚህ እናንተ ፊት ላነብላችሁ ነበር፤ ሆኖም ሰዓት የለንም ብላችሁ ስትከለክሉኝ ጊዜ ነው፣ ለተመስገን የላኩለት!››
(በቀጣዩ ሳምንት ስለመጽሐፉ በስፋት ለመወያየት ቀጠሮ ይዘን፣ ወደጀመርነው ርዕሰ-ጉዳይ እንመለስ)
ስለምን ነፍጥ አናነሳም?
በኢሕአዴግ ዘመነ-አገዛዝ ብረት የማንሳትን ተገቢነት የሚያቀነቅኑ ልሂቃን፣ ለትግሉ ስልት አግባብነት የሚያነሷቸውን መከራከሪያዎች በሁለት መልኩ ልናያቸው እንችላለን፡-
በቀዳሚነት ከገዥው-ፓርቲ ተፈጥሯዊ ባህሪ ጋር አያይዘው፣ ለአቻቻይ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ የሚያስፈልጉ ባህሪያት በፍፁም የማይስተዋሉበት፣ ይልቁንም ‹ሕገ-መንግስታዊነትን፣ የሕግ የበላይነትን፣ የተቋማት ነፃነት፣ ሃሳብን በነፃነት የመግለፅ መብትን፣ የመሰሉ ዕሴቶችን በመጨፍለቅ የሚታወቅ ነው› የሚል ጥቅል መከራከሪያ ያቀርባሉ፡፡ እውነታው እነርሱ እንደሚሉት ቢሆንም እንኳ፣ ብረት የሚቀላቀልበት ትግል የሚያፈራርሳቸውን ማሕበረ-ኢኮኖሚያዊ ተቋማትን እንደገና ከፍርስራሹ ዓመድ ላይ ለመጀመር የሚያስገድድ መሆኑን ግን የዘነጉት ይመስለኛል፡፡
ሁለተኛው ጭብጥ፣ የማሕበረሰቡን የፖለቲካ ባህል እና የአንድ ወቅት የሰላማዊ ትግልን ሙከራ ክሽፈት በማውሳት የሚቀነቀነው ነው፡፡ የፖለቲካ ባህላችን ለጦረኛነት፣ ተዋስኦን ለሚጨፈለቅ የመጠፋፋት መንገድ የቀረበ የመሆኑን መሞገቻ ለክርክር በመግፋት የሃሳባቸው ማጠንጠኛ ያደርጉታል፡፡ ይሁንና የመድበለ-ፓርቲ ሥርዓትን እና ነፃ የአደባባይ ክርክርን ያልተላመደ ማሕበረሰብን አሁንም ለትጥቅ ትግል መጥራት ይህንኑ አሉታዊ ሕዝባዊ ባህርይ ከማጠናከር የዘለለ አንዳች ፋይዳ እንደሌለው ለመሟገት የሚያስችሉ በርካታ ነጥቦች አሉ፡፡ ‹ማሕበረሰቡ ለተራዘመ ሰላማዊ ትግል አይሆንም› ብለው የሚከራከሩ ጸሐፍት የሚጠቅሱት፣ 97 ላይ የተጨናገፈውን እንቅስቃሴና መሰል ሕዝባዊ ተቃውሞን መሰረት በማድረግ ነው፡፡ በተለይም የቅንጅት ጉምቱ ፖለቲከኞች እስኪበቃን እንደነገሩን፣ ስህተቱን ሁላችንም የምንጋራው ይሆናል (የኢሕአዴግ ቢልቅም ቅሉ!)፡፡ ግና፣ የወቅቱ ክስተት ከሰላማዊ ትግል አማራጮች አነስተኛ ሚና የሚሰጠውን የምርጫ ፖለቲካን ብቻ ግብ ያደረገ መሆኑ ‹ትግሉን ሞክረነዋል› የሚለውን መከራከሪያ ያጎደለው ይመስለኛል፡፡
ከዚህ ይልቅ፣ ሰላማዊ ሕዝባዊ አብዮትን አንድም ጊዜ በቅጡ ሳንሞክር (በቀቢፀ-ተስፋ ተሞልተው የሥልጣን ጥማት ካሰከራቸው ቀልባሾች ሳንታደገው) ጠብ-መንጃ ወደማንገብ መመለስ ቢያንስ በቂ መከራከሪያዎችን ያሳጣል ብዬ አምናለሁ፡፡
ከላይ በጥቅሉ ከጠቀስኳቸው ጭብጦች ባለፈ፣ እነዚህ ኢህአዴግ ሥልጣን ከተቆናጠጠበት ማግስት አንስቶ ነፍጥ የነከሱ ቡድኖች፣ንፁሃን ዜጎችን እንዳሻው እንዲያስር እና እንዲያሰድድ ፖለቲካዊ ሰበባ-ሰበቦች ከመስጠት ባሻገር ያዋጡት በጎ አበርክቶ (ተጨባጭውጤት) አለመኖሩን ልብ ማለት ያሻል፡፡
የሆነው ሆኖ የዚህ ጽሑፍ ተጠየቅ ከተለመዱት ሁለቱ የትግል ስልቶች አንዱን መባረክ እና ሌላኛውን ማውገዝ አይደለም፡፡ ይልቁንም በህወሓት ጠቅላይነት የሚመራው ገዥው-ግንባር፣ ከብረት ትግል ይልቅ፣ በሕገ-መንግስቱ ማዕቀፍ ስር ለሚጠቃለሉ ሕዝባዊ ንቅናቄዎች ብርክ የሚይዘው መሆኑን በማውሳት፤ ባለፉት እትሞች በ‹‹ሕዳሴ አብዮት›› የጠቀስኳቸውን አተገባበሮች በበቂ ሕዝባዊ ጉልበት መግፋት እንደሚያዋጣ ዳግም አፅንኦት ለመስጠት ነው፡፡ ርግጥ ነው ሁላችንንም ግራ-ገቡ ኢህአዴግ ፍርሃት በናጠው ቁጥር ሲያሻው በገፍ ወህኒ እያጎረ፤ ሲፈልግ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርታቸውን እንኳን ያልጨረሱ ብላቴኖችን ግንባር በጥይት እያፈረሰ፣ በል ሲለው ደግሞ ይህንን መከራ እና ስቃያችንን የምንተነፍስበት ሚዲያ እያሳጣን በምሬት እንደሞላን አንክድም፡፡ ይህ ሁሉ ሆኖም ግን ድርጅቱ የተካነበትንና ለፍልሚያ የሚመርጠውን ጠብ-መንጃ አናነሳም፡፡ ጠብ-መንጃ የማናነሳው ልበ-ሙሉነታችን ከህወሓት-ኢህዴን መስራቾች የጉብዝና ዘመን ያነሰ ሆኖ በመገኘቱ አይደለም፤ ሚሊዮናት ዘመን ተጋሪዎቼ ለሀገር ጉዳይ፣ ለሕዝብ ጥቅም ግንባራቸውን እንደማያጥፉ አውቃለሁና፡፡ የደኑ መመንጠር ምሽግ ስላሳጣን ወይም የምናፈገፍግበት መሬት ስለጠፋንም አይደለም፡፡ ብረት-ጠል የሆንነው፣ በሰላማዊ ሕዝባዊ ዓመፅ ይህን ሥርዓት አስቁሞ፣ ኢትዮጵያን ማደስ እንደሚቻል ካለን የፀና እምነት ባሻገር፣ ነባራዊውም ሁነት ጮኾ የሚያስረግጥልን ይሄንን በመሆኑ ብቻ ነው፡፡ ይህ ሰላማዊ የመጨረሻ ሙከራ በኢትዮጵያ ሰማይ ስር ዳግም ነፍጥ እንዳይነሳ አስተማማኝ ዋስትናን ሰጥቶ እንደሚጠናቀቅም አልጠራጠርም፡፡ በረዥሙ የጭቆና አገዛዝ በተለይም በእርስ በርስ ጦርነት ለተጎዳና ለደኸየ ሕዝብ፣ የወጣቶቹን ደም ለሚያስገብር ትግል አሳልፎ መስጠት፣ የነገይቱን ኢትዮጵያ ባድማነት ማወጅ ነውም ብዬ አምናለሁ፡፡ እንደዚያም ሆኖ ግን ‹ብረት ያዋጣል› የሚሉ ኃይሎች በመረጡት መንገድ ሥርዓቱን አስገድደው ወደ ብሔራዊ እርቅና አገራዊ ሕዳሴ ሊያመጡልን ከቻሉ፣ የትግላቸው ታላቅ አበርክቶ እንደሚሆን ይሰማኛል፡፡ ወደምናልመው ሁለንተናዊ ሕዳሴ ለመድረስም የሚኖራቸውን ሚና በምንም አይነት መነሾ ላሳንሰው አይቻለኝም፡፡
ከዚህ በላቀ በተከታታይ የተወያየንበት የ‹‹ሕዳሴ አብዮት›› ማዕቀፍ፣ በሕዝባዊ የአደባባይ ዓመፅ ሥርዓቱን ከማውረዱ በዘለለ፣ በደም-እልባት ያጣነውን አንድ ዋነኛ እሴት አውሶን የሚያልፍ ይመስለኛል፡፡ በሰላማዊ አብዮት የሚሳተፍ ዜጋ አገራዊ ሕዳሴን በማምጣት፤ ሁላችንንም በእኩልነትና በነጻነት የሚያኖር ፖለቲካዊ ሥርዓት ማዋለዱ አይቀሬ ነው፡፡ በመጪው አስተዳደር የሚከወኑትን ሀገራዊ ጉዳዮች በያገባኛል የሚከታተል፣ እያንዳንዱን የዜግነት መብቱን አጠንክሮ የሚጠይቅ እና በውይይት (በሃሳብ ብዙሃነት) የሚያምን ትውልድ በ‹‹ሕዳሴ አብዮት›› ሂደት እንደሚፈጠር በእርግጠኝነት መናገር ይቻላል፡፡ የንቅናቄው አድማስ ሁሉን አቀፍ መሆኑ ከተሳካለት ደግሞ በድህረ-ለውጡ የሚነብረውን የፖለቲካ ባህል በእጅጉ የዘመነ ያደርገዋል፡፡ ‹የአብዮተኞች አባት› ተብሎ የሚወደሰው ካርል ማርክስ ከጓዱ ፍሬዴሬክ ኤንግለስ ጋር በጻፈው መድብል ላይ ይህን እውነት አስረግጦ አልፏል፡፡ ‹‹German Ideology›› በሚለው ያሰላሳዮቹ የጋራ ስራ ላይ የአብዮት ሂደት ዋና ፋይዳ ከለውጡ በኋላ የሚፈጠር ማሕበረሰብ የነቃ እንደመሆኑ፣
መጪዎቹ የሥልጣን ተረካቢዎች በቁመቱ ልክ ካልሆኑ (ካልመጠኑት) ለእነርሱም አስቸጋሪ እንደሚሆን የማስረገጡ እውነታ ነው፡፡
ለዚህም የቅርቡን የአረቡ መነቃቃት ማየት ያዋጣል፡፡ የግብፅ ሕዝብ ከአብዮቱ በፊትና በኋላ ያለውን የንቃት ልዩነት ማንም የሚያስተውለው ነው፤ ዛሬ ላይ የምናየው ማሕበረሰብ የሆስኒ ሙባረክ አገዛዝ ከነበረበት አንፃር ሲታይ ፍፁም ፖለቲካዊ ስለመሆኑ በብዙዎች ተወስቷል፡፡ ለእያንዳንዱ አገራዊ ጉዳይ ያገባኛል በማለት መሟገትን የዕለት ተዕለት ስራው አድርጎታል፡፡ ከዚህ አብዮታዊ ሃሳብ ትይዩ በብረት የሚመጣ ለውጥ፣ ተመልሶ ማሕበረሰባዊ ፍዝነት ውስጥ እንደሚጥለን መረዳታችንም፣ መጪውን የአብዮት አማራጭ ብቸኛው ትውልዳዊ ዕዳ ወደማድረጉ ገፍቶታል፡፡ ከሞት ይልቅ ህይወት፣ ከድቀት ይልቅ ጥንካሬ፣ ከመበታተን ይልቅ አንድነት የሚሰጠንን ሰላማዊ የለውጥ ንቅናቄ በቀጣዩ ዓመት ስለመከወን ደግመን ደጋግመን ማሰላሰል ደግሞ የዘመኑ አስገዳጅ ኃላፊነት ነው ብዬ አምናለሁ፡፡
ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር!

0 comments:

Post a Comment