ከመኢአድ የተገለለው ቡድን የምርጫ ቦርድን ሐሳብ ይደግፋል
መኢአድ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ከአንድነት ጋር ልፈጽም ያቀድኩትን ውህደት እያስናከለ ነው ሲል ከሰሰ፡፡
የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ) እና አንድነት ለዲሞክራሲና ለፍትሕ ፓርቲ (አንድነት) ውህደት ለመፈጸም ሲያካሂዱ የቆዩት ድርድር በመግባባት ቢጠናቀቅም፣ በመኢአድ ጠቅላላ ጉባዔ ሒደት ላይ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ጥያቄ በማንሳቱ ሊቋጭ እንዳልቻለ መኢአድ አስታውቋል፡፡
መኢአድ ነሐሴ 13 ቀን 2006 ዓ.ም. በጽሕፈት ቤቱ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የተለያዩ ምክንያቶችን በመፍጠር ውህደቱ እንዳይሳካ በመሥራት ላይ እንደሚገኝ አስታውቋል፡፡
የመኢአድ ፕሬዚዳንት አቶ አበባው መሐሪ እንደገለጹት፣ የመኢአድ ጠቅላላ ጉባዔ አባላት 600 ናቸው፡፡ ፓርቲያቸው ሐምሌ 13 እና 14 2005 ዓ.ም. ባካሄደው ጠቅላላ ጉባዔ 390 አባላት ተገኝተዋል፡፡ ነገር ግን ምርጫ ቦርድ በስብሰባው የተገኙ የጠቅላላ ጉባዔ አባላት 285 ብቻ በመሆናቸው ምልዓተ ጉባዔው አልተሟላም በሚል ምክንያት በጉባዔው የተላለፉ ውሳኔዎችን አልተቀበለም፡፡
ምንም እንኳን እርሳቸው ይኼን ቢሉም፣ በኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ የአገልግሎትና ግንኙነት ዘርፍ ቢሮ ምክትል መምርያ ኃላፊ አቶ ወንድሙ ጎላ፣ ‹‹በወቅቱ አባሎቻችን በርካታ ስለነበሩ የጠቅላላ ጉባዔ አባላትን ቁጥር 600 አድርገናል፡፡ አሁን ግን አባሎቻችን ስለቀነሱ ያን ማድረግ አንችልም፡፡ ያለን 285 ነው፡፡ የምትቀበሉን ከሆነ አስተያየት አድርጋችሁ ተቀበሉን፡፡ አለበለዚያ ምንም ማድረግ አንችልም፤›› የሚል ምላሽ ማግኘታቸውን መዘገባችን ይታወሳል፡፡
‹‹ጉባዔው በ390 አባላት የተካሄደ ስለመሆኑ በቂ መረጃ አለ፡፡ ምርጫ ቦርድ ሆን ብሎ ፓርቲውን ለማፍረስ ከሚንቀሳቀሱ ኃይሎች ጋር እያበረ ነው፤›› ሲሉ አቶ አበባው በምሬት ተናግረዋል፡፡
ምርጫ ቦርድ እዚህ ውሳኔ ላይ ሊደርስ አይገባውም የሚለው የመኢአድ መግለጫ፣ ከምርጫ ቦርድ በተጨማሪ እየተፈጠሩ ላሉት ችግሮች ቀደም ሲል የመኢአድ አባል የነበሩና በዲሲፕሊን ጥሰት ምክንያት ከፓርቲው የተወገዱ አባላትን ተጠያቂ አድርገዋል፡፡
ፓርቲው እንደሚለው በዲሲፕሊን ምክንያት የተወገዱ 14 አባላት ሲሆኑ፣ እነዚህ የተወገዱ አባላት ባለፈው እሑድ ነሐሴ 11 ቀን 2006 ዓ.ም. ከማለዳ ጀምሮ ከመንግሥት የፀጥታ ኃይሎችና ከኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ባልደረቦች ጋር የፓርቲው ጽሕፈት ቤት ላይ ወረራ ፈጽመዋል ብሏል፡፡
በዚህ ሒደት ጽሕፈት ቤት ውስጥ የነበሩት አባላት እንዳይወጡ፣ ለመግባት የሞከሩ አባላት ደግሞ ወደ ጽሕፈት ቤቱ እንዳይገቡ እስከ ቀትር ድረስ አግተው ውለዋል በማለት አቶ አበባው ገልጸዋል፡፡
ይህ ቡድን ከአራት ዓመት በፊት በዲሲፕሊን ጥሰት ከፓርቲው የተወገደና በፍርድ ቤትም እንዲወገድ የተወሰነበት መሆኑን መኢአድ በመግለጫው ጠቅሶ፣ ነገር ግን ከመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች ጋር በመሆን ፓርቲው ላይ ከፍተኛ ጥፋት በመፈጸም ላይ መሆኑን አብራርቷል፡፡
የፓርቲው ፕሬዚዳንት አቶ አበባው እንደገለጹት በዲሲፕሊን የተወገደው ቡድን ወደ ፓርቲው ለመመለስ ፍላጐት አሳይቷል፡፡ ነገር ግን ዕርምጃ የተወሰደበት ቡድን በመሆኑ የመኢአድ የሥራ አስፈጻሚ በሽማግሌዎች አማካይነት የቡድኑን ጥያቄ ለጠቅላላ ጉባዔ ለማቅረብ በሒደት ላይ እያለ፣ ቡድኑ ይህንን ተግባር መፈጸሙ እንዳሳዘናቸው ጠቅሰዋል፡፡
መኢአድ በዲሲፕሊን ተወግደዋል ካላቸው የቀድሞ አመራሮች አንዱ የሆኑት የፓርቲው የቀድሞ ዋና ጸሐፊ አቶ ማሙሸት አማረ ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ድርጅት እንደገለጹት፣ መኢአድ ከአንድነት ጋር ውህደት ለማድረግ ፍላጐት ያለው ቢሆንም፣ ድርጅቱ ጠቅላላ ጉባዔውን ባለማካሄዱ ከብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ጉድለቶቹን እንዲያሟላ በተሰጠው አቅጣጫ መሠረት ለማሟላት አመራሮችና አባላት ለስብሰባ ወደ ፓርቲው ጽሕፈት ቤት ሲያመሩ በር ላይ እንዳይገቡ መታገዳቸውን ተናግረዋል፡፡ ፓርቲው ያወጣው የመተዳደሪያ ደንብ እየተጣሰ ነው ብለው፣ የምርጫ ቦርድ ሕግና መመርያ ወደጎን እየተደረገ ሕገወጥ ድርጊቶች እየተከናወኑ መሆናቸውን አቶ ማሙሸት ገልጸዋል፡፡
ነገር ግን የመኢአድ ፕሬዚዳንት እንደሚናገሩት ደግሞ እነዚህ ሰዎች የታገዱ በመሆናቸው፣ በሽምግልናው መሠረት ቀኑ ደርሶ ጉዳያቸው በጠቅላላ ጉባዔ እስኪታይ ድረስ ቦታ የላቸውም፡፡
ቡድኑ ከምርጫ ቦርድ ጋር ሆኖ እያደረገ ያለው ተግባር የተጀመረው ውህደት እንዳይካሄድ፣ ቢያንስ ለ2007 ዓ.ም. ምርጫ ውህደት ፈጽመው ጠንካራ ተወዳዳሪ ሆነው ለመቅረብ የሚያደርጉትን ዝግጅት የሚያሰናክል ሕገወጥ ተግባር መሆኑን መኢአድ አስታውቋል፡፡
0 comments:
Post a Comment