Monday, 8 January 2018

“በከፍተኛ ጥበቃ ሆኜ እንዳክም ጠይቄ ስላልተፈቀደልኝ የሞቱት ታካሚዎቼ ቁጥር 20 ደርሷል።”

ማርም ሲበዛ ይመራል።……መረረኝ!”
/ ፍቅሩ ማሩ ለፍርድ ቤቱ ከተናገሩት

(በጌታቸው ሺፈራው)

ማርም ሲበዛ ይመራል። በካቴና ታስሬ ቢገለበጥ መውጣት በማልችልበት በሽቦ በታጠረ መኪና ነው ወደዚህ (ወደ ፍርድ ቤት) የምመጣው። ዐቃቤ ሕግ ችሎት ላይ ሞባይሉን አውጥቶ ጌም ይጫወታል። እኔ ወደ እስር ቤት ተመልሼ የምጫወተው ከትኋን እና ከአይጥ ጋር ነው። ሰብአዊነት የሚባል ነገር የለም? እኛ ቀኑን ሙሉ እዚህ ስለምንውል ሊጠይቁን የሚችሉት ቤተሰቦች አያገኙንም። ልብስ እንኳ መቀየር ስላልቻልን አንድ አዳፋ ልብስ(የደንብ ልብስ) ነው የምንለብሰው።

ዛሬ እዚህ እየሆነ ያለው የነገ ታሪክ ነው። ለእናንተ (ለዳኞቹ) ልጆችም የሚደርስ ታሪክ ነው። እንደ ከብት እየተጎተትን እየመጣን ዐቃቤ ሕግ ምስክር አልመጣልኝም እያለ እያጉላላን ነው። ከብት እንኳ ክብር አለው። እኛ ታስረን ዐቃቤ ሕግ በስልክ ደውዬ አላገኘኋቸውም፣ አልመጡልኝም ማለቱ ቀልድ ነው። ባለፈው የነበረው ዐቃቤ ሕግ ዛሬ አልተገኘም። ሚስቱ ጋር ሄዶ ይሆናል። እኛ ግን መሄጃ የለንም።

እኔ በከፍተኛ ጥበቃ ወጥቼ እንዳክም ጠይቄ 15 ወንጀል ችሎት መሃል ዳኛ አንድ ቀን ብቻ ነው የፈቀዱልኝ። እንዲህ ያለ ርህራሄ የሌለው ስርዓት ነው። በእኔ መታሰር እና በከፍተኛ ጥበቃ ሆኜ እንዳክም ጠይቄ ስላልተፈቀደልኝ የሞቱት ታካሚዎቼ ቁጥር 20 ደርሷል።

ከታሰርኩ 4 አመት 8 ወር ሆኖኛል! መረረኝ! የሀሰትና ስሚ ስሚ ምስክር ነው የሚያመጡት። ዐቃቤ ሕግ ምስክር የለኝም እያለ እያጉላላን ነው። እየሰራ ያለው የኢትዮጵያ ህዝብ በሚከፍለው ግብር ነው። ምስክር ከሌለው ማረሚያ ቤት እያለን፣ ወደ ፍርድ ቤት ሳንመጣ መንገር ይችል ነበር። አሁንም ነገ ከሌለው እንዳንመላለስ ይደረግልን።


(ዐቃቤ ሕግ ባለፈው አርብ ታህሳስ 27/2010 ምስክሮችን ሳያቀርብ ቀርቷል። ዛሬም አልቀረቡልኝም ብሏል። ዐቃቤ ሕግ 30 በላይ ምስክሮች እንደቀሩት ቢገልፅም በተደጋጋሚ ሊያቀርብ አልቻለም። ምስክሮቹን ፖሊስ ሊያገኛቸው አልቻለም ቢልም ፖሊስ ይህን ምክንያት ለፍርድ ቤቱ በደብዳቤ እየገለፀ አይደለም። ተከሳሾችና ጠበቆቻቸው ዐቃቤ ሕግ ምስክር አቀርባለሁ ብሎ አልቀረቡልኝም የሚለው ተከሳሾቹን ለማጉላላት፣ ሌላ ተጨማሪ ረዥም ቀጠሮ ለማስቀጠር በመሆኑ ምስክር ለማቅረብ ፍላጎት እንደሌለው ስለሚያሳይ የምስክር ሂደቱ ታልፎ እስካሁን በቀረቡት ምስክሮች ብይን እንዲሰጥ ሲጠይቁ ቆይተዋል። ፍርድ ቤቱ ቀጠሮው የተያዘው እስከ ጥር 3/2010ዓም በመሆኑ በመጨረሻው ቀጠሮ ብይን እሰጣለሁ ብሏል። በየቀኑ የሚቀርቡት የተለያዩ ዐቃቤ ሕጎች በመሆናቸው ምስክሮች ባለመቅረባቸውና ሌሎች ጉዳዮች ለፍርድ ቤቱ በቂ ምክንያት ማቅረብ አልቻሉም። በእነ መቶ አለቃ ማስረሻ ሰጤ ክስ መዝገብ ዐቃቤ ሕግ 80 በላይ ምስክሮች አስመዝግቧል። 30 በላይ ምስክሮችን ይቀረኛል ቢልም ማቅረብ አልቻለም።)


0 comments:

Post a Comment