“የኢትዮጵያ የታሪክ ፈተናዎች እና የሚጋጩ ህልሞች” በሚል ርዕስ አንጋፋው ፖለቲከኛና የፖለቲካ ሣይንስ ምሁር ዶ/ር መረራ ጉዲና ሰሞኑን ለንባብ ካበቁት ሁለተኛ መጽሐፋቸው የተቀነጨበ
… የቡዳ ጉዳይ በሀገራችን ባሕል ውስጥ የታወቀ ስለሆነ ለማስረዳት ዝርዝር ውስጥ አልገባም፡፡ ቡዳና ፖለቲካችንን
ምን አገናኛቸው ለሚለው ጥያቄ ግን ተገቢ መልስ መስጠት ስለአለብኝ አንዳንድ ጭብጦችን ላስቀምጥ፡፡ ተረቱ
እንደሚለው፣ አንድ ቡዶችን ለይቶ የማያውቅ ሰው፣ የቡዶች መንደር ይደርስና፣ “እዚህ አካባቢ የቡዶች መንደር አለ
ይባላል፣ የትኛው ነው” ብሎ ራሱን፤ ቡዳውን ይጠይቀዋል፡፡ ቡዳው ሰው፣ “ቡዶች የምንባለው እኛው ነን” ለማለት
ድፍረት ስላጣ፣ “እኛ እዛ ማዶ ያሉት ናቸው እንላለን፣ እነሱ ደግሞ እኛን ይሉናል” አለ ይባላል፡፡
ላለፉት አርባ ዓመታት ለውጥ ለመምጣት ከአንድ ትውልድ በላይ ቀላል ያልሆነ መስዋእትነት ተከፍሎዋል። የሀገራችን
ፖለቲካ ባለህበት እርገጥ ከመሆን፣ አንዳንዴ ደግሞ የኋሊት ከመሄድ አላለፈም፡፡ ሌሎች የአፍሪካ ሀገሮች ለፀረ –
ቅኝ አገዛዝ ትግል ከከፈሉት በላይ ሀገራችን ውድ ዋጋ ከፍላለች፣ የታሰበው ለውጥ ግን አልመጣም፡፡ እዚህ ላይ ዋናው
ጥያቄ ለሀገራችን ፖለቲካ ምስቅልቅል ጉዞ ኃላፊነቱን የሚወስደው ማነው? የሚለው ነው። ቢያንስ አንዱ በሌላው ላይ
ጣት ከመቀሰር አልፎ የየድርሻችንን እንኳ እንውሰድ ሲባል አይታይም፡፡ እንደቡዳው፤ ስህተት የሠራሁት እኔ ነኝ
ከማለት ይልቅ፤ አጥፊዎች እነዛ ናቸው ማለት ይቀላል፡፡ የአንድ ትውልድ ምርጦችን ያለርህራሄ የጨፈጨፈው መንግሥቱ
ኃይለማርያም እንኳ “ሰው ይቅርና ዝንብ አልገደልኩም” ነበር ያለው፡፡ ተባባሪዎቹ የነበሩ የደርግ ባለሥልጣናትም
ያንን አስከፊ ግፍ የፈጸምነው “የሀገር ፍቅር ያንገበገበን ወታደሮች ነበርን” እያሉ መጽሐፍ እየጻፉ ነው፡፡ የጥፋት
ኃላፊነቱንም በሌሎች ላይ እየደፈደፉ ነው፡፡ ቢያንስ ብዙዎቹ በድንቁርና ለጨፈጨፉዋቸው ዜጐች ኃላፊነቱን ለመውሰድ
አልተዘጋጁም፡፡ እውነቱን ለመናገር እኔም ባለፈው ጊዜ በጻፍኩት መጽሐፌ ላይ የነገሮችን ሚዛን ለመጠበቅ በጣም
አስቸግሮኝ እንደነበረ አስታውሳለሁ። ለአብነት፤ የቀድሞ የመኢሶን ጓዶቼ ከኢሕአፓ ጋር አመሳሰልከን የሚል ቅሬታ
እንዳላቸው ነግረውኛል። ታሪክ ፀሐፊዎች ስለ አንድ ድርጊት እርግጠኛ ሆነው መጻፍ ያለባቸው የድርጊቱ ተሳታፊዎች
ሲሞቱ ነው የሚሉት የገባኝ አሁን ነው፡፡
አንድ ቀን ከቀድሞ የሕወሓት አመራር አባል ጋር ስለዚህ ጉዳይ
አንስተን ስናወራ ለተሠሩት ስህተቶች የኃላፊነት ደረጃ ለድርጅቶች ስጥ ብትለኝ ደርግ አንደኛ፣ ሕወሓት ሁለተኛ፣
ኢሕአፓ ያንተ ድርጅት ስለሆነ ነው ወንጀሉን ያስነሳከው” አለኝ፡፡ የቀልድም ይሁን፤ የምር አስተያየቱ ቢያናድደኝም፣
ገርሞኛል፡፡
በእኛ ትውልድ ስላየናቸው የአፄ ኃይለሥላሴ፣ የደርግና የኢሕአዴግ መንግሥታት የትኛውን
ትመርጣለህ ቢባል፣ የየዘመኑ ተጠቃሚ ያለምንም ጭንቀት እራሱ ተጠቃሚ የነበረበትን ሊመርጥ እንደሚችል ይገመታል።
በሕዝብ ደረጃ ሲታሰብ ግን፤ እንደጊዜው ሁኔታ ሊታይ እንደሚችል አያጠራጥርም፡፡ ከቀይ ሽብር በኋላ፣ አብዮቱ የደርግ
መንግሥት ጭፍጨፋ እየመረረው ሲመጣ ብዙ ወጣቶች፤ “ተፈሪ ማረኝ፣ የደርጉ ነገር ምንም አላማረኝ” ሲሉ መስማቴን
አስታውሳለሁ፡፡ ይህ ምርጫ እንደየ ማህበረሰቡም ሊለያይ ይችላል፡፡ ኦሮሚያና ደቡብ ውስጥ፣ ከዝንጀሮ ቆንጆ…ቢሆንም
የደርግ መንግሥት ሊመረጥ ይችላል፡፡ የኢትዮጵያ ተማሪዎች ንቅናቄ ውለታ ይሁን፣ የደርግ መንግሥት፣ የመሬት አዋጅ
በእነዚህ አካባቢዎች እስከ ዛሬም ድረስ እጅግ በጣም ሰፊ ድጋፍ አለው፡፡
የቡዳ ፖለቲካችንን ከሁሉም በላይ
አስቸጋሪ የሚያደርገው ሁሌም ጥፋተኞች እኛ ሳንሆን እነዛ ናቸው ብለን ስለምንደርቅ ነው፡፡ እዚህ ላይ ፈረንጆች
የሚበልጡን በሁለት መሠረታዊ ጉዳዮች ነው፡፡ አንደኛው፣ ለነሱ ዛሬ ለደረሱበት ደረጃ ጥፋት መቀበልን እንደሞት
አያዩትም፡፡ ሁለተኛ፤ ሥልጣንን የሙጥኝ በማለት አጥፍቶ መጥፋትን ከባህላቸው አስወግደዋል ወይም የኋላቀሮች
አስተሳሰብ አድርገውታል፡፡ ቢያንስ ከሂትለር ወዲህ የአብዛኞቹ ጉዞ በዚህ አቅጣጫ ነው፡፡ ሦስተኛው፣ ፖለቲካቸው
ሰጥቶ መቀበል ላይ የተመሠረተ ነው፡፡ ሁሉንም አግኝ ወይንም ሁሉንም እጣ (Zero –sum-game) የሚባለውን
ፖለቲካ ከልብ እየተው መጥተዋል፡፡ ይበልጥ ደግሞ ከሥልጣን በኋላ፣ ጥሩ ኑሮ መኖርም፣ ክብር ማግኘትም እንደሚቻል
አውቀዋል፡፡ እንደውም ከሥልጣን በኋላ ያለጭንቀት የተደላደለ ኑሮ መኖር እንደሚቻል ያውቃሉ፡፡ ኦባማ በአፍሪካ
ኅብረት ንግግሩ የአፍሪካ መሪዎችን ለማስተማር የሞከረው ይህንኑ ነው፡፡ ትምህርቱ ገብቶት ይሁን፤ በተለመደው
የኢሕአዴግ ባለሥልጣናት የማስመሰል ፖለቲካ፤ የኢትዮጵያው ጠቅላይ ሚኒስትርም ሲያጨበጭብ አይቻለሁ፡፡ …
0 comments:
Post a Comment