እነ ብርሃኑ የእምነት ክህደት ቃላቸውን ሰጡ
‹‹ድርጊቱን ፈጽመናል፣ ጥፋተኞች ግን አይደለንም››
በነገረ ኢትዮጵያ ሪፖርተር
ከግራ ወደ ቀኝ – ፍቅረማርያም አስማማው፣ ብርሃኑ ተክለያሬድ እና እየሩሳሌም ተስፋው
የኢትዮ-ኤርትራ ድንበርን በማቋረጥ ኤርትራ ከሚገኘው ግንቦት ሰባት የተባለ በተወካዮች ምክር ቤት ሽብርተኛ ተብሎ
ከተፈረጀ የሽብር ቡድን ጋር ለመቀላቀል ሲጓዙ ድንበር አካባቢ ማይካድራ ላይ እንደተያዙ በመግለጽ በመንግስት የሽብር
ክስ የተመሰረተባቸው እነ ብርሃኑ ተክለያሬድ የእምነት ክህደት ቃላቸውን ሰጡ፡፡
ዛሬ ነሐሴ 11/2007
ዓ.ም በፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ 14ኛ ወንጀል ችሎት የቀረቡት ብርሃኑ ተክለያሬድ፣ እየሩሳሌም ተስፋው፣
ፍቅረማርያም አስማማውና ደሴ ካህሳይ ‹‹በክሱ ላይ የተመለከተውን የወንጀል ድርጊት ፈጽመዋል ወይስ አልፈጸሙም››
የሚል ጥያቄ ከፍርድ ቤቱ እየተነሳላቸው፣ በየተራ የእምነት ክህደት ቃላቸውን ሰጥተዋል፡፡ በዚህም አራቱም ተከሳሾች
ድርጊቱን እንደፈጸሙ በመግለጽ፣ ነገር ግን ጥፋተኛ አለመሆናቸውን አስረድተዋል፡፡
አንደኛ ተከሳሽ ብርሃኑ
ተክለያሬድ፣ ‹‹ሀገሬ በፋሽስት አምባገነኖች ተይዛ ዜጎች በጨቋኝ ስርዓት ውስጥ ስላሉ ሀገሬንና ህዝቤን ነጻ
ለማውጣት ወጣትነቴን ሰውቼ ለመታገል ግንቦት ሰባት ከሚባል ነጻ አውጭ ድርጅት ጋር ለመቀላቀል ወስኜ ወደዚያው
አቅንቻለሁ፡፡ ስለዚህ ድርጊቱን ፈጽሜያለሁ፣ የግንቦት ሰባት አባል ነኝ፡፡ ወንጀለኛ ግን አይደለሁም›› ሲል ቃሉን
ለፍርድ ቤቱ ሰጥቷል፡፡ ሁለተኛ ተከሳሽ እየሩሳሌም ተስፋው በበኩሏ፣ ‹‹ድርጊቱን ፈጽሜያለሁ፤ ነገር ግን ጥፋተኛ
አይደለሁም›› ብላለች፡፡
ሦስተኛ ተከሳሽ ፍቅረማርያም አስማማው ደግሞ፣ ‹‹ህገ-መንግስቱን አምኜ በሰላማዊ
ትግል ውስጥ ስሳተፍ የደረሰብኝን አውቃለሁ፡፡ ሰላማዊ ትግል እንደማያዋጣም ተረድቻለሁ፡፡ በዚህ ሰዓት ኢትዮጵያ
ውስጥ ዴሞክራሲን ለመገንባት የሚያስፈልገው የነጻነት ትግል ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ ግንቦት ሰባት ነጻ አውጭን
ለመቀላቀል ስጓዝ ማይካድራ ላይ ተይዣለሁ፡፡ ስለዚህ ድርጊቱን ፈጽሜያለሁ፤ ጥፋተኛ ግን አይደለሁም›› ብሏል
ለችሎቱ፡፡
አራተኛ ተከሳሽ ደሴ ካህሳይ በበኩሉ፣ ‹‹አርሶ አደር ነኝ፣ ሰሊጥ አመርታለሁ፡፡ ነገር ግን
ያመረትሁትን ሰሊጥ የኢህአዴግ ወታደሮች ይዘርፉኛል፤ መስራት አልቻልኩም፡፡ በዚህ ምክንያት ሌላ ስራ መስራት
ስላልቻልኩ የኢትዮጵያ አርበኞች ግንባርን ተቀላቅያለሁ፡፡ ለዚህ ግን ጥፋተኛ አይደለሁም›› ሲል የእምነት ክህደት
ቃሉን ሰጥቷል፡፡
ፍርድ ቤቱ የተከሳሾችን ቃል ካዳመጠ በኋላ የአቃቤ ህግን አስተያየት የጠየቀ ሲሆን፣ አቃቤ
ህግ ተከሳሾች ጥፋተኝነታቸውን ስላላመኑ ማስረጃ እንዲያቀርብና እንዲያሰማ እንዲፈቀድለት ጠይቋል፡፡ ስለሆነም ፍርድ
ቤቱ የአቃቤ ህግ ማስረጃን ለመስማት ለነሐሴ 22/2007 ዓ.ም ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡
0 comments:
Post a Comment