Wednesday, 5 August 2015

የቃሊቲ ማረሚያ ቤት ለ3ኛ ጊዜ አቶ አንዳርጋቸውን አላቀረበም

‹‹ቤተሰቦቼ አሸባሪ ተብለው ቤት የሚያከራያቸው አጥተዋል፤ ልጆቼ በረንዳ ላይ ወድቀዋል፤ ቤተሰባችን ተበትኗል››
ም/ኢንስፔክተር ሙልዬ ማናዬ ረታ (7ኛ ተከሳሽ)

በነገረ ኢትዮጵያ ሪፖርተር
በዘመነ ካሴ የክስ መዝገብ ከ2ኛ እስከ 5ኛ ለተከሰሱት አቶ አሸናፊ አካሉ (2ኛ ተከሳሽ)፣ አቶ ደናሁን ቤዛ (3ኛ ተከሳሽ)፣ አቶ ምንዳዬ ጥላሁን (4ኛ ተከሳሽ) እና አቶ አንሙት የኔዋስ (5ኛ ተከሳሽ) ዋስ እንዲሆኑ ለዛሬ ሀምሌ 29/2007 ዓ.ም ፍርድ ቤት እንዲያቀርብ የፍርድ ቤት ትዕዛዝ የደረሰው የቃሊቲ ማረሚያ ቤት አቶ አንዳርጋቸውን ሳያቀርብ ቀርቷል፡፡

ተከሳሾቹ አቶ አንዳርጋቸው ፅጌን በመከላከያ ምስክርነት እንዲቀርቡላቸው የጠየቁት የፌደራል አቃቤ ህግ ‹‹ከአንዳርጋቸው ፅጌና ፋሲል የኔዓለም እንዲሁም ከሌሎቹ የአሸባሪው ድርጅት አመራሮች ጋር በአካልና በሌሎች የመገናኛ ዘዴዎች በመገናኘት ስለ ሽብር ተግባሩ አፈፃፀም በመግባባት፣ ኤርትራ ወደሚገኘው የግንቦት ሰባት ካምፕ ሄደው ስልጠና በመውሰድ፣ ተልዕኮ ተቀብሎ ወደ ሀገር ውስት በመመለስ፣ ....›› የሚል ክስ ስለመሰረተባቸው ነው፡፡

የልደታ ፍርድ ቤት አቶ አንዳርጋቸው ፅጌ በዘመነ ካሴ የክስ መዝገብ ከ2ኛ እስከ 5ኛ ለሚገኙት ተከሳሾች ሀምሌ 13/2007 ዓ.ም ልደታ ፍርድ ቤት ቀርበው ምስክርነት እንዲሰጡ ወስኖ የነበር ቢሆንም ለቃሊቲ ማረሚያ ቤት የሚላከው ማዘዢያ እንደዘገየ በመግለጽ ለሀምሌ 15/2007 ዓ.ም እንዲቀርቡ ቀጠሮ መስጠቱ ይታወቃል፡፡ ሆኖም አቶ አንዳርጋቸው ሀምሌ 15/2007 ዓ.ም ያልቀረቡ ሲሆን ማረሚያ ቤቱ ትዕዛዙ ለቃሊቲ ማረሚያ ቤት መጻፍ ሲገባም ለአዲስ አበባ ማረሚያ ቤት ተብሎ ስተለጻፈ ማቅረብ እንዳልቻለ ገልጾ ነበር፡፡ ፍርድ ቤቱም ማዘዢያው ለቃሊቲ ማረሚያ ቤት ተብሎ እንዲፃፍ አዝዞ ለሶስተኛ ጊዜ ማረሚያ ቤቱ ለሀምሌ 29/2007 ዓ.ም አቶ አንዳርጋቸውን እንዲያቀርብ ትዕዛዝ ሰጥቶ ነበር፡፡ ይሁንና በዛሬው ዕለትም የቃሊቲ ማረሚያ ቤት አቶ አንዳርጋቸውን ሳያቀርብ ቀርቷል፡፡ ፍርድ ቤቱ አቶ አንዳርጋቸው ምስክር እንዲሆኑ ከወሰነ ጊዜ ጀምሮ ይቀርባሉ ተብለው ሳይቀርቡ ሲቀሩ የዛሬው ለሶስተኛ ጊዜ ነው፡፡

በዛሬው ዕለት የልደታ ፍርድ ቤት 19ኛ ወንጀል ችሎት የቃሊቲ ማረሚያ ቤት አቶ አንዳርጋቸውን ለምን እንዳላቀረበ እንዲያብራራ፣ እንዲሁም በዛው ቀን ለምስክርነት እንዲያቀርብ ሲል ለጥቅምት 12/2008 ዓ.ም ለአራተኛ ጊዜ ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡ ተከሳሾቹ አጭር ቀጠሮ ተሰጥቶ የቃሊቲ ማረሚያ ቤት አቶ አንዳርጋቸውን ለምን እንዳላቀረበ ማብራሪያ እንዲሰጥ ቢጠይቁም ፍርድ ቤቱ በሌሎች መዝገቦች የሚሰሙ ምስክሮች ስላሉና ከነሀሴ 15/2007 ዓ.ም በኋላ ፍርድ ቤት ስለሚዘጋ በሚል አቤቱታቸውን አልተቀበለውም፡፡
በሌላ በኩል በማረሚያ ቤትና በፍርድ ቤቱ ችግር አቶ አንዳርጋቸውን ለምስክርነት ማቅረብ ባለመቻሉ እየተጉላሉ መሆናቸውን ተከሳሾቹ አቤቱታ አቅርበዋል፡፡ 7ኛ ተከሳሽ ም/ኢንስፔክተር ሙልዬ ማናዬ ‹‹የአዲስ አበባ ማረሚያ ቤት በመባሉ በሚል ተልካሻ ምክንያት ለምን እንጉላላለን? እኛ ፍትህ ፈላጊ ነን፡፡ ቃሊቲና ቂሊንጦ በአንድ ደቂቃ የስልክ ግንኙነት መገናኘት እየቻሉ በቀጠሮ እየተጉላላን ነው›› ብለዋል፡፡

ተከሳሹ አክለውም ‹‹እኔ የመከላከያ ምስክሬን ያቀረብኩት የዛሬ አመት ነው፡፡ ለእኔ ብለው ቤተሰቦቼ በሬያቸውን ሸጠዋል፡፡ ግን አሁንም ድረስ እየተጉላላሁ ነው፡፡ ቤተሰቦቼ አሸባሪዎች ናቸው ተብለው ቤት የሚያከራያቸው አጥተዋል፡፡ ልጆቼ በረንዳ ላይ ወድቀዋል፡፡ ቤተሰባችን ተፈትቷል፡፡ ምስክሩን ማቅረብ ካልቻሉ ለምን ክሱን ውድቅ አታደርጉትም?›› ሲሉ የፍርድ ሂደቱ በመጓተቱ እየደረሰባቸው የሚገኘውን በደል ገልጸዋል፡፡

የፌደራል አቃቤ ህግ ‹‹የአማራ ክልል ወጣቶች ፕሬዝደንት ሆኖ ባለበት በሐምሌ ወር 2004 ዓ.ም በኬንያ አድርጎ ከሀገር ከወጣ በኋላ የአሸባሪውን የግንቦት 7 ልዩ ኃይል (Popular Force) ታጥቆ እየተንቀሳቀሰ የሚገኝ›› በሚል በሌለበት ክስ የመሰረተበት የዠመነ ካሴ ክስ መዝገብ 10 ተከሳሾቹ የተከሰሱ ሲሆን 10ኛ ተከሳሽ ወ/ሮ ሙሉ ሲሳይ መቆያ የአቃቤ ህግ ምስክር ሆና ግንቦት 19/2006 ዓ.ም በነፃ ተለቃለች፡፡

0 comments:

Post a Comment