Monday 3 August 2015

በእነ አቡበክር አህመድ የክስ መዝገብ የተጠቀሱ 18 ተከሳሾች ከ22 እስ ከ 7 አመት ፈረደባቸው


22 አመት የተቀጡት ፍርድ ቤቱ በሽብር ወንጀሉ ከፍተኛ ሚና ነበራቸው ያላቸው አቡበክር አህመድ፣ አህመዲን ጀበል፣ ያሲን ኑሩ እና ከሚል ሸምሱ ናቸው ። ችሎቱ በመዝገቡ የተጠቀሱ 5ኛ፣ 7ኛ፣ 8ኛ፣ 11ኛ እና 15ኛ ተከሳሾችን፥ በድሩ ሁሴን፣ ሳቢር ይርጉ፣ መሃመድ አባተ፣ አቡበክር አለሙ እና ሙኒር ሁሴንን እያንዳንዳቸውን በ18 አመት ጽኑ እስራት ቀጥቷቸዋል ።

ሼህ መከተ ሙሄ፣ አህመድ ሙስጠፋ፣ ሼህ ሰኢድ አሊ፣ ሙባረክ አደም እና ካሊድ ኢብራሂም የ15 አመት ጽኑ እስራት ተወስኖባቸዋል ። እንዲሁም ሙራድ ሽኩር፣ ኑሩ ቱርኪ፣ ሼህ ባህሩ ዑመር እና የሱፍ ጌታቸውን በ7 አመት ጽኑ እስራት ቀጥቷቸዋል ። ተከሳሾችም ይሁን ከሳሽ አቃቤ ህግ የቅጣት አስተያየት እንዲያቀርቡ የ10 ቀን ጊዜ በችሎቱ ተሰጥቷቸው የነበረ ሲሆን ፥ አቃቤ ህግ ቀድሞ ማቅረቡን ችሎቱ አትቷል ።

ተከሳሾች የአቃቤ ህግን የቅጣት አስተያየት ካላየን አናቀርብም ማለታቸውን ተከትሎ ችሎቱ የአቃቤ ህግ የቅጣት አስተያየት እንዲደርሳቸው ትዕዛዝ አስተላልፎ ነበር ።

ይሁን እንጂ ከተሰጣቸው የመጀመሪያው 10 ቀን ሌላ ተጨማሪ ቀን ቢሰጣቸውም የቅጣት ማቅለያ ሊያቀርቡ አልቻሉም ።
ፍርድ ቤቱ ቅጣቱን ያስተላለፈው አቃቤ ህግ ተከሳሾች ወንጀሉን የፈጸሙት በስምምነትና በአንድነት ነው የሚለውን የቅጣት ማክበጃ ተቀብሎ ነው ።

ችሎቱ ከእስራት ቅጣት በተጨማሪ ተከሳሾች ይህ ውሳኔ ከፀናበት እለት ጀምሮ ለአምስት አመታት እንዳይመርጡ ፣ እናዳይመረጡ ፣ በየትኛውም ቦታ ዋስም ምስክርም እንዳይሆኑ በአጠቃላይ ከማህበራዊ መብታቸው አግዷል ።

የፍርዱን ሂደት ለመከታተል፣ ለመሪዎቻቸው ያላቸውን አክብሮት ለማሳየት እና አጋርነታቸውን ለመግለጽ ከወትሮው በተለየ መልኩ የሙስሊሙ ማህበረሰብ አባላት በርከት ብለው በፍርድ ቤቱ ተገኝተዋል።

ኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች “ከወያኔ የካንጋሮ ፍርድ ቤት ከዚህ የተለየ ነገር አልጠበቅንም ነበር” ብለዋል።
“ከዝንብ ማር አንጠብቅም” እያሉ ያሉት ኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች ወደፊትም በኢትዮጵያ የሐይማኖት ነጻነት እና እውነተኛ ዲሞክራሲ እስኪመጣ ድረስ ትግላችንን አናቆምም ብለዋል።

0 comments:

Post a Comment