Monday, 28 April 2014

አገር እንዲህ ኾናም አትቀርም

በጽዮን ግርማ

Mimi Sebhatu
Mimi Sebhatu
ዘወትር እንደምታደርገው ሁሉ በምታዝበት ሬዲዮ ጣቢያ ጓደኞቿን ሰብስባ ወደ ስቱዲዮ የገባችው ሚሚ ስብሃቱ ከትናንት በስቲያ ጀምሮ ስለታሠሩት ሁለት ጋዜጠኞችና ሰባት ጦማሪዎች ከፖሊስ አገኘኹት ያለችውን መረጃ ጠቅሳ ስታወራ ነበር፡፡ ኢትዮጵያን ለማተራመስ ከሚሠራው አርቲክል ዐሥራ ዘጠኝ ከሚባል ድርጅት ጋር ሲሠሩ ነበር፣ ትልልቅ ሆቴል እየተገናኙ ይወያዩ ነበር፣ ኢትዮጵያ ውስጥ ሰዎችን ያደራጁ ነበር፣ ከሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅትና ከአምነስቲ እንዲሁም ከግብጽና ከኤርትራ ገንዘብ ይቀበሉ ነበር፤  የሚሉ ውርጅብኞችን በማውረድ እነርሱን የኢትዮጵያ ጠላት እራሷን ደግሞ የኢትዮጵያ ወዳጅ አድርጋ በመሳል ውንጀላዋን ስታዥጎደጉደው ነበር፡፡
በወሬዋ መካከልም ‹‹ይህ ሞያ ሠላሣ ዓመት ያገለገልኩበት ነው፡፡ ታአማኒነት ያለኝ ጋዜጠኛ ስለመኾኔ ደግሞ የኢትዮጵያ ሕዝብ ምስክር ይኾነኛል›› ስትል ነበር፡፡ እንዳለችው ሠላሳ ዓመት በማገልገል ተአማኒነት የሚገኝ ቢኾንማ ዛሬ ጋዜጠኝነት በዚህ ደረጃ አይዘቅጥም ነበር፡፡ ሚሚ ዛሬ እንኳን ከፖሊስ አገኘኹት ያለችውን መረጃ ዜና አድርጋ ለማቅረብ አልፈለችገም፡፡ ከእርሷ በዕድሜ በጣም የሚያንሱትን በአስተሳሰብ ግን በእጅጉ የሚልቁትን ወጣቶች አገር ሊያተራምሱ ስትል ወቀሰቻቸው፡፡ ኢትዮጵያ እኮ የአንድ ግለሰብ መኖሪያ አይደለችም፡፡ የሁላችንም ናት፣ ሁላችንም ባለመብቶች ነን፡፡ እነዚህ ወጣቶች እዚሁ አገር ቤተሰብ አላቸው አገሪቱ ስትተራመስ ቤተሰቦቻቸው ይተራመሳሉ ቢያንስ እርሱ ያሳስባቸዋል፡፡
በአመለካከት እና በአስተሳሰብ ስለተለዩ አገር ያተራምሳሉ ማለት ትንሽ እንኳን ጉሮሮን ያዝ አያደርግም?
ተስፋለም በዕድሜም በጋዜጠኝነት ልምድም በቁጥር ከእርሷ በእጅጉ ያንሳል፡፡ በአስተሳሰብ፣በጠንካራ ሞራሉ፣ለሞያው በሚሰጠው ትልቅ ክብር ደግሞ ከእርሷ በእጅጉ ይለያልም ይልቃልም፡፡ እርሱ የሞያው ሥነምግባር በሚፈቅድለት ልክ ‹‹ጋዜጠኛ›› ነው፡፡ እርሱ የተቀደደ ጫማ አድርጎ ይሄዳታል እንጂ ለገንዘብ ሲል እስኪሪፕቶውን አያንሻፍፍም፡፡ እንደርሱ ቢኾንማ በጣም ቀላል ነበረለት እኮ እርሷ እንዳለችው ምን አርቲክል 19 ድረስ አስኬደው እርሷ የምታደርገውን ከእርሷ በላይ ማድረግ ይችል ነበርኮ ያውም ከእርሷ በተሻለ፡፡ እርሱ ግን የእዚህ ሰው አይደለም የእርሱ ፍላጎትና ጥረት ኢትዮጵያ ውስጥ ጋዜጠኝነት በራሱ ኃይል እንዲቆም የሚጥር፣ለሞያው ሥነ ምግባርና ክብር አንገቱን የሚሰጥ በማንኛውም መልኩ ትክክለኛ ዘገባ ለማቅረብ የሚጥር ጋዜጠኛ ነው፡፡ ለነገሩ ሚሚ ጋዜጠኞችን ለመወንጀል ስትሽቀዳደም ዛሬ የመጀመሪያዋ አይደለም፡፡ እኔም ከዛሬ በስተቀር ለዚች ሴት ቦታ ሰጥቼያት አላውቅም፡፡
ከእሥረኞቹ አንዱ ማንነቱን አበጥሬ የማውቀው ጋዜጠኛ ተስፋለም ነውና በእንደርሷ ያለች ጋዜጠኛ ተብዬ ‹‹ጋዜጠኛው ተስፋለም›› ሲወነጀል እየሰማኹ ግን መቻል አቃተኝ፡፡ እናም ወ/ሮ ሚሚን እንዲህ ልላት ፈለኩ፤ ‹‹ይቺ አገር የእሷና የጓደኞቿ ብቻ አይደለችም፣ ይቺ አገር እንዲህ ኾናም አትቀርም፤ምናልባት ነገ እርሷ በተስፋለም ቦታ እርሱ ደግሞ በእሷ ቦታ ይኾኑ ይኾናል፤   ዕድሜ ይስጣት እንጂ ያኔ ተስፋለም የጋዜጠኝነትን ሀሁ ጥሩ አድርጎ ያስተምራታል›› አበቃሁ!

Zone 9

0 comments:

Post a Comment