Saturday, 29 March 2014

የክህደት ኣቀበት

አብረሃ ደስታ


እውነቱን ለመናገር በኢትዮጵያ ፖለቲካ ምክንያት እንደሰሞኑን በግኜ የማውቅ ኣይመስለኝም። ኣቤት ክህደታችን! እንዴት ተክነንበታልሳ ወገኖች! ረጋ ብላችሁ በጥሞና ኣንድታነቡኝ ብርታቱን ይስጣችሁ፥
1• በዛሬይቱ ኢትዮጵያችን ነባራዊ ሁኔታ ብሄር ማለት ምን ማለት እንደሆነ በትክክል የሚነግራችሁ ሰው ኣታገኙም። የብሄር ፖለቲካ ኣቀንቃኞቹ ራሳቸው የሚግባቡበት ወጥ የሆነ የብሄር ትርጉም እንኳን የላቸውም። ብሄር ለኣንዳንዱ በቋንቋ ነው የሚገለፀው፤ ለሌላው በዘርና ትውልድ ሃረግ ነው የሚገለፀው፤ ደግሞ ለሌላው በጂኦግራፊ ነው የሚገለፀው፤ የምርጫ ጉዳይ እንጂ ሌላ ምንም መስፈርት ኣይጠይቅም የሚሉም ኣሉ። ከየትም ይወለድ የትም፤ ማንኛውንም ቋንቋ ይናግር፤ የትም ይኑር ብሄሩ «የመረጠው» የህይወት ዘይቤ ነው የሚሉ የብሄር ፖለቲካ ኣራማጆችም ኣሉ። (ወደ ዝርዝሩ ኣልገባም፤ ጊዜና ቦታ ይፈልጋልና፤ ሆኖም በትርጉም ደረጃ እንኳን እንደማይግባቡ ኣስምረንበት እንለፍ።)
2• በብሄር ትርጉም የማይግባባ ፖለቲከኛ የብሄር ፖለቲካ ሲያራምድ ማየት በጣም የሚደንቅ ምፀት ነው። የብሄርን ትርጉም በቅጡ ሳናውቅ፤ ምናባዊ ብሄሮች ፈጠረን ስም ሰጠናቸው። ትግራይ፡ ኦሮሞ፡ ኣማራ፡ ሶማሌ፡ •••።
እስቲ ቆም እንበል እዚች ጋ። 30 ሰኮንድ።
ትግራይ የሚባል ብሄር በዛሬይቱ ኢትዮጵያችን ውስጥ ኣለ? ኣማራ የሚባል ብሄር ኣለ? ኦሮሞ የሚባል ብሄር ኣለ? •••? እስኪ ረጋ ብለን እናስበው ትግራዋይ የምንለው ማንን ነው? ኣማራ የምንለው ማንን ነው? ኦሮሞ የምንለው ማንን ነው?
በደንብ የማውቃትን ትግራይን እንደኣብነት ብንወስድ፤ የራያ ገበሬ ከሽረ/እንዳስላሴ ገበሬ በጣም በትንሹ ከሚቀራረብ ቋንቋቸው ውጪ በባህል፡ በዘር ሃረጋቸውና በታሪካቸው የማይገናኙ ፍፁም የተለያየ የየራሳቸው ኣመጣጥ ያላቸው ማህበረሰቦች ናቸው። ቋንቋውም ቢሆን ከሁለቱም ኣካባቢ ራንደምሊ ኣንዳንድ ገበሬዎችን ወስደን በ”ትግርኛ” ቋንቋቸው እንዲወያዩ ቢደረግ ምናልባትም ከግማሽ በላይ ላይግባቡ ይችላሉ። በብሄርተኞች ኣይን ግን ኣንድ ናቸው፤ ትግራዋይ። እዚህ ላይ ልብ ማለት ያለብን ‘ኣንድ ናቸው’ ወይም ‘ትግራዋይ ናቸው’ መባላቸው ኣይደለም ችግሩ፤ ይህ ‘ኣንድነታቸው/ትግራዋይነታቸው’ ከሌላው የሚለያቸው “ልዩ ማነንታቸው/Identity” ነው መባሉ ነው ዋንኛ ችግሩ።
ኣማራውም በዚህ መልኩ ነው ኣማራ የተባለው። ኦሮሞውም በዚህ መልኩ ነው ኦሮሞ የተባለው። በራያና በሽረ ገበሬዎች ያለው ልዩነት እንዳለ ሆኖ “ኣንድ/ትግራዋይ ናቸው” ከተባለ፤ በወሎና በጎጃም ገበሬዎች ያለው ልዩነት እንዳለ ሆኖ “ኣንድ/ኣማራ” ናቸው ከተባለ፤ በሃረር በባሌና በወለጋ ገበሬዎች መሃከል ያለው ልዩነት እንዳለ ሆኖ “ኣንድ/ኦሮሞ” ናቸው ከተባለ፤ ••• ወዘተ፤ በትግራዋይ፡ ኦሮሞ፡ ኣማራና ሌሎቹም “ብሄሮች” ያለው ልዩነት እንዳለ ሆኖ “ኣንድ ብሄር/ ብሄረ-ኢትዮጵያዊ” የማይባሉበት ምክንያት ምንድን ነው??! የብሄር ፖለቲከኛው/ዋ መልስ ኣለህ/ሽ?
3• ከላይ ያነሳሁት ጥያቄ ሎጂካሊ ትክክል ሆኖ፤ ለብዙዎቻችን ስሜት የሚሰጥ እንዳልሆነ ኣስባለሁ። ምክንያቱም ለ23 ዓመታት የብሄር ፖለቲካ ተግተነዋልና፤ ትግራዋይ፡ ኣማራና ኦሮሞ የሚባሉ ብሄሮች እንደ «ነባራዊ እውነታ» ተቀብለናቸዋል። ከታች ያስቀመጥኩት የኣንድ ምሁር ንግግር እንደሚያሳየን፤ ብሄሩን በብሄር ደረጃ ብቻ ሳይሆን በካርታም ደረጃ ጭንቅላታችን ውስጥ ኣሰፍረነዋል። ትግራዋይ ማለት በትግራይ ክልል ያለ ኗሪ በሙሉ እንደሆነ ነው የሌላው ክልል ሰው የሚረዳው። በክልሉ ውስጥ በራሳቸው ማንነት ለመታወቅ የሚንገታገቱት ብቻ ናቸው ትግራዋይ ማለት እነሱን እንደማያካትት የሚያውቁት፤ በርግጥ በተቀዣበረ ስሜት ውስጥ ሆነን እኛም ያካባቢው ሰዎች በትግራዋይ ስም እየተደፈጠጡ ያሉ የራሳቸው የ”ብሄር” መለያ ያላቸው ማህበረሰቦች እንዳሉ እናውቃለን። ነገር ግን ፖለቲካዊም ይሁን ማህበራዊ ኣስተሳሰባችን የተቃኘው ትግራይ ኣንድ ናት በሚል ነው። ( “ትምክህተኞች ከኣንድ ፋብሪካ በወጣ ሳሙና ይመስሉናል” ተባሎ በኣንድ ወቅት ይሰራጭ የነበረ ፕሮፓጋንዳ፤ ከፕሮፓጋንዳነቱ ኣልፎ በፖሊሲ ደረጃ በክልሉ ውስጥ ያሉትን በሙሉ በመደፍጠጥ ኣንድ ለማድረግ እየተሞከረ ያ.ሁ.ነ.ያ. )
4. ታድያ በዚህ በተቀዣበረ ሁኔታ ውስጥ ሆነን ብሄርተኝነትን ኣለቅጥ ለጥጠን እያቀነቀንን ህዝባችን መሃል እየፈጠርን ያለነውን ሁኔታ ሙልጭ ኣድርጎ መካድ ሁሉ ይቃጣናል። ዛሬ ከላይ በተጠቀሰው መልኩ የቀረበልንን የብሄር ትርጉምና ፖለቲካ ተቀብለን፤ ልዩነታችንን እያሰፋን የምንኖረው ሁላችንም ነን። እያንዳንዳችን ኣስተሳሰባችን ሁሉ በዘር ተቃኝቷል ማለት ይቻላል። “diversified” የሆንን ህዝብ እንደሆመሆናችን መጠን ድሮም እኛና እነሱ የሚል ክፍተት የነበረን ቢሆንም፤ ኣሁን ግን ክፍተቱ ህገመንግስታዊ ይዘትንና ድንበርን ተላብሷል፤ politicized ሆኗል።
ድህነት፡ ስራ ኣጥነት፡ የፍትህ እጦት፡ ዝርፊያና በስልጣን መባለግ ባንሰራፋባት ምድር፤ ኣቅመ ቢሱ ህዝብ ብሶቱን የሚወጣበት ብቸኛ መንገድ “scapegoating” ነው። ለዚህ ደግሞ ምቹ ሁኔታ የዘር ፖለቲካችን ፈጥሮልናል። ኣንዱ ፀሃፊ እንዳለው ‘The people may have felt greater anger but no institutions existed … Their rage exploded from time to time but could not be sustained. Discontent was often directed against ´rival ethnic group´ rather than at the government; and the government was happy to leave his people fighting among themselves.’
5. ትላንት ባህርዳር ያየነው ሁኔታ ወዳጄ Tamrat Tam Rat በትክክል እንዳስቀመጠው “[It] is only the tip of the Iceberg”። በኣንድ ወቅት (ኣፈሩን ድንጋይ ያርግለትና!) ኣቶ መለስ በኢቲቪ ለህዝብ ‘የፕላዝማ ሌክቸር ‘ ሲያደርግ እንዲህ ብሎን ነበር፥ “በፌዴራሊዝም ስርዓት ክልሎች (ለኔ ብሄሮች ከሚለው ቃል ጋር synonymous ነው) መዋቀራቸው፤ የብሄር እኩለነት ከማረጋገጥ ኣልፎ የኢኮኖሚ ፖለቲካና ማህበረሰባዊ ፉክክር በክልሎች መካከል እንዲኖር በር ይከፍታል፤ ጤናማ ፉክክር ደግሞ ለልማት ኣስፈላጊ ግብኣት ነው”። ለ23 ዓመት ከሰርቶ ማሳያነት ያልዘለለው የፌደራሊዝም መዋቅር፡ ለጤናማ ፉክክር የሚያስፈልጉት ምቹ ሁኔታዎችን ሳያዘጋጁለትና የታሪክ ጠባሳ እየፈቀፈቁ ማፎካከር የመጨረሻው ውጤቱ ምን ሊሆን እንደሚችል ትላንት በባህርዳር ከታየው ክስተት መገመት ይቻላል።
6. ታድያ እውነታው ይህ ሆኖ ሳለ፤ በክህደትና ቅጥፈት የተሞላ ምክንያት ሲደረደርልን ስናይ ያሳዝናልም ያበግናልም። ጩኸቴን ቀሙኝ እንደሚባለው ኣገራዊ ብሂል፤ ዘረኝነትን ህገመንግስታዊ ኣድርገዉ ስልጣናቸውን ለማስጠበቅ ሌት ከቀን እየሰሩበት፤ ዘረኝነትን ኣወግዛለሁ እያሉ ቀድመውን ይጮኻሉ ጣታቸውን የሚቀስሩት በዘረኛ ኣመለካከት በክለው ያሳደጉት ትውልድ ላይ ሆነ።
ልብ ብላችሁ ከሆነ በተለይ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ብሄርተኝነትን ለማራገብ ባህርዳር ብዙ ነገር ተስርቶባታል። በከተማዋ የተከሰተው የባለፈው ኣመት ቃጠሎ፡ በኣደባባይ በተኩስ እሩምታ የተፈጁት ዜጎች፡ ኣማርኛ ተናጋሪ ዜጎች ከሌሎች ክልሎች መፈናቀላቸው፤ ዘንድሮም በክልሉ ኣመራር መሰደባቸው፤ ከሞረሽ ንቅናቄና የኢሳት ኣራጋቢነት ጋር ተደማምሮ በባህርዳር ይቅርና በሌላም ቦታ የኣማራ ብሄርተኝነትን ኣለቅጥ ኣራግቧል። የተከሰተው ነገር ቢያሳዝንም፤ ክስተቱ የሚገርም ኣይደለም፤ ሰው የዘራውን ነው የሚያጭደውና።
7. ኣንዳንድ ወገኖች ከቅንነት የመነጨ ሊሆን በሚችል መልኩ ጉዳዩን እግር ኳስ ከፈጠረው ስፖርታዊ ስሜታዊነት ጋር ኣያይዘውታል። እንደዚህ ዓይነት መግለጫ ለጊዜው ሁኔታዎችን ለማርገብ ኣስፈላጊ ቢሆንም ማዘናግያ እንዳይሆን ግን እሰጋለሁ። ዛሬ የክልል ቡድኖች ይቅርና የእግር ኳስ ክለቦች ሳይቀር የብሄር ቅርፅ ተላብሰዋል። እስኪ እውነቱን እንነጋገርና ትግርኛ ተናጋሪ ያልሆነ “ደደቢትን” የሚደግፍ ኣለ?? በቅርብ ጊዜ እዚህ ፌስቡክ ላይ ያየሁት ስሜት እንኳን “ደደቢት” የብሄር ፖለቲካ ማዳመቂያ ሲሆን ነበር። ማንዴላ ደቡብ ኣፍሪካውያንን ለማስተሳሰር የተጠቀመበት ቁልፍ ስፖርት እግር ኳስ ነበር። የኛ ኣለመታደል ደግሞ የብሄር ፖለቲካችንን የምናራግብባቸው በብሄር የሚጠሩና የታጠሩ ቡድኖችን እንቀፈቅፋለን።
እኔን እስከሚገባኝ ድረስ ኣብዛኛውን ጊዜ የእግር ኳስ ደጋፊ በስፖርታዊ ስሜት የሚጋጨው የቆየ ቁርሾ ሲኖረው ነው። ኣንድ የፌስቡክ ወዳጃችን በተሳሳተ ግንዛቤ ሊያንፀባርቅ እንደሞከረው፤ የኣርጀንቲናና የኢንግላንድ ብሄራዊ ቡድን ገና ሜዳ ሳይገቡ ብጥብጥ የሚጀምሩት በታሪካዊ ጠባሳቸው ምክንያት እንጂ ጊዜያዊ የስፖርት ስሜት የፈጠረው ሆኖ ኣይደለም። ትላንት የተመለከትነው ክስተትም የዘረኛ ፖሊሲያችን ውጤት መሆኑን ኣሌ የማይባል ነው። እንኳን ጎነታትለውኝ እንዲሁ ኣልቅሽ ኣልቕሽ ይለኛል እንዳለችው ኣንዷ ወዳጄ፤ ሰዎችን ፍፁም irrational የሚያደርግ የስፖርት ስሜት ተጨምሮበት ይቅርና እንዲሁም ዘረኛ ፖሊሲያችንና ስርዓት ዓልባው መንግስታችን እርስ በእርስ የሚያፋጁን ናቸው። ይህን መካድ ኣያስፈልግም፤ የሚያስፈልገው ዓይናችን እያየ ወደ ጥፋት ሳናመራ በፊት ቆም ብሎ ማሰብ ነው። ኣለበለዚያ ይህን የክህደት ኣቀበት የምንወጣው ኣይሆንም።
የምታምኑበትን ዛሬ ምረጡ፤ እኔና ቤቴ ግን ብሄረ-ኢትዮጵያን መርጠናል!
ዘረኝነትንና HIV/AIDSን በጋራ እንከላከል! Abraha Desta

0 comments:

Post a Comment