Monday, 8 June 2015

በሽብር የተከሰሱ የተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮች ላይ የአቃቤ-ህግ ምስክሮች መሰማት ተጀመረ

᎐ሚዲያዎች የምስክሮችን ቃል መዘገብ አይችሉም ተብሏል

በሽብርተኝነት ተከሰው ጉዳያቸው እየታየ የሚገኙት የሰማያዊ፣ የአንድነትና የአረና ፓርቲዎች አመራሮች ላይ የአቃቤ ህግ ምስክሮች መሰማት ተጀመረ፡፡ በእነ ዘላለም ወርቃገኘሁ የክስ መዝገብ የተካተቱት አብርሃ ደስታ፣ የሺዋስ አሰፋ፣ ሀብታሙ አያሌው፣ ዳንኤል ሺበሽና ሌሎች ስድስት ተከሳሾች ላይ አቃቤ ህግ አሉኝ ያላቸውን የሰው ማስረጃዎች ምስክርነት ዛሬ ሰኔ 01/07 ዓ.ም በከፍተኛው ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ማሰማት ጀምሯል፡፡

ምስክሮች መሰማት ከመጀመራቸው በፊት አከራካሪው ጉዳይ ምስክሮቹ በግልጽ ችሎት ይሰሙ ወይስ በዝግ ችሎት የሚለው ነበር፡፡ በዚህም አቃቤ ህግ የጸረ ሽብር አዋጁ አንቀጽ 32 ላይ የተመለከተውን የምስክሮች ጥበቃ ድንጋጌ በመጥቀስና ምስክሮቹ ዛቻና ማስፈራሪያ እንደደረሰባቸው በማውሳት ችሎቱ ምስክሮችን በዝግ እንዲሰማ ጠይቋል፡፡ ተከሳሾች በበኩላቸው ህገ መንግስቱን በመጥቀስ አቃቤ ህግ ያቀረበው ምክንያት በማስረጃ ያልተደገፈ ስለሆነ ችሎቱ ግልጽ እንዲሆን ተከራክረዋል፡፡

ሶስተኛ ተከሳሺ አቶ ዳንኤል ሽበሺ ‹‹አቃቤ ህግ እስከ ሞት በሚያደርስ ወንጀል ከሶናል፤ ይህን ጉዳይ በግልጽ መከታተል አለብን፡፡ እናንተ ብቻ ሳትሆኑ የኢትዮጵያ ህዝብም መፍረድ አለበት›› በማለት ችሎቱ ምስክሮችን በግልጽ እንዲሰማ አሳስቧል፡፡ አቶ ሀብታሙ አያሌው በበኩሉ ‹‹እኛ ዋስትና ተከልክለን በእስር ቤት ነን፤ የምስክሮች ስም ዝርዝር እንኳ አልተገለጸልንም፡፡ ታዲያ ማን ነው ምስክሮች ላይ ዛቻና ማስፈራሪያ የሚያደርስባቸው?›› ሲል አቃቤ ህግ ያቀረበው ምክንያት ተቀባይነት እንደሌለው በማስረዳት ችሎቱ ግልጽ እንዲሆን ጠይቋል፡፡

አቶ ሀብታሙ ሁሉንም ተከሳሾች በመወከል እንዳስረዳው ደግሞ ፍርድ ቤቱ ምስክሮችን በዝግ የሚሰማ ከሆነ ሁሉም የግፍ ፍርደኛ ሆነው ወደ እስር ቤት ለመመለስ ዝግጁ መሆናቸውን አስታውቀዋል፡፡ ‹‹ሁሉንም ወክየ ነው የምናገረው…በዝግ ችሎት ምስክሮችን የምትሰሙ ከሆነ ዛሬውኑ የግፍ ፍርደኞች ሆነን ወደ እስር ቤት ለመመለስ ዝግጁዎች ነን፤ ከዚህ በኋላም አንዳችንም ክርክር አናደርግም፡፡››
ፍርድ ቤቱ በአቃቤ ህግና በተከሳሾች መካከል የተነሳውን ክርክር መርምሮ ብይን የሰጠ ሲሆን በብይኑ መሰረትም የአቃቤ ህግ ምስክሮች በግልጽ ችሎት እንዲሰሙ ወስኗል፡፡ ሆኖም ግን ፍርድ ቤቱ የህትመትም ሆነ የኤሌክትሮኒክስ ሚዲያዎች የምስክሮችን ቃል ዝርዝር በተመለከተ መዘገብ እንደማይችሉ በብይኑ ላይ አመልክቷል፡፡

ዛሬ መሰማት የጀመረው የአቃቤ ህግ ምስክሮች እስከ ሰኔ 3/2007 ዓ.ም እንደሚቀጥል ታውቋል፡፡
በዚሁ መዝገብ ተከሳሾች መካከል አምስተኛ ተከሳሽ የሆነው የሰማያዊ ፓርቲ አመራር አቶ የሺዋስ አሰፋ ዳኞቹ ሲሰየሙና ስሙ ሲጠራ ከመቀመጫው ባለመነሳት በችሎቱ ላይ ተቃውሞውን ገልጹዋል፡፡ አቶ የሺዋስ ዳኞቹ ለምን እንደማይነሳ ሲጠይቁት በዝምታ ያለፋቸው ሲሆን፣ ተነስ ሲባልም ያለምንም ንግግር በተቀመጠበት ረግቷል፡፡

Friday, 5 June 2015

ሰማያዊ የG-7 መሪዎች በኢህአዴግ ላይ ጫና እንዲያደርጉ አሳሰበ

ሰማያዊ ፓርቲ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ነገ ግንቦት 29/2007 ዓ.ም በሚካሄደው የG-7 ስብሰባ መጋበዛቸውን ተከትሎ የወቅቱ የጉባኤው መሪ ለሆኑት የጀርመን ቻንስለር ለአንጌላ ሜርክል በፃፈው ደብዳቤ መሪዎቹ በኢህአዴግ ላይ ጫና እንዲያደርጉ አሳስቧል፡፡

አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ በስብሰባው ላይ መጋበዛቸው ቅር እንዳሰኘው የገለፀው ፓርቲው 24 አመት በስልጣን ላይ የቆየው የጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ፓርቲ አፋኝ ለመሆኑ የ2007 ዓ.ም ጠቅላላ ምርጫን በምሳሌነት ጠቅሷል፡፡ ምርጫው ልምድ ያላቸው የውጭ ታዛቢዎች ያልተገኙበትና የአፍሪካ ህብረት ታዛቢ ቡድንም ‹‹ነፃና ፍትሓዊ›› ነበር ለማለት ያልደፈረበት፣ ሰማያዊን ጨምሮ ሌሎች ተቃዋሚ ፓርቲዎች የተጭበረበረ መሆኑን ማረጋገጣቸውን በደብዳቤው አስታውሷል፡፡


ምርጫው ገዥው ፓርቲ 100% አሸነፍኩ ያለበት፣ ተቃዋሚዎች ላይ ከፍተኛ ጫናና እስር ከዚህም ሲያልፍ ለሞት የተዳረጉበት ነበር ያለው ሰማያዊ ፓርቲ ገለልተኛ ሲቪክ ማህበራት እንዳይታዘቡ መከልከላቸውን ገልጾአል፡፡ ጋዜጠኞችን፣ ጦማሪያንን፣ የሀይማኖት አባቶችንና ፖለቲከኞችን ለማጥቃት በወጣው የፀረ ሽብር ህግ ምክንያት ኢትዮጵያ በፖለቲካ እስረኞች ብዛት ከአፍሪካ ቀዳሚዋ መሆኗን ፓርቲው አስታውሳል፡፡

የጉባኤው አባላት ከኢትዮጵያ ጋር ባላቸው የንግድ ግንኙነትና በሚያበረክቱት እርዳታ ምክንያት በሰብአዊ መብት፣ ዴሞክራሲና ልማት ላይ አዎንታዊ አስተዋጽኦ ማድረግ የሚችሉ ቢሆንም የኃይለማርያም ደሳለኝ ፓርቲ የሚመራው መንግስት ለሰብአዊ መብት፣ ሀሳብን በነፃነት የመግለፅ መብት እየገደበና ተቃዋሚዎች ላይ ከፍተኛ በደል እያደረሰ ይገኛል ብሏል፡፡

ጉባኤው ሰብአዊ መብትና ዴሞክራዊያዊ መብትን ለልማትና የኢኮኖሚ ግንኙነት በቅድመ ሁኔታነት በመውሰድ ጫና ማድረግ ካልቻለ የኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ግንባታን እንደሚጎዳም ሰማያዊ ፓርቲ አሳስቧል፡፡ በመሆኑም ጉባኤው የፖለቲካ እስረኞች ያለ ቅድመ ሁኔታ እንዲፈቱ፣ ኢህአዴግ ተቃዋሚዎችን ማሰርና እንቅስቃሴያቸውን ከመገደብ እንዲቆጠብ እና አፋኝ አዋጆች ላይ ማሻሻያዎች እንዲደረግባቸው በኢህአዴግ መንግስት ላይ ጫና እንዲያደርግና ተገቢውን እርምጃ እንዲወስድ አሳስቧል፡፡



 

Thursday, 4 June 2015

ዳኛ ብርቱካን ማሙሸትን ፈታች – ፖሊስ በራሱ ውሳኔ አልፈታውም!

Mamushet_court_order_062015

አሳዛኝ ዜና – ተፈታ ታሠረ
(ለገሰ ወ/ሃና)
የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ) ፕሬዝደንት አቶ ማሙሸት አማረ ዛሬ ግንቦት 25/2007 ዓም ጠዋት 3:00 አካባቢ የተሠየመው ችሎት ማሙሸት አማረ ክሱ ተቋርጦ ይፈታ ብሎ ወስኗል።

በዚህ መሠረት የማስፈቻ ወረቀት ይዘን ታስሮበት የነበረው ቦሌ ፓሊስ መምሪያ ከጠዋት ጀምሮ ብንጠብቅም እስረኞች ሲመለሱ ማሙሸት አልተመለሰም የቦሌ ክ/ከተማ ፓሊስ ሀላፊዎች ማሙሸት ለምን እንዳልመጣ ስንጠይቃቸው ጠብቁ ሲሉን ቆይተው ከቀኑ 11:55 ላይ ማሙሸት አዲስ አበባ ፓሊስ ኮሚሽን መወሰዱን ነግረውናል እስካሁን ያለበትን ማወቅ አልቻልንም ነበር ፡፡


አሁን በደረሰን ዜና በሌላ ክስ ሳይከሰስ እንዳልቀረ የሚጠቁም ነገር እየሠማን ነው የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድረጅት ( መኢአድ) አባላት እና ቤተሰቦቹ ማሙሸት አማረ ታስሮበት የነበረው ቦሌ ፓሊስ መምሪያ ተሰባስበን የፕሬዝዳንታችንን መፈታት አስመልክቶ ደስታቸንን ለመግለጽ ተሰባስበን ነበር ይህንን ዜናም ለአለም ለማብሰር ዝግጅታችንን ጨርሰን ባለንበት ሰአት አስደንጋጭ ዜና ሰማን ማሙሸት አዲስ አበባ ፓሊስ ኮሚሽን እንደተወሰደ ነገሩን የኛ ሰዎችም በፍጥነት አዱስ አበባ ፓሊስ ኮሚሽን ሄደው ሲጠይቁ ማሙሸት እነሱ ጋረ መግባቱን አና አስረኛ መሆኑን በመግለፅ ምግብ እና ልብስ አምጡለት እንደተባሉ ገልፀዋል ሚያዝያ 12/2007 ዓም ድንጋይ አስወርውረሀል የሚል ሌላ ክሰ እንደተፈበረከለትም ጭምር ሠምተናል ታስሮበት የነበረው ክስ ሚያዚያ 14/2007 ዓም መንግስት የጠራውን ሰልፍ ወጣቶችን አደራጅተህ አመፅ እንዲነሳ አቀነባብረሀል የሚል ነበር ተከላከል ተብሎ መከላከያ አሰምቶ ነበር ከሰው ማስረጃ ሌላ በተከሰሰበት ቀንና ሰአት ልደታ ፍረድ ቤት ችሎት ላይ እንደነበረ ከፍረድ ቤት ያቀረበው ሠነድ አላፈናፍን ስላላቸው እንደገና ወደ 12/2007 አውርደው መክሰሳቸወ ነው ነገ ጠዋት ግንቦት 26/2007 ዓም በ3:00 አራዳ የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት እንደሚቀርብ ታውቋል ፡፡

የአለም ሀገራት ባሰፈኑት የህግና ፍትህ ስርአት ምዘና ኢትዮጵያ ከ102 የአለም ሀገራት 94ተኛ ደረጃ ተሰጥቷታል



ዎርልድ ጀስቲስ ፕሮጀክት የተባለው በአለም ላይ ፍትህና የህግ የበላይነት እንዲረጋገጥ እሰራለሁ የሚል ተቋም የ 102 የአለም ሀገራትን የፍትህና ህግ ስርአት ደረጃ ይፋ አድርጓል፡፡ ከተለያዩ ሀገራት ከ 100 ሺህ የማያንሱ ህዝቦችን መጠይቅ በማድረግ ጭምር የተጠናቀረው ይህ የተቋሙ ሪፖርት በዚህ ረገድ የኢትዮጵያችንንም ደረጃ ይፋ አድርጓል፡፡ …
የፍትህና ህግ የበላይነት ጉዳይ ብዙ ጊዜ የህግ ሰዎች ስራ ብቻ ተደርጎ ሊታይ ይችላል ነገር ግን ሁላችንንም በየእለቱ የሚያጋጥም የእለት ተእለት ጉዳይ ነው ያለው ተቋሙ የአለም መንግስታት ለዜጎቻቸው ያላቸው ግልጽነትና ተጠያቂነት የሚለካውም በዚሁ መስፈርት እንደሆነ ነው ያስቀመጠው፡፡

ሪፖርቱ በዋናነት የአለም መንግስታት ለዜጎቻቸው የቱን ያክል ግልጽነትና ተጠያቂነት አስፍነዋል የሚለውን ሲያስቀምጥም በአራት መስፈርቶች እንደመዘናቸው ነው የገለጸው፡፡ መንግስታቱ በተጻፉ ህጎችና መረጃዎች ነው ወይ ህዝባቸውን የሚያስተዳድሩት የሚለው ቀዳሚው መስፈርት ሲሆን፣ የዜጎች መረጃ የማግኘት መብት፣ የሲቪክ ማህበራት ተሳትፎ፣ እንዲሁም ቅሬታና አቤቱታ አፈታት በሚሉ አራት መመዘኛዎች ሀገራቱ መገምገማቸው ታውቋል፡፡

በዚህም መሰረት ከአጠቃላይ 102 ሀገራት ውስጥ ስዊድን፣ ኒውዚላንድና ኖርዌይ እጅግ ግልጽ የሆኑ የመንግስት ስርአት የሰፈነባቸው ተብለው የህግና ፍትህ ስርአታቸው ሲወደስ እንደ ማይናማር፣ ኡዝቤኪስታንና ዚምባብዌ ያሉ ሀገራት ደግሞ መንግስታቶቻቸው ዝግ በሆነና ፍትህና ህግ ባልሰፈነበት ሁኔታ ህዝባቸውን የሚያስተዳድሩ ተብለው በመጨረሻዎቹ እርከኖች ላይ ሰፍረዋል፡፡
የኢትዮጵያችንንም ደረጃ ያስቀመጠው ይህ ሪፖርት በአራቱም መስፈርቶች መልካም የሚባል ውጤት እንዳላገነች ነው ይፋ ያደረገው፡፡

በተጻፉ ህጎችና መንግስታዊ መረጃዎች 73ተኛ፣ በመረጃ ማግኘት መብት 79ኛ፣ በዜጎች ተሳትፎ 97ተኛ፣ እንዲሁም በቅሬታ አፈታት ስርአት 89ኛ ደረጃዎችን ያገኘችው ኢትዮጵያችን ይህ ደግሞ በዚህ ሪፖርት በአጠቃላይ ውጤት ከ 102 ሀገራት በ 94ኛ ደረጃ ላይ እንድትሰለፍ እንዳደረጋት ነው የተነገረው፡፡

Wednesday, 3 June 2015

መኢአድና ኢራፓ የምርጫውን ውጤት አንቀበልም አሉ



የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ) እና የኢትዮጵያ ራዕይ ፓርቲ (ኢራፓ) ግንቦት 16 ቀን 2007 ዓ.ም. የተካሄደውን ጠቅላላ ምርጫ ውጤት እንደማይቀበሉት፣ ግንቦት 25 ቀን 2007 ዓ.ም. በየጽሕፈት ቤታቸው በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ አስታወቁ፡፡

መኢአድ ቴዎድሮስ አደባባይ አካባቢ በሚገኘው ዋና ጽሕፈት ቤቱ ምርጫውን አስመልክቶ በፕሬዚዳንቱ አቶ አበባው መሐሪና በሌሎች የፓርቲው ከፍተኛ አመራሮች መግለጫ ሲሰጥ፣ በምርጫው ወቅት ገጠመኝ ያላቸውን ችግሮችና ጫናዎች ዘርዝሮ አቅርቧል፡፡

‹‹ባለፉት አራት ምርጫዎች በተከሰቱ ችግሮች ዙሪያ መፍትሔ አስቀምጦ ሙሉ በሙሉ ተሻሽሎ ይካሄዳል የሚል ዕምነት ቢኖረንም፣ ራሱን ሙሉ በሙሉ ወደ አምባገነንነት በቀየረው ገዥ ፓርቲ አፈና፣ ወከባ፣ እስራትና ግድያ የተነሳ ምርጫው ሳይሳካ ቀርቷል፤›› በማለት መኢአድ አስታውቋል፡፡

መኢአድ በምርጫው ዕለትና ከዚያ ቀደም ብሎ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ደረሰብኝ ያላቸውን ችግሮች ዘርዝሯል፡፡ ከአዲስ አበባ በስተቀር ኦሮሚያ፣ አማራና ደቡብ ክልሎችን ጨምሮ አባላቱ መታሰራቸውንና ታዛቢዎቹ ከምርጫ ጣቢያ መባረራቸውን ገልጿል፡፡
‹‹ምርጫው ነፃ፣ ፍትሐዊና፣ ሰላማዊ እንደሆነ ይገለጽ እንጂ በተግባር የታየው ግን የዚህ ተቃራኒ ነው፤›› ብሏል፡፡ ‹‹ሰው እየደበደቡ፣ እያሰሩ፣ እያንገላቱ፣ ከመኖሪያ እያፈናቀሉና የግድ ንብን ምረጡ ብለው ለማስፈራራታቸው ተጨባጭ መረጃ ባለበት ሁኔታ እንዴት ብሎ ነፃ፣ ፍትሐዊና ሰላማዊ ምርጫ እንደተካሄደ የሚያውቀው አፋኙ ሥርዓት ብቻ ነው፤›› በማለት መኢአድ በመግለጫው አስታውቋል፡፡

በምርጫው ምክንያት የታሰሩ የፓርቲ አባላትና ሌሎች የፖለቲካ እስረኞች በአስቸኳይ እንዲፈቱ ጠይቋል፡፡ ‹‹ምርጫው ታዋቂ የሆኑ ዓለም አቀፍ ታዛቢዎችና ከፖለቲካ ገለልተኛ የሆኑ የሲቪክ ማኅበራት ባልተገኙበት ኢሕአዴግ ባደራጃቸው የሲቪክ ማኅበራትና አባብሎ ወደ ታዛቢነት ያሰማራቸው የምርጫ ታዛቢዎች በተገኙበት የተካሄደ በመሆኑ፣ ይህንን የፖለቲካ ድራማ የተከናወነበት ምርጫ የማንቀበለው መሆኑን እናስታውቃለን፤›› በማለት መኢአድ መግለጫውን አጠቃሏል፡፡
የፓርቲውን የወደፊት አቅጣጫ በተመለከተ የፓርቲው ፕሬዚዳንት አቶ አበባው ሲገልጹም፣ ‹‹ከሌሎች ፓርቲዎች ጋር መክረን ዘክረን ወደፊት የምናሳውቀው ይሆናል፤›› ብለዋል፡፡

በተመሳሳይም በዋና ጽሕፈት ቤቱ መግለጫ የሰጠው የኢትዮጵያ ራዕይ ፓርቲ (ኢራፓ)፣ የዘንድሮው ምርጫ በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ መካሄዱን ያስረዱልኛል ያላቸውን የተለያዩ ክስተቶች በማንሳት አስረድቷል፡፡ በፓርቲው ፕሬዚዳንት አቶ ተሻለ ሰብሮና በሌሎች ኃላፊዎች በተሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ እንደተገለጸው፣ ለምርጫ ቦርድ ፓርቲው ያቀረባቸው ዕጩዎች ቁጥራቸው ያለምንም አሳማኝ ምክንያት ተቀንሶ ፓርቲው በተወሰኑለት ዕጩዎች ብቻ እንዲወዳደር መደረጉ ከፍተኛ ጫና ፈጥሮበታል፡፡
እንዲሁም በአማራ፣ በደቡብና በኦሮሚያ ክልሎችና በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በዕጩ ምዝገባ ወቅት፣ በቅስቀሳና በምርጫው ዕለት አጋጠሙኝ ያሏቸውን ችግሮች በባለ 6 ገጽ መግለጫው አስታውቋል፡፡ አብዛኛዎቹ ችግሮችም ከዕጩዎች አለመመዝገብ፣ ከአባላት መዋከብና መታሰር እንዲሁም የታዛቢዎች በሥፍራው ተገኝተው መታዘብ ከመከልከላቸው ጋር የሚያያዙ ናቸው፡፡
‹‹ጠጣር ግድፈቶች በተንፀባረቁበትና በተስተዋሉበት ሁኔታ የሕግ የበላይነት ተሟልቷል ተብሎ ከነጉድፉ መቀበል የፖለቲካ ቃር የሚያስይዝ ከመሆኑም በላይ፣ ከቀደምቶቹ ምርጫዎች 2002 እና 2005 (ማሟያና አካባቢያዊ) ባልተለየ መልኩ በአንድ ቅርጫት የተቀመጠ የቅድመ ምርጫ ሒደትና ውጤት በመሆኑ ፓርቲው አልተቀበለውም፤›› በማለት አስታውቋል፡፡

ቀጣይ አቅጣጫቸውን በተመለከተ ከሪፖርተር ለቀረበላቸውም ጥያቄ፣ ‹‹በትግል ደክመን ሳይሆን በመንግሥት ጫና ምክንያት መፈናፈን ባለመቻላችን ምንም እንኳን ዛሬ በዝረራ ብንወጣም፤ ዝረራው ግን ለነገው ቁጭት ጭሮብናል፤›› በማለት መልሰዋል፡፡
ፓርቲው ለወደፊቱ ሁለት አቅጣጫዎች ማዘጋጀቱን ገልጿል፡፡ አንደኛው ብሔራዊ መግባባትን ማስገኘት የሚል ሲሆን፣ ሁለተኛው ደግሞ ከሌሎች ፓርቲዎች ጋር አብሮ መሥራት የሚሉ ናቸው፡፡

Tuesday, 2 June 2015

ናትናኤል የዓለም ዘውድ የ3 አመት ከ3 ወር እስራት ተፈረደበት

የኢትዮጵያ መንግስት አይ ኤስ አይ ኤስ ኢትዮጵያውያን ላይ የፈፀመውን የጭካኔ እርምጃ ለመቃወም በጠራው ሰልፍ ላይ ‹‹ሁከትና ብጥብጥ›› ፈጥረሃል በሚል ተይዞ የታሰረው ናትናኤል የዓለም ዘውድ የ3 አመት ከ3 ወር እስራት ተፈረደበት፡፡ ዛሬ 25/2007 ዓ.ም የፌደራል መጀመሪያ ፍርድ ቤት መናገሻ ምድብ ችሎት የቀረበው ወጣት ናትናኤል የዓለም ዘውድ ላይ የቀረበው ክስ ‹‹ሁከትና ብጥብጥ መፍጠር›› የሚል ሲሆን አቃቤ ህግ ‹‹ሁከትና ብጥብጡን የፈጠረው ኢትዮጵያውያን ላይ ግድያ የፈፀመውን አይ ኤስ አይ ኤስ ለማውገዝ የተጠራው ሰልፍ ላይ በመሆኑ፣ በተፈጠረው ረብሻ በርካታ ሰዎች የተጎዱ በመሆኑ እና ረብሻውን የፈፀመው አምስተኛው አገራዊ ምርጫ እየተቃረበ ባለበት ወቅት በመሆኑና ይህም አደጋውን ያባብስ የነበር መሆኑን በማገናዘብ›› የሚል የቅጣት ማክበጃ መጨመሩን ገልጾአል፡፡

በሌላ በኩል በተመሳሳይ ክስ ተከሰው በዚሁ ፍርድ ቤት የቀረቡት ማቲያስ መኩሪያ፣ ብሌን መስፍን፣ ተዋቸው ዳምጤና መሳይ የተባለ ሌላ ወጣት መከላከያ ምስክር ለማቅረብ ለሰኔ 4 ተቀጥረዋል፡፡ እነ ማቲያስ ‹‹ሰልፉ ላይ ሀሰተኛ ወሬ በማውራት፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ እየተናገሩ በነበረበት ወቅት ወደ ፖሊስ ድንጋይ በመወርወር፣ ህዝቡን አትነሳም ወይ በማለት...›› የሚል ክስ የቀረበባቸው ሲሆን በጉዳዩ ላይ ዛሬ ይቀርባል ተብሎ የነበረው የቪዲዮ ማስረጃ ባለመቅረቡ በሚቀጥለው ቀጠሮ እንዲቀርብላቸው ጠይቀዋል፡፡

በተመሳሳይ ‹‹ጠቅላይ ሚኒስትሩ እየተናገሩ በነበረበት ወቅት ወደ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ድንጋይ በመወርወር ሰልፉን አውካችኋል›› የተባሉ ሌሎች አምስት ወጣቶች ለሰኔ 4 የመከላከያ ምስክር እንዲያቀርቡ ተቀጥረዋል፡፡ በሰልፉ ሰበብ ተይዘው የታሰሩት ወጣቶች በቤተሰብ እንዳይጠየቁ መከልከላቸውን ለፍርድ ቤቱ አስረድተዋል፡፡

ይህ ሕዝብ የዋዛ አይመሰላችሁ … (ለራስ ያልተፃፈ ደብዳቤ)


ይሕ ሕዝብ፡-
አፄ ቴዎድሮስን ወልዶ የበላ፤ የአፄ ዮሐንስን አንገት ያስቆረጠ፤ በእምዬ ምንሊክ ሐውልት ላይ ቁማር የሚጫወት፤ አባባ ጃንሆይን (ሥዩመ-እግዚአብሔር) አንግሶ ያዋረደ፤ ቆራጡን መሪ ጓድ መንግሥቱ ኃይለማሪያምን አንቆራጦ ያባረረ (በቁሙ አስቀምጦ ቲያትር የሚያሳይ)፤ ታጋይ መለስ ዜናዊን ያስደነገጠ (አስደንግጦ የገደለ የሚሉም አሉ)፤እንደሠራ አይገድል!
መሪዎቹን የሚፈራ- መሪዎቹን የሚጠላ
መሪዎቹ የሚፈሩት-መሪዎቹ የማይወዱት ፡፡ (No love lost between them)
ሠምና ወርቅ የሆነ ሕዝብ ነው፡፡

ይሕ ሕዝብ፡-
ፍቅሩንም ጥላቻውንም በሆዱ የሚፈጅ ምሥጢረ ሥላሴ የሆነ ሕዝብ ነው፡፡

ይሕ ሕዝብ፡-
አድዋ ላይ ነጭ ተራ ፍጡር መሆኑን ያስመሰከረ፡፡ “ጥቁር ሠው” የሠው ዘር መገኛ ብቻ ሳይሆን ከሌላው ዕኩል መሆኑን ያረጋገጠ ኩሩ ሕዝብ ነበር፡፡

ይሕ ሕዝብ፡-
ክፉ ቀንን ያለፈ፤ ከ66 የተረፈ፤ 77 ትንም 97ትንም ያያ… ተአምረኛ ሕዝብ ነው፡፡

ይሕ ሕዝብ፡-
ለኮሪያ የዘመተ፤ ማንዴላን ያሠለጠነ፤ ለአፍሪካ የነፃነትና የባንዲራ እርሾ ያበደረ… ገራሚ ሕዝብ ነበር፡፡

ይሕ ሕዝብ፡-
እየሱስ ክርስቶስ ሲጠመቅ ቆሞ የመሠከረ፤ ሞስሊሞች ሲሳደዱ ያስጠጋ፤ በመጽሐፍ ቅዱስ እስከ ቱንት የተጠቀሰ፤ በቅዱስ ቁራን የተወደሰ፤ በእየሩሳሌም ርስት ያለው፤ለነብዩ መሐመድ አዛን ያለ፤ የጠገበ መንፈሳዊ ታሪክ ያለው ሕዝብ ነው፡፡

ይሕ ሕዝብ፡-
የአክሱም ሀውልትን ያቆመ፤ የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናትን ያነፀ፤ የጎንደር ቤተ-መንግሥቶችንና የሐረር ግንቦችን የገነባ አሪፍ ሕዝብ ነበር፡፡

ይሕ ሕዝብ፡-
ንጉሡ ጥለውት ጠፍተው (ተሰደው) ለራሡ የጎበዝ አለቃ በመፍጠር ፋሺሽቶችን ተዋግቶ አገሩን ነፃ ያወጣ፤ መንግሥቱም (ኃይለማሪያም)ወደ ዚምባቡዬ ሪፈር በተባለ ጊዜ ራሱን በራሱ ያስተዳደረ ጨዋና ንጉሡ ከሥደት ሲመለሱ አልጋውን ያስረከበ የዋህ ሕዝብ ነበር (አይገርምም?)፡፡

ይሕ ሕዝብ፡-
በራሡ ቋንቋ ፍቅሩን አስከመቃብር የጻፈ፤ ሼክስፒርን ፈቶ የመግጠም ፀጋ (ዬ) የተሠጠው ሕዝብም ነው፡፡

ይሕ ሕዝብ፡-
በቅዱስ ያሬድ በኩል ከሠማየ ሠማያት የመልአክትን ዝማሬ ሰምቶ ዜማ የሠራ ዜመኛ ሕዝብ ነው፡፡ (ሞዛርት የለ -ቬቶቨን የት ነበር? ወፍ የለም)

ይሕ ሕዝብ፡-
ጦርነትን በባዶ እጁ እንዳሸነፈ ሁሉ ኦሎምፒክንም በባዶ እግሩ ድል ያደረገ ጉደኛ ሕዝብ ነው፡፡ (ሮም ሁለቴ ጉድ ሆነች እንዳሉት የአውሮፓ ወሬኞች…)

ይሕ ሕዝብ፡-
የዓባይን ልጅ ውሀ ጠማው ተረቱን እያደሰ ሱዳንን አልፎ ግብፅን እስከ ሲናይ በርሀ ውሃ የሚያጠጣ ሳይተርፈው የሚቸር ውሃ የሚያደርግ ሕዝብ ነው፡፡

ይሕ ሕዝብ፡-
ሌላው የአፍሪካ ሕዝብ የቀኝ ግዛት እባጩ ንፍፊት ሳይፈነዳለት አብዮት ያፈነዳና እውነተኛው መንገድ የእኔ ብቻ ነው ብሎ ባላብ አደርና በወዛደር በእናቸንፋለንና በእናሸንፋለን ጎራ ለይቶ አንድ ጥይትና ወጣት እስኪቀር ድረስ የሚጫረስ ግራ የገባው-ግራ -ዘመም ሕዝብ ነበር (ው)፡፡

ይሕ ሕዝብ፡-
ከእናቱ ልጅ ይልቅ በመጽሐፍ ለሚያውቃቸው አብዮተኞች በማድላት ወንድሙን የሚገድል፤ አገር ለመገንጠልና ለማስገገንጠል እስ-በሱ የተጫረሰ ጉደኛ ሕዝብ ነው፡፡
የሆነው ሆኖ…

ይሕ ሕዝብ፡-
መሪዎቹን የሚፈራ- መሪዎቹን የሚጠላ
መሪዎቹ የሚፈሩት-መሪዎቹ የማይወዱት ፡፡
ሠምና ወርቅ የሆነ ሕዝብ ነው፡፡
ፍቅሩንም ጥላቻውንም በሆዱ የሚፈጅ ምሥጢረ ሥላሴ የሆነ ሕዝብ ስለሆነ በቅጡ ግዙት፡፡