Tuesday 31 October 2017

ንግስት ይርጋ በማረሚያ ቤቱ ኃላፊዎች ማስጠንቀቂያ እንደተሰጣት ገለፀች

(በጌታቸው ሺፈራው)

በአማራ ክልል በነበረው ህዝባዊ እምብይተኝነት ሰበብ "ሽብር ክስ" የተመሰረተባቸው እነ ንግስት ይርጋ ዓቃቤ ህግ ያቀረበባቸው ማስረጃ መሰረት ይከላከሉ ወይም በነፃ ይሰናበቱ የሚለውን ለመበየን ቀጠሮ ተሰጥቷቸው የነበር ቢሆንም ብይኑ አልተሰራም ተብሎ ብይኑን ለመስራት 3 ጊዜ ለህዳር 1/2010 ቀጠሮ ተሰጥቶባቸዋል።

1 ተከሳሽ ንግስት ይርጋ በስም ካስመዘገበቻቸው የቤተሰብ አባላት ውጭ እንዳትጠየቅ፣ እንዲሁም ከቀኑ 6 ሰዓት እስከ ቀኑ 7 ሰዓት ባለው አንድ ሰዓት ውስጥ ብቻ እንድትጠየው ገደብ የተጣለባት መሆኑን ለፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 4 ወንጀል ችሎት አቤቱታ አቅርባ እንደነበር ይታወሳል።

ሀምሌ 21/2009 ዓም በዋለው ችሎት ፍርድ ቤት በቤተሰብ፣ የሀይማኖት አባት፣ የትዳር ጓደኛ እና በጠበቃዋ የመጠየቅ ህገ መንግስታዊ መብት እንዳላት፣ የሰዓት ገደብም እና ልዩ ክልከላ ሊደረግባት እንደማይገባ ወስኖ ለቃሊቲ ማረሚያ ቤት ትዕዛዝ ቢሰጥም የቃሊቲ ማረሚያ ቤት የፍርድ ቤቱን ትዕዛዝ ሳያከብር ቀርቷል።

ፍርድ ቤቱ ነሃሴ12/2009 የቃሊቲ ማረሚያ ቤት ለምን የፍርድ ቤቱን ትዕዛዝ እንዳላከበረ ኃላፊዎቹ በአካል ቀርበው እንዲያስረዱ ለዛሬ ጥቅምት 21/2010 ዓም ቀጠሮ ሰጥቶ የነበር ቢሆንም የቃሊቲ ማረሚያ ቤት ኃላፊዎች ዛሬም አልቀረቡም።

1 ተከሳሽ ንግስት ይርጋ ፍርድ ቤቱ የላከው ትዕዛዝ ለቃሊቲ ማረሚያ ቤት መድረሱን ገልፃ የእስር ቤቱ ኃላፊዎች እየጠሩ ለምን ማረሚያ ቤቱን ትከሻለሽ? ከማን በልጠሽ ነው? እያሉ በተደጋጋሚ እንዳስጠነቀቋት ለፍርድ ቤቱ ገልፃለች። ሆኖም ፍርድ ቤቱ "የፍርድ ቤቱን ትዕዛዝ ፈፅመዋል አልፈፀሙም የሚለውን ካጣራን በኋላ ማስጠንቀቂያ ሰጥተዋል አልሰጡም የሚለውን የምናጣራ ይሆናል" ብሎ በተደጋጋሚ ማስጠንቀቂያ ተሰጥቶኛል ብላ ያቀረበችውን አቤቱታ አልተቀበለውም።

6 ተከሳሽ ያሬድ ግርማ ማዕከላዊ እስር ቤት የምርምር ስራዎቹን ወስዶ እንዳልመለሰለት፣ በዚህ ጉዳይ ያቀረበው አቤቱታም መልስ እንዳላገኘ ለፍርድ ቤቱ አመልክቷል። ፍርድ ቤቱ በሌላ መዝገብ ምስክር ሊያሰማ መሆኑን በመግለፅ የሌሎች ተከሳሾችን አቤቱታ ሳይቀበል ቀርቷል። 5 ተከሳሽ በላይነህ አለምነህ " ለዚህ ቀን የተቀጠርነው የራሳችን ሰዓት ተመድቦልን ነው። በሌላ መዝገብ ምስክርነት አለ ልንባል አይገባም" ሲል ፍርድ ቤቱ አካሄዱን እንዲያስተካክል ቢያሳስብም ፍርድ ቤቱ አቤቱታውን አልተቀበለውም። "ቢያንስ ችሎቱ ያለንን ሀሳብ እንድናስረዳ ዕድል ይፍጠርልን" ቢልም ፍርድ ቤቱ በድጋሜ አቤቱታውን ሳይቀበለው በሌላ መዝገብ ወደያዘው ምስክርነት ገብቷል።

በሌላ በኩል ፍርድ ቤቱ ንግስት ይርጋን "ንግስቲ" እያለ በመጥራቱ የንግስት ይርጋ ጠበቃ 1 ተከሳሽ ስም "ንግስት" ተብሎ እንዲስተካከል ጠይቀዋል። በእነ ንግስት ይርጋ መዝገብ የተከሰሱት ንግስት ይርጋ፣ አለምነህ ዋሴ፣ቴዎድሮስ ተላይ፣አወቀ አባተ፣ በላይነህ አለምነህ እና ያሬድ ግርማ ናቸው።

                                                                                ንግስት ይርጋ

1 comment: