Sunday, 23 February 2014

የባህር ዳር ህዝብ ሆ ብሎ ወጣ!! ህዝቡ “ከባዶ ጭንቅላት… ባዶ እግር ይሻላል፡፡” አለ!

(ዜና ጥንቅር ዳዊት ከበደ ወየሳ)

የተቃውሞ ሰልፉ መነሻ የብአዴኑ ምክትል ሊቀመንበር አለምነው መኮንን የአማራውን ህዝብ በመናቅ እና በመሳደብ የተናገሩት ቃል ነው:: አማራውን… “በባዶ እግሩ እየሄደ ሌላውን ይንቃል” ካሉ በኋላ ለአማራው የሚቆረቆሩትን ደግሞ “ለሃጫቸውን…” እና የመሳሰሉትን እዚህ ላይ ለመጻፍ የምንጸየፋቸውን ቃላቶች ጭምር በመጠቀም አሽሙር አይሉት ስድብ ሰንዝረዋል:: ነገሩ ከአንድ የአማራን ህዝብ እወክላለሁ ወይም እመራለሁ ከሚል ሰው የሚጠበቅ ባለመሆኑ ብዙዎችን አሳዝኗል፣ አናዷልም::
በመሆኑም የአንድነት እና የመኢአድ ፓርቲዎች በጥምረት ሆነው በባህር ዳር ከተማ የተቃውሞ ሰልፍ ለማድረግ ወሰኑ:: ምክትሉ ሊቀመንበሩ ከሰልፉ በፊት እንደበፊቱ በትእቢት ተወጥረው ሳይሆን ረጋ ብለው ምን ለማለት እንደፈለጉ ቢያስረዱም ህዝቡ ግን ተቃውሞውን ቀጠለበት:: ለነገሩ በዚህ አጋጣሚ ሌሎች የሚነሱ የህዝብ ብሶቶች እንዳይነሱ በመስጋት የክልሉ አስተዳዳሪዎች አንዳንድ እንቅፋቶችን ለመፍጠር መሞከራቸው አልቀረም:: እርግጥ ነው… ተቃዋሚ ፓርቲዎቹ የተቃውሞ ሰልፉን ለማድረግ ሲዘጋጁ ብዙ እክል ገጥሟቸው ነበር:: ከተማ ውስጥ በራሪ ወረቀት መስጠት እና ቅስቀሳ ማድረግ ጭምር ተክልክለዋል:: ሆኖም ህዝቡ ራሱ ከልካዮቹን በመቃወሙ የፖሊሶቹ እገታ እና ጫና በረድ አለ:: ተቃዋሚዎቹ በባዶ እግር መሄድ ማለት ምንም ማለት እንዳልሆነ ለማሳየት ቅስቀሳ ሲያደርጉም ሆነ ዛሬ በሰላማዊ ሰልፉ ላይ… ጫማቸውን አውልቀው በባዶ እግራቸው ነበር የታዩት::
bahrdar demo13 2232014
ዛሬ እሁድ… እ.ኢ.አ የካቲት 16, 2006 ባህር ዳር ቀበሌ 12፣ ግሽ አባይ በሚገኘው የአንድነት ፓርቲ ጽ/ቤት አካባቢ ሰልፉ ሲጀመር የተለያዩ መፈክሮች እየተደመጡ ነው፡፡ በሰልፉ የፊት ረድፍ ላይ የፓርቲው ሊቀ መንበር ኢንጂነር ግዛቸው፣ ዶ/ር ኃይሉ አርአያ እና ሌሎችም አመራሮች ከህዝቡ ጋር ሆነው ታይተዋል:: ከግሽ አባይ የተነሳው ሰልፈኛ ጉዞውን በባህር ዳር ጎዳናዎች ላይ ማድረግ ሲጀምር ሌሎች በሺህ የሚቆጠሩ የከተማው ነዋሪዎች ሰልፈኛውን ተቀላቅለዋል:: የኢትዮጵያ ሰንደቅ አላማ የያዙ ወጣቶች ከፊት ሆነው መፈክር በማሰማት ከተማዋን ከጠዋት እንቅልፏ አባነኗት:: የባህር ዳሩን የተቃውሞ ሰልፍ የአንድነት ፕሬዝዳንት ኢ/ር ግዛቸው ሽፈራው፣ የመኢአድ ፕሬዝዳንት አቶ አበባው መሃሪ፣ የትብብር ለዴሞክራሲ ሰብሳቢ አቶ ግርማ በቀለ እንዲሁም የአንድነት ፓርቲ ብሄራዊ ምክር ቤት አባል የሆኑት አንጋፋው ፖለቲከኛ ዶ/ር ኃይሉ አርአያ ከፊት በመምራት ላይ ይገኙ ነበር::
bahrdar demo7 2232014
ከባህር ዳር በደረሰን ዘገባ መሰረት… ህጻናት ልጆቻቸውን በጀርባቸው ያዘሉ፣ በዊልቼይር የሚሄዱ፣ አዛውንቶች፣ ወጣቶች በአንድነት ሆነው በባህርዳር ከተማ የተቃውሞ ድምጻቸውን አሰምተዋል፡፡
bahrdar demo9 2232014
ሰልፉ 

ከመጠናቀቁ በፊት ቁጥራቸው 15 ሺህ ያህል ሰዎች እንደነበሩ ነው ከስፍራው የተዘገበው:: በወቅቱ ከተያዙት መፈክሮች የተወሰኑት…
“የመሬት ቅርምቱ ያብቃ!”
“ህዝብን ከርስቱ ማፈናቀል ይቁም”
“ገበሬው በገዛ መሬቱ ስደተኛ አይሆንም”
“የህዝብን ክብር የደፈሩት አቶ አለምነው ለፍርድ ይቅረቡ”
“ከባዶ ጭንቅላት ባዶ እግር ይሻላል”
“ህዝብን እየሰደቡ መግዛት አይቻልም”
“ድል የህዝብ ነው”
“አቶ አለምነው የሰደቡት የአማራን ህዝብ ብቻ አይደለም”
“ብአዴን /ኢህአዴግ የአማራን ህዝብ የመምራት የሞራል ልእልና የለውም”
ከስፍራው ሁኔታውን እየተከታተለ በቀጥታ ሲዘግብ የነበረው ነብዩ ሃይሉ እንደገለጸው ከሆነ… በሰልፉ ላይ አቶ አለምነው በአማራ ህዝብ ላይ የተናገሩት የጥላቻ ንግግር ለሰልፈኛው ተለቆ ህዝቡ ንግግሩን በቁጭት በብአዴን ላይ ተቃውሞውን እያሰማ ነው፡፡
“ክብራችንን የደፈሩት የብአዴን አባላት ለፍርድ ይቅረቡ”
“ነፃነታችን በእጃችን ነው”
“ከባዶ ጭንቅላት ባዶ እግር ይሻላል፡፡”
“ብአዴን የአማራን ህዝብ ለመምራት የሞራል ልዕልና የለውም”
“መተማ የኛ ነው፣ ቋራ የኛ ነው” በሰልፉ ላይ ከተስተጋቡ መፈክሮች መሀከል ይገኝበታል፡፡ ሰልፉ በህዝብ እንደታጀበ ቀጥሏል፡፡
በመጨረሻም የየፓርቲዎቹ ተጠሪዎች ለህዝቡ ንግግር አድርገዋል:: አቶ አበባው መሃሪ 1-አቶ አለምነው መኮንን በህግ እንዲጠየቅ
2- ብአዴን የአማራ ህዝባ ወኪል ነኝ ማለቱን እንዲያቆም
3-አቶ አለምነው መኮንን የአማራን ህዝብ ይቅርታ እንዲጠይቁ አሳስበዋል፡፡
የትብብር ለዴሞክራሲ ሰብሳቢ አቶ ግርማ በቀለ በንግግራቸው… አቶ አለምነው እንዲህ እንዲናገሩ ያደረገውን አምባገነን የኢህአዴግ ስርአት ለመቀየር እንስራ ብለዋል፡፡
የሰላማዊ ሰልፉን የመዝጊያ ንግግር ያደረጉት የአንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ ፕሬዘዳንት ኢንጂነር ግዛቸው ሽፈራው ናቸው፡፡ ኢንጂነሩ የመግቢያ ንግግራቸውን የከፈቱት በዛሬው እለት ደስ ካሰኙን መፈክሮች “ከባዶ ጭንቅላት ባዶ እግር ይሻላል” የሚለውን በማለት ነበር፡፡ ኢ/ር ግዛቸው ሽፈራው በንግግራቸው መጨረሻ ላይ አቶ አለምነው ይቅርታ ካልጠየቀና በህግ ፊት ካልቀረበ አንድነት በድጋሚ በባህርዳር የተቃውሞ ሰልፍ እንደሚጠራ አሳውቀዋል፡፡
አሁን ሰልፉ ተጠናቆ ህዝቡ በሰላም እንደወጣ፣ በሰላም ወደ ቤቱ እየተመለሰ ነው:: የሰላማዊ ሰልፉ በሰላም መጠናቀቅ የህዝቡን ጨዋነትና የአመራሩን ብስለት ያሳያል:: እርግጥ ነው… ሰላማዊ ሰልፉ ተጠናቆ ህዝቡ በሰላም ወደቤቱ ቢያመራም… ባህር ዳር ላይ የተለኮሰው የመነቃቃት ስሜት ግን በቀላሉ የሚበርድ አይመስልም:: እኛም መልካሙን ሁሉ እየተመኘን ዘገባችንን እዚህ ላይ አጠናቀናል::

ምስጋና: ሙሉውን ዘገባ ለማድረግ የቻልነው በተለይ ነብዩ ሃይሉ፣ ዳዊት ሰለሞን እና እስከዳር አለሙ ሁኔታውን እየተከታተሉ ከሚያቀርቡት የፎቶ እና የጽሁፍ መረጃ ተነስተን ነው:: በመሆኑም በኢ.ኤም.ኤፍ እና በአንባቢዎቻችን ስም ከልብ እናመሰግናችኋለን::

0 comments:

Post a Comment