Monday 30 December 2013

የአንድነት ፡ ሶስት ጠቅላላ ጉባዔ ፣ ሶስት ተፎካካሪዎች፣ ሶስት የተለያዩ ሊቀመንበሮች


ትላንት እሁድ ታህሳስ 20 ቀን 2006 ዓ.ም፣ በተሳካ ሁኔታ የተጠናቀቀዉን ጠቅላላ ጉባኤ ጨምሮ፣ የአንድነት ፓርቲ ሕጋዊ ሰርተፍኬት ካገኘበት ጊዜ ጀመሮ፣ ሶስት ጊዜ ጠቅላላ ጉባኤዎችን አድርጓል። ሶስቱንም ጊዜ፣ ሶስት የሚሆኑ እጩዎች ቀርበው ለሊቀመንበርነት ፉክክር ያደረጉ ሲሆን፣ ሶስቱንም ጊዜ የተለያዩ ግለሰቦችን ነዉ ሊቀመንበር አድርጎ የመረጠዉ።
የመጀምሪያዉ ጊዜ ኢንጂነር ግዛቸው ሽፈራዉ ፣ አቶ ተመስገን ዘዉዴና ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ ነበሩ ለእጩነት የቀረቡት። ወ/ት ብርቱካን በከፍተኛ ድምጽ የመጀመሪያዋ የአንድነት ፓርቲ ሊቀመንበር ሆና ተመረጠች። ኢንጂነር ግዛቸውና እና አቶ ተመስገን ምክትል ሊቀመናብርትና የሥራ አስፈጻሚ ኮምቴ አባላት ሆነው ቀጠሉ። ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ በመለስ ዜናዊ ግፈኛ አገዛዝ፣ በግፍና በጭካኔ፣ ወደ እሥር ቤት በተወሰደች ጊዜ፣ እስከሚቀጥለዉ ሁለተኛ የጠቅላላ ጉባኤ ድረስ ኢንጂነር ግዛቸው በተጠባባቂነት ድርጅቱን መሩ።
በሁለተኛዉ ጠቅላላ ጉባኤ ፣ ኢንጂነር ግዛቸው ለሊቀመንበርነት እንደማይወዳደሩ አሳወቁ። ዶር ነጋሶ ጊዳዳ፣ ኢንጂነር ዘለቀ ረዲ፣ ዶር ንጋት ራሳቸውን እጩ አደርገዉ አቀረቡ። ዶር ነጋሶ ጊዳዳ ድርጅቱን እንዲመሩ በአብላጫ ድምጽ ተመረጡ።
በትላንትናዉ ጠቅላላ ጉባኤ ከአባላትና ደጋፊዎች ዘንድ ከፍተኛ ግፊትና ተማጽኖ በመቅረቡ ኢንጂነር ግዛቸው ድርጅቱን በሊቀመንበርነት ለመምራት እራሳቸዉን እጩ አድርገዉ አቀረቡ። የፓርላማ ብቻኛ የመድረክ ተወካይ፣ የተከበሩ አቶ ግርማ ሰይፉ፣ እንዲሁም የአንድነት የፋይናንስ ክፍል ሃላፊ ሆነዉ የሚሰሩት የተከበሩ አቶ ተክሌ በቀለም ተወዳደሩ።
«ለምን መመረጥ እንዳለባቸው ? ምን ለመስራት እንዳሰቡ …» ለጠቅላላ ጉባኤዉ በግልጽና በነጻነት እንዲያስረዱ ፣ አሥር አሥር ደቂቃዎች ተሰጣቸው። አቶ ተክሌ በወቅቱ ለነበረዉ የዲሞርካሲያዊ መንፈስ ያላቸውን አድናቆት ገልጸው፣ እራሳቸዉን ከዉድድሩ አወጡ። አቶ ግርማ ሰይፉ የ«ምረጡኝ» ንግግራቸውን አሰሙ። ኢንጂነር ግዛቸውም እንደዚሁ። ኢንጂነር ግዛቸው ብዙ የሚናገሩት ስለነበረ አንድ ደቂቃ እንዲሰጣቸው በጠየቁ ጊዜ ፣ «ከሌሎች እኩል ነዉ መጠቀም ያላብህ» በሚል ንግግራቸውን እንዲያቋረጡ፣ ተደረጉ። በዚህ መልክ ምርጫዉ ፍትሃዊነት እንዲኖረው ካደረጉ አራት የአስመራጭ ኮሚቴ አባላት ዉስጥ ሁለቱ ሴቶች ነበሩ።
ከብዙ ውይይት በኋላ ድምጸ ተሰጠ። ኢንጂነር ግዛቸው በአብላጫ ድምጽ ድርጅቱን እንዲመሩ ተመረጡ። ከተሰጡት ድምጾች 37 የሚሆኑ፣ የሶስቱን ተወዳዳሪዎች ስም በመጻፉ፣ ሳይቆጠሩ ቀረ። ምንም እንኳን ኢንጂነር ግዛቸው ቢመረጡም፣ ጠቅላላ ጉባዔና የአንድነት ደጋፊዎች ምን ያህል ለአቶ ሰይፉና ለአቶ ተክሌ ያላቸውን ከበሬታ ያሳየ ነበር።
አንድ ግለሰብ ለዝንተ አለም የሚመራበት የፖለቲካ ባህል በስፋት በሚንጸባረቅበት የኢትዮጵያዉያን ማህበረሰብ፣ ይህ አይነቱ የአመራር አባላትን በዴሞክራሲያዊ ምርጫ የመምረጥና የመቀያየር አሰራር፣ የአንድነት ፓርቲ የበሰለና የስለጠነ ፖለቲካን በገሃድ ያሳየ ነዉ። የስለጠነ፣ የበሰለ፣ ዴሞክራሲያዊ የፖለቲካ ባህል በአገራችን እንዲሰፋ የምትፈልጉ ሁሉ ፣ የትግሉ አጋር እንዱትሆኑ ጥሪ እናቀርባለን።

0 comments:

Post a Comment