በሳውዲ ለሚገኙ ወገኖቻችን በአፋጣኝ እንድረስ፤ በወያኔ ላይ በጋራ እንነሳ!!! ግንቦት 7
በሳውዲ አረቢያ በሚገኙ ወገኖቻችን ላይ እየደረሰ ያለው መጠን የለሽ የመብት ጥሰት ለመቃወም በተለያዩ የዓለም አገራት የሚገኙ ኢትዮጵያዊያን በየአገራቱ የሚገኙ የሳውዲን ኢምባሲዎችን በተቃውሞ እያጨናነቁ ነው። በወገኖቻችን ላይ እየደረሰ ባለው ዘግኛኝ በደል የተሰማቸውን ጥልቅ የመጠቃት ስሜት ኢትዮጵያን በተቃውሞ ሰልፎቹ ላይ በሚያሰሟቸው መሪር የሐዘን እንጉሮችና የቁጭት ንግግሮች እየገለፁ ነው። ከሐዘንና ቁጭት ባለፈም ለበደል ለተጋለጡ ወገኖቻችን አስቸኳይ ሰብዓዊ ርዳታ ለማድረስ እና የዲፕሎማሲ ድጋፍን ለማሰባሰብ ዓለም ዓቀፍ ግብረ ኃይል ተቋቁሞ ሥራውን ጀምሯል።
ግንቦት 7: የፍትህ፣ የነፃነትና የዲሞክራሲ ንቅናቄ ይህንን ዓለም ዓቀፍ ጥረት ለመደገፍ በውጭ አገራት የሚገኙ አባላቱ ንቁ ተሳትፎ እንዲያደርጉ መመሪያ አስተላልፏል።
ይህ ሁሉ በውጭ አገራት እየተደረገ ያለ ጥረት ነው። ኢትዮጵያዊያን ባሉበት አገራትና ከተማዎች ሁሉ በዚህ ጉዳይ ላይ በአንድነት መንቀሳቀሳቸው የሚያስደስት ነገር ነው። ሌላው ቀርቶ በሳዉዲ ዋና ከተማ ሪያድ ውስጥ እንኳን ኢትዮጵያውያን የሳውዲን መንግሥት ተቃውመው ሰላማዊ ሰልፍ ወጥተዋል።
የሳውዲ መንግሥት በኢትዮጵያ ስደተኞች ላይ የያዘውን ጨካኝ አቋም እና በመንግሥት እውቅና በወገኖቻችን ላይ እየደረሰ ያለውን በደል መቃወም ያልተቻለው በኢትዮጵያ ውስጥ ብቻ ነው። በኢትዮጵያ ውስጥ ብቻ!!! ይህ እጅግ ያማል፣ ልብን ያደማል።
ወያኔ የሳውዲ የንግድ ሸሪኮቹን ለማስደሰት የፈንሳይን ግማሽ የሚያህል ለም መሬት በነፃ መስጠቱ በቂ አልመሰለውም። በአገራቸው ኢትዮጵያዊያንን ሲጨፈጭፉ፣ ሲገሉና ሲደፍሩ በቸልታ መመልከቱ በቂ የወዳጅነት ስጦታ መስሎ አልተሰማውም። እናም ሸሪኮቹ የበለጠ እንዲደሰቱና ከእስከዛሬ በበለጠ ገንዘብ እንዲደጉሙት ለማበረታታት አዲስ አበባ በሚገኘው ኤምባሲያቸው ፊት ለፊት ኢትዮጵያንን ደበደበላቸው።
ወያኔ ከሳውዲ ጋር ያለው ግኑኝነት “የቢዝነስ ሽርክና” ነው። ቢዝነሱም ኢትዮጵያዊያንን በቁማቸው መሸጥንም ያጠቃልላል። የወያኔ ሹማምንት እና የሳውዲም ቱጃሮች በዘመናዊ ባርነት ንግድ ውስጥ አቀባይና ተቀባይ ናቸው። ለዚህም ነው እየተነገደበት ያለው ምስኪን ኢትዮጵያዊ እጣ ፈንታ በአዲስ አበባና በሪያድ አንድ ዓይነት የሆነው። እዛ ዱላ፤ እዚህም ዱላ። እዛ እስር፤ እዚህም እስር። እዚያ ስድብ፤ እዚህም ስድብ። እዚያ ቶርቸር፤ እዚህም ቶርቸር። በባርያ ንግድ ውስጥ አቀባዩም ተቀባዩም ባርያዉን መግዛታቸው፣ መስበራቸው፣ መግደላቸው የማይቀር መሆኑ የታወቀ ነው።
ሌላው አሳዛኝ ጉዳይ ደግሞ የወያኔ ድኩማን ሹማምንት የሚሰጡት አስተያየት መስማት ነው። በሳውዲ ለሚገኙ ኢትዮጵያዊያን ፍትህ ለመጠየቅ በመላው ዓለም እና በአዲስ አበባ ደግሞ በሰማያዊ ፓርቲ አስተባባሪነት ወደ ጎዳና በወጡ ኢትዮጵያዊያን የኮሚኒኬሽን ሚኒስትር ተብየው “የፋሺሽት መፈክር አንግቦ በተጎሳቆሉ ዜጎች ስም የፖለቲካ ትርፍ ለማግኘት መጣር ብሎም መንግሥት በዜጎቹ ግዴለሽ እንደሆነ አስመስሎ ማቅረብ” ሲል ተሳልቋል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ተብየው ጨምሮ ሁሉም የወያኔ ሹማምንት “ሳውዲዎች በግዛታቸው ውስጥ ያሻቸውን የማድረግ “ሉዓላዊ” መብት አላቸው፤ መንግሥታችን የሳውዲ አረቢያን ሉዓላዊ መብት ያከብራል” እያሉ ይከራከራሉ። ለመሆኑ ይህንን የሚሉት ከልባቸው ነው? ፈጽሞ። ኢትዮጵያዊያንን ማሰቃየትና መግደል የቢዝነሳቸው አካል ስለሆነ ነው እንጂ የሉዓላዊነት ትርጉም ይህን ያህል ተምታቶባቸው አይደለም።
ሰብዓዊ መብቶች አገር፣ ድንበር፣ ዜግነት፣ ወይም ሌላ ማናቸው ሰው ሠራሽ ህግጋት ሊጥሷቸው እንደማይገቡ የወያኔ ሹማምንት ቢያንስ ሲነገር ሰምተው ያውቃሉ። ማንኛውም ሰው ያለፍርድ ቤት ትዕዛዝ መገደል፤ ሰቆቃ (ቶርቸር) እንዲደርስበት ማድረግ፤ ጾታዊ ጥቃት እንዲደርስበት ማድረግ እንደማይቻል ሰምተው ያውቃሉ። ሰብዓዊ መብቶች ሰዎች ሰው በመሆናቸው ብቻ ሊያገኙት የሚገባ ክብር መሆኑ በተሳተፉባቸው በርካታ ዎርክ ሾፖች ሰምተዋል። ያም ሆኖ ግን በዘመናዊው ዓለም እንስሳ እንኳን ያገኘውን ክብር ኢትዮጵያዊያን ተነፍገው በሪያድ ጎዳናዎች ሲታረዱ፤ በጭካኔ ሲደበደቡና ሲገረፉ፤ ሴቶች ሲደፈሩ፤ ሕፃናት በረሀብና በእርዛት ሲቀጡ የወያኔ ባለሥልጣኖች የበዳዮች አፈቀላጤ ሆነው የሚከራከሩት በዳዮቹ ሸሪኮቻቸው ስለሆኑ ነው።
ይህ ድርጊት በወያኔ እየደረሰብን ያለው በደል ምን ያህል ሥር የሰደደ እንደሆነ እና የኢትዮጵያዊያን ሰቆቃ ምንጭ የት እንዳለ አመላካች ሆኗል።
“ትግላችን የነፃነት ትግል ነው” ስንል “ከማን ነፃ ለመውጣት?” እያሉ የሚሳለቁ እንደነበሩና እንዳሉም ይታወቃል። በወያኔ አገዛዝ ኢትዮጵያዊያን ወደ ባርነት ማሽቆልቆላቸው ይህ ተጨባጭ ማስረጃ ነው። ከወያኔ የባርነት አገዛዝ ነፃ እስካልወጣን ድረስ ሌሎች አገሮች መብቶቻችን የሚያከብሩልን በየአገራቱ ልምድ እና ከወያኔ ጋር ባላቸው ሽርክና መጠን ነው።
ለሳውዲ መንግሥትና ቱጃሮቹ ከነዳጅ ቀጥሎ የሀብታቸው ምንጭ ከየአገሩ የሚመጣላቸው የድሀ ጉልበት ነው። የሳውዲ ቱጃሮች ድሆችን ከባርነት ባልተሻለ መንገድ ረግጠው በመግዛት ኑሮዓቸውን ያደለቡ ናቸው። ለወያኔ አገዛዝ ደግሞ ከቡና ቀጥሎ ከፍተኛው የገቢ ምንጩ ዜጎቹን በመሸጥ የሚሰበስበው ነው። ለወያኔ፣ ኢትዮጵያዊያን ወንዶችና ሴቶች ትርፍ አምጪ ሸቀጦች ናቸው። ወያኔና ሳውዲ – ሻጭና ገዢ ናቸው።
ባርያ ከሻጩ ነፃ ሳይወጣ ከአንድ ገዢ ነፃ ቢወጣ ሌላ ገዢ ስለሚመጣ ዘለቄታነት የለውም። እኛም ከወያኔ ነፃ ሳንወጣ ከሳውዲ ነፃ መወጣት አይቻለንም፤ ቢቻልም ነፃነታችን ዘላቂነት አይኖረውም።
ግንቦት 7: የፍትህ፣ የነፃነትና የዲሞክራሲ ንቅናቄ በሳዉዲ አረቢያ በሚገኙ ወገኖቻችን ላይ በሚደርሰው ጥቃት ክፉኛ ተቆጥቷል። በዚህ የመከራና ጭንቅ ሰዓት ለወገኖቻችን ለመድረስ የሚቻለውን ጥረት ሁሉ ማድረግ እንዳለብን ያምናል። አባላቱ በነብስ አድን ርብርብ በግንባር ቀደምትነት እንዲሳተፉ መመሪያ አስተላልፏል። ይህ አጣዳፊ ሆኖም ጊዜዓዊ መፍትሔ ነው። በግንቦት 7 እምነት የችግሮቻችን ሰንኮፍ ያለው አዲስ አበባ ነው። ሰንኮፉን ሳንነቅል የሚደርስብንን ውርደት በዘላቂነት መቀልበስ አንችልም። ስለሆነም በችግር ላይ የወደቁትን ወገኖቻችን እየረዳን፤ የችግሮቻችን ምንጭ በሆነው ወያኔ ላይ የተባበረ ክንዳችንን እናንሳ ይላል።
ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ!!!
0 comments:
Post a Comment