ዋዜማ
ራዲዮ- የኦሮሞ ነፃነት ግንባር ባለፉት ቀናት በደቡብ ምዕራብ ሞያሌ እና በምዕራብ ወለጋ አካባቢዎች በመንግስት ወታደሮች ላይ ጥቃት አድርሻለሁ ሲል አስታወቀ።
በአስመራ
ዋና መቀመጫውን ያደረገው የኦሮሞ ነፃነት ግንባር የማዕከላዊ ኮሚቴ አባልና ከፍተኛ አመራር የሆኑት ቢሎ ገርቢ ለዋዜማ የኦሮምኛ ቋንቋ እንደተናገሩት መንግስት በሞያሌ በኦሮሞዎች ላይ ያደረሰውን ጥቃት ተከትሎ በሁለት አቅጣጫ በተደረገ የደፈጣ ጥቃት በመንግስት ላይ ጉዳት አድርሰናል ብለዋል።
በሞያሌ
የውሀ ቦቴዎችን፣ ወታደራዊ ተሽከርካሪና በጉዞ ላይ በነበሩ ወታደሮች ተሽከርካሪ ላይ በተደረገ ጥቃት ሙሉ በሙሉ ውድመት አድርሰናል ብለዋል ቢሎ ገርቢ።
በምዕራብ
ወለጋ ጊዳሚ በሚባል ቦታ ከአሶሳ ወደ ደምቢ ዶሎ በሚጓዙ የመንግስት ወታደራዊ ተሽከርካሪዎች ላይ በተፈፀመው ማጥቃት አንዱ ተሽከርካሪ ሙሉ በሙሉ ሌላው በከፊል ወድመዋል። ይጓጓዙ የነበሩ ወታደሮች ላይ ጉዳት የደረሰ ሲሆን አንድ የመንግስት ወታደር ብቻ ተርፏል ብለዋል አመራሩ።
በጉዳዩ
ላይ የኣኢትዮጵያ መንግስት አስተያየትን ለማግኘት ተደጋጋሚ ሙከራ ብናደርግም የመንግስት ቃል አቀባዩ ስብሰባ ላይ በመሆናቸው ምላሽ አላገኘንም። መንግስት በአስመራ የሚደገፉ ሀይሎች በኢትዮጵያ ለተከሰተው ቀውስ ተጠያቂ ያደርጋል። በሞያሌ ለተፈፀመው ግድያም ኦነግን ማሳበቢያ አድርጎ ማቅረቡ ይታወቃል።
አቶ
ቢሎ ገርቢ ድርጅታቸው በሞያሌ አካባቢ መንቀሳቀሱ አዲስ ነገር አለመሆኑንና ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በተለያዩ አቅጣጫዎች ጥቃት በማድረስ በሀገር ቤት የሚደረገውን የኦሮሞ ህዝብ ትግል ለመደገፍ እየሞከረ መሆኑን አስምረውበታል።
አሁን
ለተደረሰበት ደረጃ ከዚህ ቀደም ኦነግ ያደረገው ትግልና የከፈለው መስዋዕትነት ውጤት ነው ያሉት አቶ ቢሎ ከዚህም በኋላ ከህዝባችን ጎን በመሆን ትግሉን እንቀጥላለን ብለዋል።
በዳውድ
ኢብሳ የሚመራውና በአስመራ የሚገኘው ኦነግ ነፃ ኦሮሚያን የመመስረት የፖለቲካ ግብ ያለው ሲሆን በኢትዮጵያ የሚካሄደውን ህዝባዊ ተቃውሞ እየመራሁ ያለሁት እኔ ነኝ ሲል ከዚህ ቀደም አስታውቋል።
0 comments:
Post a Comment