Friday, 10 November 2017

ንግስት ይርጋ በክሷ ምክንያት በደል እየደረሰባት እንደሆነ ተገለፀ

በጌታቸው ሺፈራው

"ሽብር" ክስ የተመሰረተባት ንግስት ይርጋ በክሷ ምክንያት ማረሚያ ቤት ውስጥ በደል እየደረሰባት መሆኑን ጠበቃዋ ለፍርድ ቤቱ ገልፀዋል። ንግስት ይርጋ በቤተሰብ ጥየቃ ገደብ እየተደረገባት መሆኑን ለፍርድ ቤት አቤቱታ ባቀረበችው መሰረት ፍርድ ቤቱ ምንም ገደብ ሳይደረግባት እንድትጠየቅ ቢወስንም የቃሊቲ ማረሚያ ቤት የፍርድ ቤቱን ትዕዛዝ ሳያከብር ቀርቷል።

ፍርድ ቤቱ ትዕዛዙን ለምን እንዳላከበረ በችሎት እንዲያስረዳ ትዕዛዝ ቢልክም ማረሚያ ቤቱ በሁለት ቀጠሮች ቀርቦ አላስረዳም። የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 4 ወንጀል ችሎት 3 ጊዜ በሰጠው ትዕዛዝ ዛሬ ህዳር 1/2010 ሁለት ኃላፊዎች ቀርበዋል።

የፌደራል ማረሚያ ቤቶች አስተዳደር የፍትህ አስተዳደር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዋና ሱፐር ኢንተንደንት አስቻለው መኮንን የማረሚያ ቤቱን እና የታራሚውን ደህንነት ለማስጠበቅ ሲባል ንግስት ተለይታ እንደምትጠየቅ፣ እንዲሁም ሁሉን እስረኛ በተመሳሳይ ሰዓት ማስተናገድ ስለማይቻል የንግስት ጥየቃ ሰዓት ከሌሎች እስረኞች የተለየ መሆኑን እና ባስመዘገበችው የቤተሰብ አባላት እየተጠየቀች መሆኑን አስረድተዋል።

ንግስት ይርጋ በበኩሏ ወደ ቃሊቲ ማረሚያ ቤት ስትገባ የሚጠይቋትን አስመዝግቢ መባሏንና ከተመዘገቡት ውጭ ያሉና 720 ኪሎ ሜትር ርቀት ድረስ ሊጠይቋት የሚመጡ ዘመድና ወዳጆቿ አልተመዘገባችሁም እየተባሉ እንደሚመለሱ ለፍርድ ቤቱ ገልፃለች። ጉዳዩን ለፍርድ ቤት በአቤቱታ አቅርባ ገደብ እንዳይደረግባት ብይን ቢሰጥም ማረሚያ ቤቱ ትዕዛዝን አለማክበሩን አስታውሳለች። ማረሚያ ቤቱ ለምን የፍርድ ቤቱን ትዕዛዝ እንደማያከብር በጠየቀችበት ወቅትም የሴቶች ጥበቃ እና ማረፊያ አስተዳደር ኃላፊ ዋና ሱፐር ኢንተንደንት አለም ጥላሁን "ይህን ትዕዛዝ የሰጠው ዳኛ ማን ነው? ማወቅ እፈልጋለሁ።" እንዳሏትና እኚህ ኃላፊ ችሎት ውስጥ እንደሚገኙ ለፍርድ ቤቱ አስረድታለች።

ሆኖም ፍርድ ቤቱ ችሎት ውስጥ የነበሩትን ኃለፊ ለምን ይህን እንዳሉ መልስ እንዲሰጡ ሳይጠይቃቸው ቀርቷል። ማረሚያ ቤቱ ለፍርድ ቤቱ በፅሁፍ በሰጠው መልስ ላይ የፈረሙት የሴቶች ጥበቃና ማረፊያ አስተዳደር ጥበቃና ደኅንነት ስራ ዘርፍ ኃላፊ ለተ እግዜር / መድኅን ናቸው። ሆኖም ትዕዛዙን ለፍርድ ቤት ያደረሱትና በቃል መልስ የሰጡት የለተ እግዜር ኃላፊ ናቸው የተባሉት ዋና ሱፐር አለም ናቸው።

ማረሚያ ቤቱ ኃላፊዎች ከሰጡት መልስ በተቃራኒ ገደብ እየተደረገባት መሆኑን ንግስት ለፍርድ ቤቱ ገልፃለች። በሀገራችን ባህል የታመመ እና የታሰረ ሰው ማንም እንደሚጠይቀው ያስታወሰችው ንግስት ይርጋ ጠያቂዎቿ መታወቂያ እስከያዙ እና ጠያቂና እሷን የሚቆጣጠሩ ፖሊሶች እስካሉ ድረስ በማንኛውም ሰው መጠየቅ መብቷ እንደሆነ ገልፃለች።

"ማንኛውም የተከሰሰ ሰው ነፃ ሆኖ የመገመት መብት አለው" ያሉት ጠበቃ ሄኖክ አክሉሉ በበኩላቸው፣ ማረሚያ ቤቱ ንግስት ይርጋን በክሷ ምክንያት በደል እየፈፀመባት እንደሚገኝ ለፍርድ ቤቱ አስረድተዋል። የፌደራል ማረሚያ ቤቱ ተወካይ ከገለፁት በተቃራኒ ሌሎች እስረኞች 3 ሰዓት እስከ 6 ሰዓት ሲጠየቁ ንግስት ይርጋ 6 እስከ 7 ሰዓት ባለው አንድ ሰዓት ብቻ እንደምትጠየቅ ገልፀውም ማረሚያ ቤቱ የሚያደርሰውን አድሎ አስረድተዋል። ካስመዘገብሽው ውጭ አትጠየቂም የሚለው የማረሚያ ቤቱ አሰራርም ህገ መንግስታዊ እንዳልሆነ ገልፀዋል።

የንግስት ይርጋ ሌላኛው ጠበቃ አቶ አለልኝ ምህረቱ ፍርድ ቤቱ የቃሊቲ ማረሚያ ቤት መልስ እንዲሰጥ ትዕዛዝ ቢሰጥም፣ መልስ ለመስጠት የመጡት የእስረኞችን የዕለት ተዕለት ጉዳይ የማይከታተሉ የፌደራል ማረሚያ ቤት ኃላፊ መሆናቸው ጉዳዩን በደንብ እንደማያውቁት ለፍርድ ቤቱ አስረድተዋል። የቃሊቲ ማረሚያ ቤት ባስመዘገበቻቸው ዘመድና ጓደኛ እየተጠየቀች ነው ያለ ሲሆን አቶ አለልኝ በበኩላቸው ህገ መንግስቱ የቅርብ ዘመድ እና ጓደኛ ሲል ወሰን እንደሌለው፣ ከዚህ መለስ ተብሎ ሊገደብ እንደማይገባ አብራርተዋል።

በንግስት አቤቱታ ጉዳይ ቀጠሮ የተሰጠው ማረሚያ ቤቱ የፍርድ ቤቱን ትዕዛዝ ለምን እንዳላከበረ ቀርቦ እንዲያስረዳ ለማዳመጥ የነበር ቢሆንም ዛሬም የሁለቱን ክርክር አዳምጦ ትዕዛዝ ሰጥቷል።

በዚህም መሰረት ንግስት ይርጋ በህገ መንግስቱ አንቀፅ 21 መሰረት ገደብ ሳይደረግባት እንድትጠየቅ ትዕዛዝ ሰጥቷል። የማረሚያ ቤቱ ኃላፊዎች ንግስት ይርጋ የማይገባ ጭቅጭቅ ማድረጓን ባይገልፁም ፍርድ ቤቱ " ተከሳሽም የማይገባ ጭቅጭቅ ውስጥ ላለመግባት ጥንቃቄ ያድርጉ፣ ህጉን ለይተው አውቀው ይጠቀሙ" ብሏዋል። ከችሎት ውጭ ያነጋገርኳቸው የንግስት ጠበቆች ንግስት መሰል ባህሪ አሳይታለች ባልተባለበት ፍርድ ቤቱ ያልተነሳ ነገር ላይ ለተከሳሽ ትዕዛዝ መስጠቱ ተገቢ አይደለም ብለዋል። በሌላ በኩል ንግስት ይርጋ ጥርሷን ታማ መድሃኒት ቢታዘዝላትም መድሃኒቱ በታዘዘላት ሰዓት እየተሰጣት እንዳልሆነ አቤቱታ አቅርባለች።

የማረሚያ ቤቱን መልስ ከመስማት በተጨማሪ እነ ንግስት ይከላከሉ ወይስ አይከላከሉ በሚለው ላይ ብይን ለመስጠት ተቀጥረው የነበር ቢሆንም ፍርድ ቤቱ "መዝገቡ ተመርምሯል።ጊዜ አግኝተን ማጠቃለል አልቻልንም" ብሎ ለህዳር 5/2010 ለብይን ሌላ ቀጠሮ ሰጥቷል።

0 comments:

Post a Comment