Thursday 8 December 2016

በአዋሽ አርባ በርሃ የታሰሩ ዜጎች በምግብና ውሃ እጦት እየተሰቃዩ ነው

ከአገሪቱ የተለያዩ ክፍሎች በኮማንድ ፖስቱ ኃይሎች እየታደኑ ለእስራት ከተዳረጉ ቁጥር የለሽ የስርዓቱ ገፈት ቀማሾች መካከል ከ5000 የማያንሱት በአዋሽ አርባ በረሃ በሚገኝ ወህኒ ቤት ውስጥ ታጉረው እንደሚገኙ ለማወቅ ተችሏል፡፡

ከአዲስ አበባ በቅርቡ በአዋሽ አርባ እንደሚገኙ የተነገረላቸውን የቤተሰቦቻቸውን አባላት ለመጠየቅ ያመሩ እናቶች፣አባቶች፣የትዳር አጋሮችና ህጻናት በወህኒ ቤቱ ጠባቂዎች ‹‹ሁለተኛ ድርሽ እንዳይሉ››ማስጠንቀቂያ ተነግሯቸው የናፈቋቸውን ወገኖቻቸውን የሚገኙበትን ሁኔታ ለማየት ጭምር ሳይፈቀድላቸው በሐዘን እንዲመለሱ ተደርገዋል፡፡

የቀድሞው የአንድነት ለፍትህና ለዴሞክራሲ ፓርቲ የፖለቲካ ጉዳዩች ኃላፊ የነበረው ደራሲው ሰሎሞን ስዩምን ጨምሮ የፓርቲው የብሄራዊ ምክር ቤት ሰብሳቢ የነበረው መምህርና ደራሲ አበበ አካሉ በአዋሽ አርባ ከሚገኙ ታዋቂ የህሊና እስረኞች መካከል ይጠቀሳሉ፡፡ የአበበ አካሉ ባለቤትና ልጆቹ እንዲሁም የሰሎሞን ቤተሰቦችና ለመውለድ ጥቂት ሳምንታት የቀራት ባለቤቱ በአዋሽ አርባ ቢገኙም ታሳሪዎቹን ለማግኘት ሳይፈቀድላቸው መመለሳቸውን ለመረዳት ተችሏል፡፡

በወህኒ ቤቱ እስረኞች ቆርቆሮ በቆርቆሮ በሆነ ክፍል ውስጥ ተፋፍነው እንዲታሰሩ መደረጋቸውና በቀን ሁለት ዳቦና አንድ ላስቲክ ውሃ ብቻ የሚሰጣቸው በመሆኑም ህይወታቸው አሳሳቢ ሁኔታ ላይ እንደሚገኝ ተነግሯል፡፡ አካባቢው ከፍተኛ ሙቀት ያለበት በመሆኑ የሚሰጣቸው ውሃ በቂ ባለመሆኑም ሁኔታውን አስቸጋሪ እንዳደረገባቸው የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡



0 comments:

Post a Comment