በቀጣዩ ወር በኢትዮጵያ ጉብኝት የሚያደርጉት የእንግሊዙ ጠቅላይ ሚኒስትር ዴቪድ ካሜሮን በጉብኝታቸው ወቅት የአቶ
አንዳርጋቸው ፅጌን ጉዳይ የመወያያ አጀንዳ እንደሚያደርጉት ተገለጠ። የብሪታኒያ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ተቋማት
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከተለያዩ አካላት የቀረበባቸውን ግፊት ግምት ውስጥ በማስገባት በኢትዮጵያ መንግስት ላይ ጫናን
እንዲያደርጉ በማሳሰብ ላይ መሆናቸውም ታውቋል። በቀጣዩ ወር መጨረሻ ላይ በኢትዮጵያ ጉብኝታቸው የሚያደጉት ጠቅላይ
ሚኒስትሩ ከአቶ አንዳርጋቸው ፅጌ ጉዳይ በተጨማሪም በሁለቱ ሃገራት መካከል ስላለው የደህንነት እና የፀጥታ ትብብር
ዙሪያ እንደሚመክሩም በሃገር ውስጥ ያሉ መገናኛ ብዙሃን ረቡዕ ዘግቧል።
ስማቸውን መግለጽ ያልፈለጉት የውጭ ጉዳይ
ሚኒስቴር ባለስልጣናት በዴቪድ ካሜሮን ጉብኝቶች ወቅት የአቶ
አንዳርጋቸው ፅጌ ጉዳይ ለውይይት እንደሚቀርብ አስረድቷል። ከሳምንት በፊት በኢትዮጵያ ጉብኝት ያደረጉ የእግሊዝ
የደህንነትና የኢሚግሬሽን ባለስልጣናት ዴቪድ ካሜሮን በኢትዮጵያ በሚኖራቸው ቆይታ የተለያዩ አበይት አጀንዳዎችን
አንስተው እንደሚወያዩ ይፋ ማድረጋቸውን መዘገባችን ይታወሳል።
የጠቅላ ሚኒስትሩ ጉብኝትም በቅርቡ ከተለያየ አካላት
አቶ አንዳርጋቸው ፅጌ እንዲፈቱ ግፊትን እንደሚያደርጉ የቀረበላቸውን ከ130ሺ በላይ ፊርማ ተከትሎ መሆኑም ታውቋል።
ሪፕሪቭ የተሰኘውን የብሪታኒያ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅት ጨምሮ በርካታ አካላት ሀገሪቱ ለኢትዮጵያ
የምትሰጠውን የደህንነትና የጸጥታ ድጋፍ እንድትቋረጥ ሲያሳስቡ መቆየታቸውም የሚታወቅ ነው። ይኸው የሁለቱ ሃገራት
የደህንነት ትብብር በዴቪድ ካሜሮን ጉብኝት ወቅት ሰፊ ውይይት ይካሄድበታል ተብሎም ይጠበቃል። የታሰሩበት ቦታ
የማይታወቀው አቶ አንዳርጋቸው ፅጌ በቤተሰቦቻቸውም ሆነ በህግ አካላት ዘንድ እንዳይጎበኙ ተደርጎ የሚገኝ ሲሆን፣
የተለያዩ አካላት የአቶ አንዳርጋቸው የጤንነት ሁኔታም አሳሳቢ እየሆነ መምጣቱን በመግለጽ ላይ ናቸው።
ኢሳት
0 comments:
Post a Comment