Monday 15 February 2016

እነ ሀብታሙ አያሌው እንዲፈቱ ፍ/ቤት ትዕዛዝ ቢያስተላልፍም ማ/ቤት ሊለቃቸው አልቻለም

*‹‹ትዕዛዙ ግልጽ አልሆነልንም›› ማ/ቤት
*‹‹ይሄ የፍ/ቤቱን ትዕዛዝና ህገ-መንግስቱን አለማክበር ነው›› ዳኛ ዳኜ መላኩ

በነገረ ኢትዮጵያ ሪፖርተር
በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ከተከሰሱበት የሽብር ወንጀል ነጻ እንደሆኑ ተበይኖ ከእስር እንዲፈቱ ትዕዛዝ ከተሰጠላቸው ሰባት ወራት ያስቆጠሩትና አሁንም በእስር ላይ የሚገኙት የፖለቲካ ፓርቲዎች አመራሮች እነ ሀብታሙ አያሌው ዛሬም ጠ/ፍ/ቤት በሰጠው ትዕዛዝ መሰረት ከእስር ሊፈቱ አለመቻላቸው ታውቋል፡፡

ዛሬ የካቲት 7/2008 ዓ.ም ፍ/ቤት የቀረቡት አቶ ሀብታሙ አያሌው፣ አቶ ዳንኤል ሺበሺ፣ አቶ አብርሃ ደስታ፣ አቶ የሽዋስ አሰፋ እና መምህር አብርሃም ሰለሞን ባለፈው ሳምንት ዳኛ ዳኜ መላኩ ‹‹ከቤታችሁ መጥታችሁ ችሎት ትቀርባላችሁ›› ብለዋቸው የነበር ቢሆንም ትዕዛዛቸው ሳይከበር ቀርቶ ሁሉም ከቤታቸው ሳይሆን ከማረሚያ ቤት ቀርበዋል፡፡

መዝገቡ ለዛሬ የተቀጠረው አቃቤ ህግ የደህነት መስሪያ ቤት የሚልክለትን ማስረጃ ማቅረቡን ለመጠባበቅ ሲሆን፣ ‹‹በፍ/ቤቱ ትዕዛዝ መሰረት 367 ገጽ ያለው ማስረጃ አቅርበናል›› ብሏል አቃቤ ህግ፡፡ ሆኖም አቃቤ ህግ የካቲት 5/2008 ዓ.ም ከደህንነት መ/ቤት ተላከልኝ ያለውን ማስረጃ ኮፒውን ለተከሳሾች ማድረስ አልቻለም፡፡ በዚህም ኮፒውን በችሎት ለይግባኝ መልስ ሰጭዎች ለማድረስ ለየካቲት 9/2008 ዓ.ም ቀጠሮ ተሰጥቶታል፡፡

ፍርድ ቤቱ ይግባኝ መልስ ሰጭዎች እስካሁን ከእስር አለመፈታታቸውን በተመለከተ ማረሚያ ቤቱን ጠይቋል፡፡ የቃሊቲ ማረሚያ ቤት አቶ ዳንኤል ሺበሽ፣ አቶ አብርሃ ደስታና አቶ የሽዋስ አሰፋ የችሎት መድፈር ቅጣት አለመጨረሳቸውን ላለመፍታቱ በምክንያትነት አቅርቧል፡፡ ሦስቱ ይግባኝ መልስ ሰጭዎች በበኩላቸው የችሎት መድፈር ቅጣታቸውን እንደጨረሱ ተናግረዋል፡፡ አቶ የሺዋስ አሰፋ ቅጣታቸውን በተመለከተ፣ ‹‹ችሎት መድፈር የተቀጣነው ሁለታችን (የሽዋስና ዳንኤል) 14 ወራት፣ እና አብርሃ 16 ወራት እስር ነው፡፡ እኛ ከታሰርን 1 አመት ከ9 ወራት ሆኖናል፡፡ ስለዚህ እስራችንን ጨርሰናል›› ብሏል፡፡

ማረሚያ ቤቱ ግን ቅጣቱ የሚታሰበው ችሎት መድፈሩ ከተፈጸመበት ቀን ነው ወይስ እጃቸው ከተያዘበት አንስቶ ነው የሚለው ግልጽ እንዳልሆነለት ይገልጻል፡፡ ሦሥቱ ይግባኝ መልስ ሰጭዎች የችሎት መድፈር ቅጣቱ የተወሰነባቸው መጋቢት 1/2007 ዓ.ም እንደነበር ይታወሳል፡፡

በሌላ በኩል በቂሊንጦ ማረፊያ ቤት የሚገኙት አቶ ሀብታሙ አያሌውና መምህር አብርሃም ሰለሞን ምንም አይነት ቅጣት ባይኖርባቸውም ከእስር ሊፈቱ አልቻሉም፡፡ የማረሚያ ቤቱ ተወካይ ‹‹የፍ/ቤቱ ትዕዛዝ ግልጽ አልሆነልንም›› የሚል መልስ ሲሰጥ ዳኛ ዳኜ መላኩ ደግሞ ‹‹እናንተ ምክንያቱ አያገባችሁም፤ መፍታት አለባችሁ፣ ይህ የፍርድ ቤቱን ትዕዛዝ እና ህገ መንግስቱን አለማክበር ነው›› በማለት ዛሬውኑ ከእስር እንዲፈቱ ሲሉ አዝዘዋል፡፡

በሌላ በኩል ቃሊቲ የሚገኙት እነ አብርሃ ደስታ የእስር ቤት አስተዳደሩ በቤተሰቦቻቸው እና በጓደኞቻቸው እንዲጠየቁ እንዲያደርግ ትዕዛዝ እንዲሰጥላቸው በድጋሜ አቤቱታ አቅርበዋል፡፡ ‹‹ለምን እንደታሰርንም ለምን እንደምንፈታም አሳሪው አካል ያውቃል፡፡ አሁን እኛ የምንጠይቀው፣ መቼም እንፈታ መቼ ታስረን እያለን ሰዎች እንዲጠይቁን ትዕዛዝ እንዲሰጥልንና የትዕዛዙን መፈጸም ክትትል እንዲደረግልን ነው›› ሲል አቶ ዳንኤል ሺበሺ ተናግሯል፡፡


0 comments:

Post a Comment