Saturday, 7 November 2015

ከዞን ዘጠኝ በኋላስ-ዝምታ?

የዞን ዘጠኝ ጦማርያን መፈታትን ተከትሎ በኢትዮዽያ ውህኒ የሚማቅቁ ሌሎች ጋዜጠኞች ጉዳይ ተገቢውን ትኩረትና ድጋፍ እንዳላገኘ የሚያመላክቱ ፍንጮች እየታዩ ነው። አለም አቀፍ ተቋማትም ሆኑ የመብት ተቆርቋሪ ወዳጆች ስለ ቀሪዎቹ ታሳሪዎች አስታዋሽ የሚፈልጉ ይመስላሉ።

በኢትዮጵያ መንግስት የታሰሩ የፖለቲካ እስረኞች አያያዝ ኹኔታ እየከፋ መምጣቱን ከታሳሪዎቹ ቤተሰቦች በሚሰሙ ቅሬታዎች እየተተገለጹ ነው። ዋዜማ ያነጋገረቻቸው የጋዜጠኛው ተመስገን ደሳለኝ ቤተሰቦች ተመስገን ከጤናው መታወክ በተጨማሪ በቤተሰቦቹ እንዳይጎበኝና ምግብ እንዳይገባለት በመደረጉ ያለበትን እስር የከፋ ደረጃ ላይ እንዳደረሰው ተናግረዋል። ቤተሰቦቹ ከሚኖሩበት 165 ኪሜ ርቀት ላይ በሚገኘውየዝዋይ እስር ቤት የታሰረው ተመስገን ይህን ያህል ርቀት እየተመላለሱ እንዲጠይቁትና ስንቅ እንዲያቀብሉት በተገደዱት የቤተሰቡ አባላት ላይ የተጣለው እገዳ ተጨማሪ መንገላታት እንዳመጣባቸው ይናገራሉ።
ተመስገን ደሳለኝ የፍትህ ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ
ከጥቅምት 3/2007 ዓ.ም ጀምሮ የመንግስትን ስም ማጥፋት፣ ህዝብን ማነሳሳትና የህዝብን አመለካከት ማናወጥ በሚሉ ሶስት ክሶች፣ የቅጣት ርዝመት 3 አመት ጽኑ እስራት
ይህን የመሰለው ድርብ ቅጣት በተመስገን ላይ ብቻ የተገደበ አይደለም። ሌሎችም የፖለቲካ እስረኞች ይህን የመሰለ ችግር እየደረሰባቸው እንደኾነ ሲነገር ቆይቷል። ሌላው ታሳሪ ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋም ይህን የመሰለድርብርብ ቅጣት እንደተጣለበትም ይነገራል። በሽብርተኝነት ሴራ ተካፍለሃል በሚል ሰበብ የ18 ዓመት እስር የተፈረደበት እስክንድር በተመሳሳይ ኹኔታ በቤተሰቡና በጓደኞቹ እንዳይጎበኝ ከመደረጉም በተጨማሪየሚያነበው መጽሐፍ እንዳይገባለትና ከሌሎች እስረኞች ጋር እንዳይገናኝ ማዕቀብ ሲጣልበት መቆየቱም ሲዘገብ ነበር። ከዚህም በላይ በተደጋጋሚ በጭለማ እስር ቤት ውስጥ እንዲቆይ ሲደረግ ቆይቷል።

መታሰሩ በራሱ የከፋ የመብት ጥሰትና በደል ሆኖ ሳለ ስለምን ነውረኝነት የተቀላቀለበትና የበቀል አያያዝ በጋዜጠኞች ላይ ይበረታል? የሚለው ጥያቄ – መልሱ ……የኢህአዴግ መንግስት ለዜጉቹ ባለው ዝቅ ያለ አመለካካትና ጥቂቶች ለስልጣናቸው ባላቸው ስስት ሳቢያ ነው።
እስክንድር ነጋ

                             ሳተናው፣ ወንጭፍ እና ምኒልክ የተባሉ ጋዜጦች አዘጋጅ
                             ጥፋተኛ የተባለበት ወነጀል ከአሸባሪነት ጨምሮ 23 ወንጀሎች
                             የቅጣት ውሳኔ የተሰጠበት ጊዜ ሐምሌ 6/2004 የኢትዮጵያ ፌዴራል ፍርድ ቤት
                            የቅጣት ርዝመት ለ18 ዓመታት

የውብሽት ደሳለኝ አያያዝም ከዚህ የተለየ አይደለም። ዘላለም ወርቃአገኘሁ፣ ዮናታን ተስፋዬና ባህሩ ደጉ በኢንተርኔት ደህንነት ዙሪያ ስልጠና ይሰጣል የሚል መረጃ ደርሷቸው፣ በስልጠናው ለመወዳደር ማመልከቻ በመፃፋቸው የአሸባሪነት ክስ ቀርቦባቸው ከአንድ አመት በላይ ወህኒ እየተንገላቱ ነው።
“የፖለቲካ እስረኞች የሉም፣ ማንም ሰው በሚጽፈው ነገር ምክንያት ወይም ባለው የፖለቲካ አመለካከት ሰበብ አልታሰረም” እያለ የሚክደው የኢትዮጵያ መንግስት ይህን የመሰለውን ተደራራቢ ቅጣት በእነኚህና በሌሎችም የፖለቲካ እስረኞች ላይ መፈፀሙ ሰለሀገሪቱና ስለዜጎቹ ያለውን ዝቅ ያለ አመለካከት ያንፀባርቃል።

በእስረኞቹ ላይ ይህን በቀለ መሰል ተደራራቢ ቅጣት መፈጸሙ ለብዙዎች በእነዚህ ሰዎች ላይ የሚቀርበው ክስ ፖቲካዊ ለመኾኑማረጋገጫ ነው። እነዚህን ታሳሪዎችም ከሌሎች እስረኞች በተለየ አደገኛ ናቸው ብሎም እንደሚሰጋ የሚያሳይ ድርጊት እንደሚፈጸምባቸው ማሳያ እንደኾንም ለብዙዎች የማያከራክር ጉዳይ ነው።
ውብሸት ታዬ
የአውራምባ ታይምስ ምክትል-ዋና አዘጋጅWubshet
የታሰረው ሰኔ 2003 አ.ም
ጥፋተኛ የተባለበት ወንጀል በሽብርተኝነት ክስ
የጥፋተኝት ፍርድ የተሰጠበት ጊዜ ጥር 2004
የቅጣት ርዝመት 14 አመት ፡፡

የዞን 9 ጦማርያንና አብረዋቸው ታስረው የነበሩ ጋዜጠኞች ጉዳይ ባልተጠበቀ ኹኔታ መንግስት የቀረበባቸውን ክስ በመተው ከክሱ ነጻ ናቸው የሚል ብያኔ ተሰጥቶ ከእስር ከመፈታታቸው በፊት ይህንኑ መሰል የተለየበደል ሲፈጸምባቸው እንደነበረ ሲነገር ቆይቷል። በቅርቡ የዞን 9 ጦማርያንና የጋዜጠኞቹን መፈታት እንደ ተስፋ ሰጪ በጎ ጅምር አድርገው የተመለከቱት ቢኖሩም እስካሁን ድረስ ሌሎቹ የፖለቲካ እስረኞችእንደሚፈቱ የሚያሳይ ፍንጭ የለም። በእስር ላይ ያሉበትም ኹኔታ ከቀድሞው በምንም ያልተለየ እንዲያውም እየባሰ መምጣቱን የችግሩ የቅርብ ገፈት ቀማሽ የኾኑት ቤተሰቦቻቸው እየተናገሩ ነው።
ዘላለም ወርቃገኘሁ ፣ ዮናታን ወልዴ ፣አብረሃም ሰለሞን እና ባህሩ ደጉZelalem Workagegnehu
ጥፋት የኢንተርኔት ደህንነት ስልጣና ለመካፈል ማመልከት
ክስ ሽብር ከግንቦት ሰባት ጋር ግንኘነት
የታሰሩት ሀምሌ 2006

የዞን ዘጠኝ ጦማርያንና አብረዋቸው ታስረው የነበሩት 3 ጋዜጠኞች ባልተጠበቀ ኹኔታ የመፈታት ጉዳይ አንዳንድ ተንታኞች ዘንድ በገዥው ፓርቲ ውስጥ በተፈጠረ ድንገተኛ ለውጥ ምክንያት የተወሰደ ርምጃ ሊኾን እንደሚችል ግምት አሳድሮ ነበር። ይኹንና ይህን የመሰለ የአቋም ለውጥ መምጣቱን የሚያሳይ ቀጣይ ርምጃ ሲወሰድ አልታየም። ብዙዎችን የሚያስማማው ጉዳይ የኢትዮጵያ መንግስት በዞን 9 ጦማርያንና በተፈቱት ሌሎች ጋዜጠኞች ባቀረበው ክስ ምክንያት የደረሰበትን ዓለማቀፋዊ ተጽዕኖ ለማርግብ ሲል ብቻ ይህን ያልተጠበቀ ውሳኔ ማሳለፉ ነው። የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ ጉብኝትም ይህንኑ ዓለማቀፋዊ ተጽዕኖ ከፍተኛ ደረጃ ላይ አድርሶት እንደነበረ ይጠቀሳል።
ለዚህ ዓለማቀፋዊ ተጽዕኖ ምክንያት የነበረው ከሌሎች የፖለቲካ እስረኞች በተለየ ለዞን 9 ጦማርያን ይደረግ የነበረው ዘመቻ #Freezone9bloggers በኢትዮጵያ ብቻ ሳይኾን በዓለማቀፍ ደረጃም ሲወዳደር ብዙ ተሳታፊዎች የነበሩት እና ዓለም አቀፍ የመገናኛ ብዙሃንን ትኩረት የሳብም ነበር።
በአገር ውስጥ ካለው ስም ይልቅ በውጪው ዓለም ላለው ገጽታው የሚፈራ የሚመስለው የኢትዮጵያ መንግስት እያንዳንዱ የፍርድ ሂደት እየተመዘነ የፈጠራ ክሶቹ ለስላቅ በመዳረጋቸው ባልጠበቀው ተጽዕኖ ስር መውደቁ ይህን ከባህርይው ውጪ የኾነ ውሳኔ እንዲወስን ያስገደደው ይመስላል።
በተመሳሳይ ክስ ወንጀለኞች የተደረጉት ዘላለም ወርቅአግኘሁና ሌሎች 3 ጓደኞቹ አለመፈታታቸውም በመንግስት በኩል የተደረገ የአቋም ለውጥ አለመኖሩን ማሳያም ተደርጎ ይቀርባል።
ዘላለም ወርቅአግኘሁና ጓደኞቹ የቀረበባቸው ክስ የኢንተርኔት ደኅንነት (Internet Security) ስልጠና ለመውሰድ ማመልከታቸው ነው። ይህንንም መሰል ክስ በዞን 9 ጦማርያን ላይ ቀርቦ የነበረና መንግስትንም ለከፍተኛ ትችት ያጋለጠው መከራክርያው ነበር።

ይህን ስልጠና መውሰድም ይኹን ተግባራዊ ማድረግ ከማንኛውም ኢንተርኔት ተጠቃሚ ግለሰብ የሚጠበቅና የኢሜይል መልዕክቶችንም ይኹን በኢንተርኔት የሚደረጉ ማንኛውንም የመረጃ ልውውጦች በጠላፊ ወይም ሀከር እንዳይጠቃ የመጠበቅ የኢንተርኔት ሀ ሁ ነው። ብዙ ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች ይህን ስልጠና ለጋዜጠኞችና ሰበአዊ መብት ተሟጋቾች ቢሰጡትም እንደ ወንጀል ሲቀርብ የታየው ግን በኢትዮጵያ ብቻ ሳይኾን አይቀርም። ዘላለም ወርቅአገኘሁና ጓደኞቹም ይህን ስልጠና ለማግኘት ያላቸው ምኞት ብቻ ከወንጀል ተቆጥሮ ከአንድ ዓመት በላይ በእስር ላይ እንዲቆዩ አድርጓቸዋል።
የኢትዮጵያ መንግስት ሐሳብን በነፃነት መግለጽንና የፈለጉትን የፖለቲካ አቋም መደገፍን ወንጀል አድርጎ እንደሚቆጥር በተደጋጋሚ ቢከሰስም የዞን 9 ጦማርያንን በተመለከተ የተደረገውን ዓይነት ውጤታማ ዘመቻ ተደርጎበት አያውቅም።
አሁን በተመስገን፣ በእስክንድርና በነዘላለም ላይ እየደረሰ ያለውን ችግር ሲገልጹ የሚታዩት በዋነኝነት የቤተሰቦቻቸው አባላትና የቅርብ ጓደኞቻቸው ናቸው። ዓለማቀፍ የመብት ተሟጋች ቡድኖችም ችግሩ በዞን 9 ተጀምሮ በእነርሱ መፈታት ያቆመ ይመስል ድምጻቸውን ብዙም አያሰሙም። አንዳንድዕቹ የድረገጽ መረጃዎቻቸውን እንኳን ወቅቱን በጠበቀ መረጃ አላስተካከሉትም።
የእነዚህ እስረኞች ጉዳይ የቤተሰቦብቻቸው ችግር ብቻ ተደርጎ መተዉም ጉዳዩን በአገር ደረጃ ካለው የለውጥ ጥያቄ የነጠለው ይመስላል። በዚህ ወቅት ለዞን 9 ጦማርያን የተደረገውን ውጤታማ ዘመቻ ለመቃኘትና ለመብት መከበር ብለው ዋጋ እየከፈሉ ላሉ ጋዜጠኞች፣ ጦማርያን፣ የመብት ተሟጋቾችና የፖለቲካና የሐይማኖት መሪዎች አዲስ ዘመቻ የሚጀመርበት እንጂ ጉዳዩ የተደመደመ አይመስልም።

Source:: wazemaradio

Thursday, 5 November 2015

ረሃብ የመንግሰት ፖሊሲ ብልሹነት እንጂ የዝናብ እጥረት ዉጤት አይደለም!

ከኤፍሬም ማዴቦ...............ከአርበኞች መንደር !!

ደርግ የቀዳማዊ ኃ/ሥላሤን ስርዐት ከደመሰሰ በኋላ ወሎ፤ ትግራይና ሰሜን ሸዋ ዉስጥ ህዝብ እንደ ቅጠል ሲረግፍ እሳቸዉ የልደት በዐላቸዉን ለማክበር ከዉጭ አገር ኬክ ያስመጣሉ ብሎ ነበር ንጉሰ ነገስቱንና ስርዐታቸዉን የከሰሰዉ። በአስራ ሰባቱ የደርግ ዘመን ሁለት ግዜ ከባድ ረሃብ ተነስቶ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎቻችን አልቀዋል። በተለይ በ1977 ዓም ሰሜን ኢትዮጵያ ዉስጥ የተከሰተዉና የአለምን ህዝብ ያስደነገጠዉ ረሃብ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ኢትዮጵያዉያንን እንደ ቅጠል ሲያረግፍ ደርግ የስብሰባ አዳራሽ ለመስራትና የኢሠፓን ምስረታ ለማክበር ብዙ ሚሊዮን ዶላር እንዳባከነ ይታወሳል። ህወሃት የደርግን ስርዐት ሲዋጋ የኢትዮጵያን ህዘብ ከጎኑ ለማሰለፍ ከተጠቀመባቸዉ ዋና ዋና የፕሮፓጋንዳ ስራዎች ዉስጥ አንዱ ይህንኑ ረሃብ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎቻቸንን ሲገድል ደርግና ባለሟሎቹ የፓርቲ ምስረታ ለማክበርና አዳራሽ ለማሰራት በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠር ዶላር ያባክናሉ የሚል ፕሮፓጋንዳ ነበር። ከዚህ በተጨማሪ በአገሪቱ ዉስጥ ለደረሰዉ ረሃብ ዋናዉ ምክንያት የዝናብ እጥረት ሳይሆን የደርግ የተበላሸ የኤኮኖሚና የፖለቲካ ፖሊሲ ነዉ ብሎ ደጋግሞ ደርግን መክሰሱ አይረሳም። ህወሃት ኢትዮጵያን በመራባቸዉ ባለፉት ሃያ አራት አመታት ዉስጥ የዘንድሮዉን ጨምሮ የኢትዮጵያ ህዝብ ሦስት ግዜ ለረሃብ አደጋ ተጋልጧል። የዘንድሮዉ ረሃብ ደግሞ ስፋቱና ጥልቀቱ እጅግ በጣም አደገኛ መሆኑ በአለም አቀፍ የመገናኛ አዉታሮች እየተነገረ ነዉ።

ዛሬ ኢትዮጵያ በየአመቱ ከ3 ቢሊዮን ዶላር በላይ የዉጭ ዕርዳታ ታገኛለች፤ በየአመቱ በቢሊዮን የሚቆጠር ዶላር ትበደራለች፤ ከ5 ቢሊዮን ዶላር በላይ የዉጭ ምንዛሪ በዉጭ አገር ከሚገኙ ዜጎቿ ታገኛለች። ኢትዮጵያ ዉስጥ ከፍተኛ የልማት ሰራዎች እንደሚሰሩ ይነገራል። ግድቦች፤ መንገዶች፤ ህንጻዎችና የኃይል ማስተላለፊያ መስመሮች ይገነባሉ እየተባለ ይነገራል። የኢትዮጵያ ኤኮኖሚ በአመት ከ10% በላይ እንደሚያድግ ይነገራል። ይህ ሁሉ ሆኖ ረሃብ በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠሩ ኢትዮጵያዉያንን ህይወት አደጋ ላይ ጥሏል። ለምን? ከህወሃት በፊት የነበሩት ሁለት መንግስታት በስልጣን ላይ በነበሩበት ግዜ ኢትዮጵያ ዉስጥ ለደረሰዉ ረሃብና በረሃብ ላለቁ ወገኖቻችን ተጠያቂዎች ነበሩ። ደርግና የቀዳማዊ ኃ/ሥላሤ ስርዐት የተከተሏቸዉ ብልሹ የሆኑ የኤኮኖሚ ፖሊሲዎችና ጎታች የመሬት ይዞታ አስተዳደር በሁለቱ ስርዐቶች ዉስጥ ለደረሰዉ ረሃብ አይነተኛ ምክንያቶች ነበሩ። ዛሬስ የሃያ ሚሊዮን ወገኖቻችንን ህይወት አደጋ ላይ ለጣለዉ ረሃብ ምክንያቱ ምንድነዉ? ተጠያቂዉስ ማነዉ? በነገራችን ላይ ህወሃት ሠላም አነገስኩባት በሚለዉ ኢትዮጵያ ዉስጥ ያለዉ ረሃብተኛ ቁጥር ላለፉት አምስት አመታት በእርስ በርስ ጦርነት በምትታመሰዉ ሦሪያ ዉስጥ ካለዉ ረሃብተኛ ቁጥር ይበልጣል።

የቀድሞዉ የኢትዮጵያ ጠ/ሚኒስቴር አቶ መለስ ዜናዊ የኢትዮጵያ ህዝብ በአጭር ግዜ ዉስጥ በቀን ሦስት ግዜ የመብላት ዋስትና ይኖረዋል ብለዉ ባዶ ተስፋ ከቀለቡን በኋላ የዘንድሮዉን አመት ጨምሮ እኛ ትዮጵያዉያን ሦስት ግዜ የረሃብ አደጋ ላይ ወድቀናል። ለመሆኑ ምን ይሆን ባለ ራዕዩ መሪ ያዩልን ራዕይ? በቀን ሦስት ግዜ መብላታችንን ወይስ ረሃብ ሦስት ግዜ እንደሚጎበኘን? ከአንድ አመት በፊት ክረምቱ መገባደጃ ላይ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ኢትዮጵያ ዉስጥ 6.5 ሚሊዮን ህዝብ የረሃብ አደጋ ይጠብቀዋል ብሎ ባስጠነቀቀ ማግስት ጠ/ሚ ኃ/ማሪያም ደሳለኝ ኢትዮጵያ በምግብ ምርት እራሷን የቻለች አገር ሆናለች ብለዉ ለአለም አወጁ። እንደ ፈረንጆቹ ዘመን አቆጣጠር በሰኔ 2015 ዓም እኚሁ ሰዉ ኢትዮጵያ ረሃብን በግማሽ እንደምትቀንስና በአመቱ ማለቂያ ላይ ኢትዮጵያ ዉስጥ ለረሃብ የሚጋለጠዉ ህዝብ ከ5% በታች እንደሚሆን አረጋገጡ። በተመድና በብዙ ለጋሽ አገሮች ጥናት መሠረት በ2015 ማለቂያ ላይ ከኢትዮጵያ ህዝብ 21% የሚሆነዉ አስቸኳይ የምግብ ዕርዳታ ካላገኘ ከፍተኛ አደጋ ይጠብቀዋል። ለምንድነዉ ኢትዮጵያ ዉስጥ መሪ ነን ተብዬዎች የኢትዮጵያን ህዝብ የማይጨበጥ ባዶ ተስፋ የሚቀልቡት? ለምንድነዉ ፈጣኑና ታዳጊዉ የአፍሪካ ኤኮኖሚ ለዜጎቹ የስራ ዕድል መፍጠር ተስኖት ወጣት ኢትዮጵያዉያን አገራቸዉን እየጣሉ የሚሰደዱት? ለምንድነዉ በቀን ሦስቴ ትበላላችሁ ተብለን አንዱም ያረረብን? ለምንድነዉ በምግብ እህል እራሳችንን ችለናል ተብሎ ተነግሮን መንፈቅ ሳይሞላ ረሃብ የሚጨፈጭፈን? ለምንድነዉ? . . . ለምንድነዉ? . . . ለምንድነዉ?

በቅርቡ CNN እና ኒዮርክ ታይምስን ጨምሮ አያሌ ታዋቂ የአለማችን መገናኛ አዉታሮች ኢትዮጵያ ዉስጥ እየመጣ ያለዉን አስፈሪ የድርቅ አደጋ መዘገብ ሲጀምሩ ጠ/ሚ ኃ/ማርያም ደሳለኝ ድርቅ ኢትዮጵያን ብቻ ሳይሆን አዉስትራሊያንና አሜሪካንን ጭምር እንዳስቸገረ ገልጸዉ ነበር። ይባስ ብለዉም “ኤልኒኖ” የተባለዉን የተፈጥሮ ክስተት ኢትዮጵያ ዉስጥ ለተከሰተዉ ድርቅ ተጠያቂ አድርገዋል። የሚገርመዉ ጠ/ሚ ኃ/ማሪያም ደሳለኝና መንግስታቸዉ ዛሬ ምግብ ካልሰጣችሁን በረሃብ ልናልቅ ነዉ እያሉ የሚወተዉቱት እንደ ኢትዮጵያ እነሱንም ድርቅ መቷቸዋል ያሉትን አሜሪካንና አዉስትራሊያን ነዉ። በነገራችን ላይ ጠ/ሚ ኃ/ማርያም ደሳለኝ ትክክል ናቸዉ – ድርቅ ኢትዮጵያ ዉስጥ እንደገባ ሁሉ አሜሪካና አዉስትራሊያ ዉስጥም ገብቷል፤ ኤልኒኖም ኢትዮጵያ ዉስጥ በተከሰተዉ የአየር ጸባይ መዛባት ላይ ተፅዕኖ ነበረዉ። ሆኖም እሳቸዉ ስራ ስለሚበዛባቸዉ ረስተዉ ሳይጠቅሱት ቀረ እንጂ ድርቅ ጎረቤት አገር ኬንያ፤ ሱዳንና ኤርትራ ዉስጥም ገብቷል። ጠ/ሚኒስትሩ የኮነኑት ኤልኒኖም ቢሆን ኤርትራንና ኬንያን ዘልሎ ኢትዮጵያ ዉስጥ ብቻ አልመጣም። ድርቅ ማለት ደግሞ ሌላ ትርጉም ካልተሰጠዉ በቀር የዝናብ እጥረት ማለት ነዉ። ዝናብ በተከታታይ ካልዘነበ ዬትም አገር ዉስጥ ድርቅ ይከሰታል። ነገር ግን ድርቅ ሁሉም አገር ዉስጥ ወደ ረሃብ አይለወጥም። ድርቅን አስመልክቶ በአገሮች መካከል ያለዉ ትልቁ ልዩነትም እዚህ ላይ ነዉ። አንዳንድ አገሮች ድርቅን በሩቁ ያዩና ዝግጅት አድርገዉ ረሃብን ይከላከላሉ፤ እንደ ኢትዮጵያ አይነቶቹ በልመና የተካኑ አገሮች ደግሞ ድርቁ ወደ ረሃብ እስኪለወጥ እጃቸዉን አጣጥፈዉ ይጠብቁና ህዝቡ ሲራብ አለም አቀፉን ህብረተሰብ “ስለ ማሪያም” ማለት ይጀምራሉ።

በቅርቡ ፕሮፌሰር መስፍን በግልጽ እንደተናገሩት አገራችን ኢትዮጵያ ክብሯንና ኩራቷን ለምዕራባዉያን አሳልፋ የሸጠች አገር ሆናለች። ምዕራባዉያንም በተለይ አሜሪካና ታላቋ ቢሪታኒያ ለዚህ በርካሽ ዋጋ ለገዙት ክብርና ልዕልና ሲሉ ኢትዮጵያን እንደ በኩር ልጃቸዉ በአንቀልባ ታቅፈዉ እሹሩሩ ሲሉ ከርመዋል፤ አሁንም እያሏት ነዉ። የአሜሪካዉ ባራክ ኦባማና የእንግሊዙ ዴቭድ ካምርን ባገኙት አጋጣሚ ሁሉ ኢትዮጵያን ሲጠቅሱ ተአምረኛዉ ኤኮኖሚ፤ በድርብ አኃዝ የሚያድገዉ ኤኮኖሚ ወይም የአፍሪካ ፈጣኑ ኤኮኖሚ እያሉ ነዉ። የህወሃት አገዛዝም ጧትና ማታ ስራዬ ብሎ የሚደክመዉ “ተዳጊዉ ኤኮኖሚ” ለመባል ነዉ እንጂ የ96 ሚሊዮን ኢትዮጵያዉያንን ህይወት ለመለወጥ አይደለም። ለዚህም ነዉ 15 አመት ሙሉ ፈጣን ዕድገት፤ ህዳሴ፤ ትራንስፎርሜሺን እየተባለ በተዘፈነባት አገር ዉስጥ ከ30 ሚሊዮን በላይ ዜጎች (ከጠቅላላዉ ህዝብ 1/3ኛዉ) በቀን የተመድ የድህነት መመዘኛ ከሆነዉ ከ$1.25 በታች እያገኘ በድህነት የሚማቅቀዉ።ግሎባል ፖስት የተባለ የዜና ማዕከል በቅርቡ ኢትዮጵያ በ30 አመት ዉስጥ ታይቶ የማይታወቅ የረሃብ አደጋ ዉስጥ ወድቃለች ካለ በኋላ ለመሆኑ ይንንን አደጋ የኢትዮጵያ መንግስት መቋቋም ይችላል ወይ ሲል ጠይቋል። ይህንን ጥያቄ ለመመለስ የኢትዮጵያ መንግስት ቅድሚያ የሚሰጠዉ ለምንድነዉ የሚለዉን ጥያቄ መመለሱ የሚበቃ ይመስለኛል። የህወሃት አገዛዝ አይን ላወጣ ዘረፋና ለሜዲያ ፍጆታ በሚያመቹ ፕሮጅክቶች ላይ ካማተኮሩ በፊት ቅድሚያ የሚሰጠዉ የኢትዮጵያን ህዝብ ክብር ለመጠበቅ፤ የኢትዮጵያን ህዘብ ልመና ይዞት ከሚመጣዉ ዉርደትና የሂሊና ዝቅጠት ለማዉጣትና ረሃብን ከአገራችን ምድር ለማጥፋት ቢሆን ኖሮ ረሃብ ከኢትዮጵያ የሚጠፋዉ ዛሬ ሳይሆን ህወሃት የኢትዮጵያን በትረ ስልጣን በተቆጣጠረባቸዉ በመጀመሪያዎቹ አምስት አመታት ዉስጥ ይሆን ነበር።

The Famine Early Warning Systems Network (FEWS Net) የተባለ ድርጅት ኢትዮጵያ ዉስጥ የምግብ እህል ምርት ከሚጠበቀዉ በታች መሆኑን ወይም ይመረታል ተብሎ የሚጠበቀዉ ምርት አገሪቱ ከሚያስፈልጋት የምርት መጠን እጅግ በጣም ያነሰ መሆኑን በግዜ አስጠንቅቆ ነበር። ለመሆኑ ለዚህ ማስጠንቀቂያ የኢትዮጵያ መንግስት የሰጠዉ ምላሽ ምን ነበር? እርግጠኛ ነኝ FEWS Net ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን በአካባቢዉ ድርቅ ለሚያዘወትርባቸዉ አገሮች መንግስታትም የድርቅ አደጋን አስመልክቶ ማስጠንቀቂያ ይሰጣል። ሌሎች መንግስታት ለዚህ ማስጠንቀቂያ የሰጡት ምላሽ ምን ይሆን? የኢትዮጵያ መንግስትስ በራሱም ቢሆን እንዲህ አይነቱን በዝናብ እጥረትና በአየር ሁኔታ መለዋወጥ የተነሳ ሊከሰት የሚችለዉን የምግብ እጥረት ከግምት ዉስጥ ያስገባ ጥናት በየአመቱ ማካሄድ አይገባዉም ነበር?

በ1977 ዓም በአገራችን ታሪክ ታይቶ የማይታወቅ ረሃብ ትግራይ፤ ወሎና ሰሜን ሸዋ ዉስጥ የሰዉን ልጅ እንደ ቅጠል ሲያረግፍ የዚህ ጸሁፍ ፀሀፊ የሰሜን ኢትዮጵያ ፕላን ቀጣና ጽ/ቤትን ወክሎ ትግራይ ዉስጥ ይሰራ ነበር። በወቅቱ የትግራይ ጎረቤት ክፍለሀገር በነበረችዉ ኤርትራ ዉስጥ ድርቅ ቢኖርም ረሃብ የሚባል ነገር አልነበረም። ዛሬ ኢትዮጵያና ኤርትራ ሁለት የተለያዩ አገሮች ከሆኑ ሩብ ምዕተ አመት ሊሆን በወራት የሚቆጠር ግዜ ነዉ የሚቀረዉ። አንድ ነገር ግን ዛሬም አልተለወጠም። ኢትዮጵያና ኤርትራ ዉስጥ ዛሬም ድርቅ አለ፤ ኢትዮጵያ ዉስጥ ድርቁ ዛሬም ወደ ረሃብ ተለዉጦ የሚሊዮኖችን ህይወት አደጋ ላይ ጥሏል። ኤርትራ ዉስጥ ግን ድርቅ ቢኖርም ድርቁ ወደ ረሃብ አልተለወጠም፤ ወይም የኤርትራ መንግስት እንደ ኢትዮጵያ መንግሰት ለአለም አቀፉ ህብረተሰብ የምግብ ያለህ የሚል የልመና ጥሪ አላቀረበም። ለምን?

ኤርትራ የምዕራቡ አለም በተለይ የአሜሪካ መንግስት የማይገባ ማዕቀብ ጥሎባት ከዉጭ አገር ቤሳ ቤስቲን የማታገኝ አገር ናት። ኢትዮጳያ ግን በጥቁር አለም ዉስጥ ከፍተኛዉን የዉጭ ዕርዳታ የምታገኛ አገር ናት። የኤርትራ ኤኮኖሚ የራሱ በሆነ መንገድ እያደገ ቢሆንም በአሜሪካ የሚመራዉ የምዕራቡ አለም ይህንን ዕድገት መመስከር አይፈልግም። የኤርትራ መንግስትም ቢሆን እንደ ወያኔ በነጋ በጠባ አደግን እያለ ጥሩምባ አይነፋም። ኤርትራ አንድም አመቱን ሙሉ የሚፈስ ወንዝ የሌለባት አገር ናት፤ ኢትዮጵያ የአፍሪካ የወንዞች ማማ ተብላ የምትጠራ አገር ናት። ኤርትራ ዉስጥ አንድም ሐይቅ የለም፤ ኢትዮጵያ ዉስጥ ግን የሀይቁን ብዛት መቁጠር ያዳግታል። ኢትዮጵያ ያላት የእርሻ መሬት ስፋቱ ከጠቅላላዉ ኤርትራ የቆዳ ስፋት እጅግ በጣም ይበልጣል። የቀድሞዉ የወያኔዉ ጠ/ሚኒስቴር በቀን ሦስቴ እንበላለን ብሎ ትንቢት ነግሮን ነበር፤ ይህ ትንቢት ሳይፈጸም ነበር እሱን የተካዉ ሰዉ ከዛሬ ወዲህ በምግብ እህል እራሳችንን ችለናል ብሎ ለአለም ህዝብ ያወጀዉ። የኤርትራ መንግስት በእንደነዚህ አይነት ተራ የሜዲያ ፍጆታዎች ግዜዉን ሲያጠፋ አናይም። ለአገሩ ህዝብ የሚያስፈልገዉን የምግብ ፍጆታ አሟልቶ አገሩን ከረሃብ አደጋ ሲከላከል የምናየዉ ግን የኤርትራ መንግስት ነዉ። እነዚህን በሁለቱ አገሮች መካካል የሚታዩትን ልዩነቶች ያነበበ ሰዉ ሁሉ አንድ ሊገነዘበዉ የሚገባ ትልቅ ሀቅ አለ። እሱም ኢትዮጵያ ዉስጥ በመንግስት ብልሹ የኤኮኖሚና የፖለቲካ ፖሊሲ የተነሳ ድርቁ ወደ ረሃብ ተለዉጦ በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎችን ህይወት አደጋ ላይ ጥሏል። የኤርትራ መንግስት ግን የድርቁን መምጣት አስቀድሞ ስለተገነዘበ እርምጃ በመዉሰዱ ኤርትራ ዉስጥ የገባዉ ድርቅ ወደ ረሃብ አልተለወጠም። በመሆኑም ዛሬ ኤርትራ ዉስጥ ረሃብ የለም። ኤርትራ ዉስጥ ድርቁ ወደ ረሃብ አለመለወጡ የሚያሳየን ኤርትራዉያን ልዩ ፍጡሮቸ መሆናቸዉን ሳይሆን የሁለቱ አገር መንግስታት ቅድሚያ የሚሰጡት ለምን እንደሆነና በሁለቱ መንግስታት መካክል ያለዉን ከፍተኛ የፖሊሲ ልዩነት ነዉ። ወያኔ የሚያጮኸዉ የድርብ አኃዝ ዕድገትና የህዳሴ ጩኸት ከቅርብም ከሩቅም ይሰማል። በኤርትራና በኢትዮጵያ መንግስታት መካከል በምግብ ራስን መቻልን አስመልክቶ የሚታየዉ ከፍተኛ የፖሊሲ ልዩነት ግን በቀላሉ አይታይም። ኤርትራ ላይ የተጣለዉ ማዕቀብ እንዳይነሳ የሚፈልጉት አሜሪካኖችማ በተለይ እነ ሱዛን ራይስን የመሳሰሉ የአዕምሮ አይነስዉራን ይህንን ልዩነት ቢታይም ማየት አይፈልጉም።

ድርቅ ድንበር አይልም፤የፖለቲካ ስርዐት አይልም፤ ደሃና ሀብታም አይለይም- አገር ከአገር ህዝብ ከህዝብ አይለይም። ድርቅ በዬትም አገር ዉስጥ በማንኛዉም ግዜ ሊከሰት የሚችል የተፈጥሮ ክስተት ነዉ። የሰዉ ልጅ ድርቅ ይዟቸዉ ሊመጣ የሚችለዉን አደጋዎች ነዉ መቆጣጠር የሚችለዉ እንጂ ድርቅን እራሱን መቆጣጠር አይችልም። ዝናብ በተከታታይ ከጠፋ ድርቅ መምጣቱ አይቀሬ ነዉ። በ2007 ዓም ኢትዮጵያ ዉስጥ የገባዉ ድርቅ ኤርትራ ዉስጥም ገብቷል። ሁለቱ አገሮች የዝናቡ እጥረት ወደ ድርቅ ከመለወጡ በፊትና በኋላ የወሰዷቸዉ እርምጃዎች ግን የሰማይና የምድርን ያክል የተራራቁ ናቸዉ። እነዚህ ሁለቱ አገሮች የወሰዷቸዉ የተለያዩ እርምጃዎች ናቸዉ ዛሬ ኢትዮጵያን የምግብ ለማኝ ኤርትራን ደግሞ በራሷ የምትተማመን አገር ያደረገዉ።

የኢትዮጵያ መንግስት ድርቅ እየመጣብህ ነዉ ተብሎ ማስጠንቀቂያ እየተሰጠዉ ትኩረት የሰጠዉ እየመጣ ላለዉ ረሃብ ሳይሆን ለ“እዩኝ እዩኝ” ፕሮጅክቶች ነዉ። ፕሮጀክቶች አያስፈልጉንም ማለቴ አይደለም። ያስፈልጉናል፤ ነገር ግን የኢትዮጵያ ህዝብ በረሃብ እያለቀ ደርግ አዳራሽ ይሰራል ብሎ የወነጀለ አካል የሱም ትኩረት በመጀመሪያ የህዝብን የምግብ ፍላጎት መሟላት እንጂ ህዘብ በረሃብ እያለቀ ሌላ ሌላ ፕሮጀክት ላይ ማተኮር አልነበረበትም። የኤርትራ መንግስት የ2007 ዓም ዝናብ መጠን የእህል አምራች በሆኑ የአገሪቱ አካባቢዎች አስተማማኝ አለመሆኑን ሲረዳ ገና ከጧቱ ነበር ከተለያዩ ምንጮች የምግብ እህል በግዢ በማሰባሰብ የአገሪቱን የምግብ ፍላጎት ማሟላት የጀመረዉ። ዛሬ የኤርትራ ህዝብ ስሙ በረሃብ የማይነሳዉ ኤርትራ ዉስጥ ድርቅ ስላልገባ አይደለም። የኤርትራ መሪዎች ድርቁ ወደ ረሃብ ከመለወጡ በፊት ቀድመዉ የወሰዱት እርምጃ አገራቸዉን ከረሃብ አደጋ ስላዳነዉ ነዉ። የኛ መንግስታት ግን ንጉሱም ሆኑ፤ ደርግ ወይም ወያኔ ድርቅ ወደ ረሃብ ተለዉጦ ህዝብን ሲጨርስ ምግብ መለመን ነዉ እንጂ ዛሬ ትንሿ አገር ኤርትራ እንዳደረገችዉ የድርቅን መምጣት አይተዉ ረሃብን ተከላክለዉ አያዉቁም። ለዚህ ነዉ መሰለኝ ኢትዮጵያ ዉስጥ በድርቅና በረሃብ መካከል ልዩነት ያለም አይመስልም።

እዉነትን ማሞጋገስና በዉሸት አለቆች ሰትደፈጠጥ ደጋግፎ ማቆም እስትንፋሴ እስካለች ድረስ በፍጹም የማልተወዉ ቋሚ ስራዬ ቢሆንም የዚህ ጽሁፍ አላማ ግን የኤርትራን መንግስት ማሞጋገስ አይደለም። እሱ የኤርትራዉያን ስራ ነዉ። የዚህ ጽሁፍ ብቸኛ አላማ ኢትዮጵያ ዉስጥ ዛሬ የ20 ሚሊዮን ዜጎችን ህይወት አደጋ ላይ የጣለዉ ረሃብ መንስኤዉ የዝናብ እጥረት ሳይሆን የኢትዮጵያን ህዝብ ፍላጎት ቅደም ተከተሎች ያላስተዋለ ብልሹ የመንግስት ፖሊሲ ዉጤት መሆኑን ለማሳየት ነዉ። ይህና ይህ ብቻ ነዉ የዚህ ጽሁፍ አላማ። ቸር ይግጠመን።

ኤፍሬም ነኝ ከአርበኞች መንደር
ebini23@yahoo.com

መንግስት በርሃብ ለተጠቁት ዜጎች እርዳታ እየሰጠ እንዳልሆነ ታወቀ

• በርሃብ የተጠቁት ዜጎች ቀያቸውን ለቀው እየተሰደዱ ነው
• ‹‹ሰው በርሃብ እያለቀ ነው››
• ‹‹የሚላስ የሚቀመስ የለም፡፡ ቤተሰባችን ፈርሷል››
• ‹‹እርዳታ ቢሰጥማ ከዚህ ድረስ አንመጣም ነበር፡፡››

 ነገረ ኢትዮጵያ

መንግስት በርሃብ ለተጎዱት ዜጎች እርዳታ እየሰጠ እንዳልሆነ ቀያቸውን ለቀው አዲስ አበባ የገቡት የርሃቡ ሰለባዎች ለነገረ ኢትዮጵያ ገልፀዋል፡፡ ከወሎ የተለያዩ አካባቢዎች በርሃብ የተጠቁ ዜጎች ህይወታቸውን ለማትረፍ ወሎ ውስጥ ከሚገኙት ከተሞች አልፈው ወደ ጎጃም፣ ጎንደርን እንዲሁም አዲስ አበባ እየተሰደዱ ሲሆን አዲስ አበባ በርካታ ተጎጅዎች ህፃናትን አዝለው እየለመኑ ይገኛሉ፡፡ የነገረ ኢትዮጵያ ሪፖርተር ካነጋገራቸው መካከል ሁሉም መንግስት ለርሃቡ ተጎጅዎች እርዳታ እየሰጠ እንዳልሆነ ገልፀዋል፡፡ ቤተሰቦቻቸውና ጎረቤቶቻቸውም እንደነሱ ቀያቸውን ጥለው ወደ መተማ፣ ሁመራ፣ ባህርዳር፣ ደሴ፣ እንዲሁም ወደ አዲስ አበባ መሰደዳቸውን በሀዘን ገልፀዋል፡፡

ወሎ ውስጥ ጮሬ ሶዶማ ከተባለ ቦታ ተነስታ እንደመጣች፣ አዲስ አበባ ከገባች ሶስት ሳምንት እንደሆናት የገለፀችውና ሁለት ህፃናትን ይዛ ስትለምን ያገኘናት፤ በግምት በ30ዎቹ መጨረሻ ዕድሜ የምትገኝ እናት ‹‹የመጣነው የሚላስ የሚቀመስ ስለሌለ ነው፡፡ ከብቶቻችን አልቀዋል፡፡ አዝመራ የሚባል የለም፡፡ ሰው በርሃብ እያለቀ ነው፡፡ እኛ ሴቶቹ ወደ ከተማው ስንመጣ ወንዶቹ ደግሞ ወደ ሁመራና መተማ ሄደዋል፡፡ እኛም ከዚህ የመጣነው ጉልበት ስላለን ነው፡፡ አብዛኛዎቹ ደካሞች በዛው አካባቢ ቀርተዋል፡፡›› ስትል በሀዘን ገልፃልናለች፡፡ መንግስት እርዳታ አይሰጥም ወይ ብለን ላነሳንላት ጥያቄም ‹‹ምንም እርዳታ አልተሰጠንም፡፡ እርዳታ ቢሰጥ ኖሮ ቤታችን ጥለን አንመጣም ነበር፡፡ ባያበቅልም መሬት አለን፡፡ የከተማው ሰው ይሻላል ብለን ነው ወደዚህ የመጣነው›› ስትል ስለ ርሃቡ አስከፊነትና መንግስትም እርዳታ እየተሰጠ እንዳልሆነ ገልፃልናለች፡፡

ባለቤቷ ወደ መታማ ሲሄድ እሷም ቤቷን ጥላ ወደማታውቀው አዲስ አበባ እየጠየቀች እንደመጣች የገለፀችልን ወጣት በበኩሏ ‹‹ቤቴ ተፈትቷል፡፡ ባለፈው አመት ከብቶችም እህልም ነበረን፡፡ ዘንድሮ ግን ምንም ነገር የለም፡፡ ጊዜው ከፍቷል፡፡ ባሌ ወደ መተማ ሄዷል፡፡ እኔም ልጄን አዝዬ እስከ ደሴ በእግሬ መጣሁ፡፡ ከዛ በኋላ እየለምንኩ ከዚህ ደርሻለሁ፡፡ ማንም እርዳታ አልሰጠንም፡፡›› ስትል ስለሁኔታው ገለፃልናለች፡፡

ከመርሳ ወረዳ እንደመጡ የገለፁልንና ከልጃቸው ልጅ ጋር እየለመኑ ያገኘናቸው የ65 አመት አዛውንት በበኩላቸው ‹‹ዝናቡ ሲቀር ከብቶቻችንም ሞቱ፡፡ አዝመራ የሚባልም ነገር የለም፡፡ ከመርሳ ደሴ እየለመንኩ መጣሁ፡፡ ደሴም እንደኛ ብዙ ሰው አለ፡፡ አገኝ ብሎ በየከተማው ተሰራጭቷል፡፡ ወደዚህ ይሻላል ብዬ በለመንኳት ተሳፍሬ መጣሁ፡፡ ርሃቡ ሲብስብን ወደማናውቀው አገር መጣን፡፡›› ሲሉ የርሃቡን አስከፉነት ገልፀውልናል፡፡

‹‹እርዱኝ!›› እያሉ እየለመኑ ያገኘናቸው ከኬሚሴ አካባቢ እንደመጡና ከ8 ቀን በፊት አዲስ አበባ እንደደረሱ የገለፁልን ሌላኛዋ እናትም ቤታቸውን ጥለው እንደመጡና፣ ሌሎች ቤተሰቦቻቸው ወደ የት እንደሄዱ እንኳን እንደማያውቁ ለነገረ ኢትዮጵያ ገልፀዋል፡፡ መንግስት እርዳታ እየሰጠሁ ነው እንደሚል ስንገልፅላቸው ‹‹ለእኔ አልደረሰኝም፡፡ እርዳታ ተሰጠኝ ያለም አልሰማሁም፡፡ እርዳታ ቢሰጥማ ከዚህ ድረስ አልመጣም ነበር፡፡ አሁን ነው ከከተማው ሰው ትንሽ ትንሽ እያገኘን ያለነው፡፡ በየ ከተማው ስንደርስ ሰው አይነፍገንም›› ሲሉ ከህዝብ እንጅ ከመንግስት እርዳታ እንዳላገኙ ገልፀዋል፡፡

ካሳንቺስ አካባቢ ልጅ አዝለው ታክሲ ተሳፋሪዎችን ምንም አይነት ቃል ሳያሰሙ ልጃቸውን በመዘርጋት ብቻ እንዲረዷቸው እየጠየቁ ያገኘናቸው እናትም የራሳቸውንና የታዘለውን ልጅ ነፍስ ለማዳን ቀያቸውን ጥለው ወደ አዲስ አበባ መምጣታቸውን ለነገረ ኢትዮጵያ ገልፀዋል፡፡

የርሃቡ ተጎጅዎች አዲስ አበባ ውስጥም ነፍሳቸውን ለማቆየት በጠራራ ፀሀይ ሲለምኑ እንደሚውሉና ምቹ ያልሆነ ቦታ አንድ ላይ የሚያድሩ በመሆኑ ልጆቻቸው ለበሽታ እየተጋለጡ እንደሆነ ገልፀዋል፡፡ ተማሪ የነበሩና በርሃቡ ምክንያት ለማቋረጥ የተገደዱት ልጆቻቸው ከእነሱ ጋር ወይንም ወደ ሌላ አካባቢ ነፍሳቸውን ለመዳን መሰደዳቸውን፣ በያለፉበት ከተማም በርካታ ስደተኛ እንዳለም ለነገረ ኢትዮጵያ ገልፀዋል፡፡

Wednesday, 4 November 2015

የታማኝ እዳ (እንግዳ ታደሰ)

እንግዳ ታደሰ – ኦስሎ
በቃል የምነት እዳ ሸክፎ ሸክሙን
እንደ ሴባስቶፖል ሽቅብ ቁልቁለቱን
ሲወጣና ሲወርድ ቋጥኝ አቀበቱን
እስቲ እንካፈለው የሃገር እዳውን ፡፡

Ethiopian activist Tamagne Beyene

እዳው በግል የናት አባት እዳ አይደለም ፡፡ የርሱ እዳ የዕምነቱ እዳ ነው ፡፡ ለሸክም የከበደ ፥ የሰው ፊት የሚያስገርፍ፥ ዕረፍት የሚነሳ ፥ ከወለዳቸውና ከሚወዳቸው ቤተሰቡ ለወራት የሚያቆራርጥ፣ እንደ አጼ ቴዎድሮስ መድፍ ሴባስቶፖል ሽቅብና ቁልቁል የሚያስሮጥ፣ ኢሳትን በግሩ ለማቆሞ የሚደረግ ትግል ፡፡

ይህ ሰው በህወሃት ቀንበር ሥር ተሸብቦ ድምጹ የታፈነውን የዘጠና ሚልዮን ህዝብ መከራና እዳ ብቻውን የተሸከመ እስኪመስል ከምድር ጫፍ ሰሜን ዋልታ ኖርዌይ ፣ እስከምድር ግርጌ ደቡብ አፍሪቃ ፥ ከዚያም አውስትራልያ ረጅም የጢያራ ጉዞ በማድረግ ኢሳት በባለቢሊዬኖሮቹ የህወሃት ቱጃሮችና ረዳት ከበርቴዎቻቸው እንዳይዘጋ የሰው ፊት እያሳቀቀው ምጽዋት ሲለምን ይታያል፡፡ በርግጥ ከጎኑ የቆሙ ቆራጥ ወገኖቹ ቢኖሩም ፣ ዳገቱን ሲያዘግም የብርታት ከዘራ የሚያቀብሉት ወገኖች ባይጠፉም፣ በዚያው አንጻር ደግሞ ምክንያት በሌለው ጥላቻ የሚጎንጡትም አልጠፉም ፡፡

ምናልባት ከአህጉር ፥ አህጉር ለርዳታ ሲዘዋወር ፣ የደላው የሚመስላቸው ሰዎች ሊኖሩ ይችላሉ ፡፡ አድካሚውንና እጅግም ሲበዛ ለበሽታ አሳልፎ የሚሰጠውን ረጅም ሰዓታት የአውሮፕላን ጉዞ ከግምት ውስጥ ያላስገቡ ተቺዎች የሚሰነዝሩት ባዶ አስተያየት እና የህወሃት ጭፍሮች ጥላቻም ጭምር እንደሆነ የታወቀ ነው ፡፡ የአባት ቅርብ ክትትልን የሚጠይቀውን ፥ በትምህርት ቤት ልጆች የሚሰጣቸውን የቤት ሥራና ከወላጆች ማግኘት የሚገባቸውን እርዳታን ፍቅር በአባት እምነት እዳ ምክንያት በቅርብ የሚያጡትን ልጆቹንም ማሰብ በተገባ ነበር ፡፡ ትልቁን የጋራ የቤተሰብ ኃላፊነት ታማኝ ለወራት የኢሳትን ዓላማ ለማሳካት ሲደክም ፣ እናትም ፥ አባትም ሆና በአሜሪካን አገር ኑሮና ፥ አስቸጋሪ የደህንነት ዋስትና በተመናመነባት አሜሪካ የምትንገላታውንም ውድ ባለቤቱንም ማሰብ ባስፈለገም ነበር ፡፡ በርግጥ ታማኝ ከህወሃት ሰዎችና ደጋፊዎቻቸው ይህን ነቀፋ ስለሚጠብቅ ብዙ የሚያሳስበው ጉዳይ አይደለም ፡፡ ይህ እዳ የታማኝ በየነ ፥ ይህ እዳ የሻምበል በላይነህ ፥ ይህ እዳ የአበበ ገላው ፥ ይህ እዳ የኤርምያስ ለገሰ ወዘተ እዳ ብቻ አይደለም ፡፡ ድምጹ የተሸበበት የዘጠና ሚልዮን ህዝብ እዳ ነው ፡፡

ኢትዮጵያ ከዘረኞችና ከባንዳዎች ነጻ ስትወጣ ፣ ሁሉም በነጻነት ወደ እናት ምድሩ ሲተም ፣ በእናት አገሩም ህይወቴና ሞቴ ከርሷ ይሁን ብሎ መኖር ሲጀምር ፣ ታማኝም እንደማንኛውም ዜጋ ነው አየሯን በነጻነት የሚስበው ፡፡ ለርሱ ለብቻው አየር አይጠለፍለትም ፡፡ ለርሱ አገሪቱ ለመጠጥ ከምታቀርበው የለገዳዲም ሆነ የገፈርሳ ውሃ ውጭ ልዩ የመጠጥ ውሃ ጅረት ለብቻው አትጠልፍለትም ፡፡ ይህ እንኳ እየተሰማ ያለው ፣ ከገዥዎቻችን መንደር ብቻ ነው ፡፡ ዛሬ ሰፈሬን በባለስልጣን ሰፈር ያድርገው እየተባለ እንደሚለመነው ፣ የህወሃት ባለስልጣኖች ካሉበት መንደር መብራትም ሆነ ዉሃ በፍጹም እንደማይጠፋ ስንቶቻችን ነን የምናውቀው ? ለሃጣን በመጣ መብራትና ዉሃ በአክባቢው ያሉ ሰዎች እየበራላቸውም እየጠጡም ነው ፡፡

በኪነ ጥበቡ ዓለም የሚገኘው ሃብት የተሻለ ነው ፡፡ ዓለምን በመዞር ከሆነ ኪነጥበቡም ያዞራል ፡፡ ብብት ሳይኮረኩሩ አስቆ ሃብት በመሃረብ ሊቋጠር ይችላል ፡፡ ለአገር ነጻነትና ትንሳኤ ኢሳትን በግሩ እናቁም ተብሎ ለልመና ሲወጣ ግን የሰው ፊት ይገርፋል ፡፡ ታማኝ ባለፈው ሳምንት ኦስሎ ውስጥ በተደረገው አኩሪ የኢሳት አምስተኛ ዓመት ክብረ በዓል ዕለት እርሱም ልክ እንደፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ ፣ ከንግዲህ ህዝብ ሰብስቤ አዋጡ አልልም ፡፡ በጋራ ሽክሙን ብንካፈል ወደ ነጻነት ያደርሰናል ፡፡ አናዋጣም ግን የሚሉ ካሉ አይስጉ ! የቆረጡ ሃብታቸውን አሟጠው እስከመጨረሻው የሚረዱ ቆራጥ ዜጎች አሉ ሲል እድምተኛው ረጅም ደቂቃ በቆየ ጭብጨባ ነበር ድጋፉን ያሳየው ፡፡

ታማኝ በተገኘበት ሥፍራ የሚነቅፉትን የሃሳብ ድኩማኖች አንስቶ ሲተች አልተሰማም ፡፡ ይልቅስ ወደላኳቸው አለቆቻቸው ነው በተጨባጭና በማስረጃ ያሰማሯቸው ከለቀቁት ፊልም ተነስቶ ባገናዛቢ መልኩ ራሳቸውን ሲሞግታቸው የሚስተዋለው ፡፡ እንደመሰለኝ ታማኝ መለመን ደክሞታል ፡፡ ኢሳት የህዝብ ዓይንና ጆሮ ሆኖ እንዲቀጥል እዳው መሆን ያለበት ወደ ነጻነት ናፋቂው ህዝብ ትከሻ ባስተማማኝ መልኩ እንዲሸጋገር ነው ፡፡ከዚህ በተረፈ ወዳጃችን ታማኝ የሚፈራው ታላቁ እስክንድር እንዳለው ፣ በአንበሳ ፊት አውራሪነት የመጣን የበግ መንጋን ሠራዊት እንጂ፣ በጠቦት በግ ፊት አውራሪነት የመጣን የአንበሳን ሠራዊት አይደለም የሚፈራው፡፡

I am not afraid of an army of lions led by a sheep; I am afraid of an army of sheep led by a lion.

Tuesday, 3 November 2015

ለጥቅምት 22 ሰማዕታት የመታሰቢያ ፕሮግራም ተካሄደ

በነገረ ኢትዮጵያ ሪፖርተር

ምርጫ 1997 ዓ.ምን ተከትሎ ጥቅምት 22/1998 ዓ.ም በወቅቱ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ቀጥታ ትዕዛዝ በ‹‹ፀጥታ ሀይሎች›› በጭቃኔ ለተገደሉት ሰማዕታት እና ለቆሰሉት ኢትዮጵያውያን በሰማያዊ ፓርቲ ፅ/ቤት መታሰቢያ ተደረገ፡፡ የፕሮግራሙ ተሳታፊዎች ጥቅምት 22/1998 ዓ.ም በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች የገጠማቸውን በተለይም ኢትዮጵያውያን ሲገደሉ ያዩትንና የራሳቸውን ገጠመኝም አካፍለዋል፡፡

የፕሮግራሙ ተሳታፊዎቹ የተገደሉትን በክብር መቅበር እንዳልቻሉ እና ታፍሰው በተለያዩ እስር ቤቶች መታሰራቸውን አስታውሰዋል፡፡ አዛውንቶችንና ህፃናትን በጭካኔ ተገድለው ባንክ ሊዘርፉ ነው የተባለበትና የሥርዓቱን የህግና ሞራል የማይገድበው መሆኑን ያሳየበት ነውም ብለዋል፡፡ ሥርዓቱ ካለፈው ስህተቱ ሳይማር ዛሬም ለመግደል ዝግጁ እንደሆነ መቀጠሉንም ገልፀዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት ሥርዓቱ ወደ ባሰ አምባገነንነት በመግባቱም ትግሉን መቀላቀላቸውን ገልፀው፣ ዘላቂው አማራጭ የሰማዕታቱን የትግል መንፈስ ፅናት ይዞ መታገል ነው ብለዋል፡፡ እነሱ አላማ ያደረጉትን ተጉዘው በአንድነት የኢትዮጵያን እጣ ፋንታ መወሰን እንደሚገባቸውም ገልፀዋል፡፡

የሰማያዊ ፓርቲ ሊቀመንበር ኢ/ር ይልቃል ጌትነት በ1997 ዓ.ም በኋላ የሥርዓቱ ሁኔታ እየተባባሰ እንደመጣና ለዚህም ዋናው ምክንያት ኢትዮጵያውያን ሥርዓቱ የሚያደርስብንን በደል ችለን ወደ ውስጥ የምናለቅስ መሆናችን ነው ብለዋል፡፡ ሥርዓቱ ይቅር የማይደረግለት ሆኖ፣ ፖለቲካው በመነታረክ መቀጠሉን ትክክል እንዳልሆነም ገልፀዋል፡፡

‹‹ሥርዓቱ ታሪክና የጋራ ነገር የላችሁም ብሎናል፡፡ መናናቅንና ሀይማኖትን ማቃለልን በተግባር አሳይቶናል፡፡ የወደፊት ኢትዮጵያ በእኛ እጅ እንድትሆን ከፈለግን የነበረውን የሀገራችን እሴት ማናናቅ የለብንም፡፡›› ያሉት ኢ/ር ይልቃል ኢትዮጵያውያን የገነቧቸው እሴቶች ሁሉ በወጣቱ ልብ ውስጥ ማደር እንዳለባቸው፣ ሰማዕታቱ የሞቱለት አላማና ኢትዮጵያውያን የገነቡት እሴት መጠበቅ እንዳለበት አሳስበዋል፡፡

Sunday, 1 November 2015

ኢትዮጵያ የኢንተርኔት ነጻነትን ክፉኛ ከሚገድቡ አገራት አንዷ ናት ተባለ

    
በኢንተርኔት ነጻነት ከ12 የአፍሪካ አገራት የመጨረሻውን ደረጃ ይዛለች ቻይና የኢንተርኔት ነጻነት በመገደብ 1ኛ ናት 

የኢንተርኔት ነጻነት በአለማቀፍ ደረጃ ለአምስት ተከታታይ አመታት እያሽቆለቆለ እንደሚገኝና ኢትዮጵያም የኢንተርኔት ነጻነት ከሌለባቸው የአለማችን አገራት አንዷ መሆኗን “ፍሪደም ሃውስ” የተባለው አለማቀፍ ተቋም ሰሞኑን ባወጣው አመታዊ ሪፖርት አስታወቀ፡፡ተቋሙ በ65 የአለማችን አገራት ላይ ያካሄደው የ2015 የኢንተርኔት ነጻነት ጥናት ሪፖርት፣ ከአለማችን አገራት የከፋ የኢንተርኔት ነጻነት የተንሰራፋባት ቻይና መሆኗን ጠቁሞ፣ ጥናቱ ካካተታቸው 12 የአፍሪካ አገራት መካከልም ኢትዮጵያ በኢንተርኔት ነጻነት የመጨረሻውን ደረጃ ትይዛለች ብሏል፡፡

2.9 በመቶ የኢንተርኔት አገልግሎት ሽፋን ባለባት ኢትዮጵያ፣ የማህበራዊ ድረ ገጾችና የኢንፎርሜሽን ኮሙኒኬሽን ቴክኖሎጂ አፕሊኬሽኖች እንዲሁም ፖለቲካዊና ማህበራዊ ይዘት ያላቸው ጽሁፎች ይታገዳሉ፣ ጦማርያንና የኢንፎርሜሽን ኮሙኒኬሽን ተጠቃሚዎችም ይታሰራሉ፣ ፕሬሱም ነጻ አይደለም ብሏል፡፡

በአገሪቱ የኢንተርኔት አቅርቦትና ተደራሽነት ችግሮች እንዳሉ የጠቆመው ሪፖርቱ፣ የአገልግሎት መቆራረጥና አዝጋሚነት በስፋት እንደሚያጋጥምና በአይሲቲው ዘርፍ ለሚሰማሩ ገለልተኛ ተቋማትና ስራ ፈጣሪዎች የሚሰጠው ዕድልም እጅግ ውስን ነው ብሏል፡፡የ2007 አገራዊ ምርጫ መቃረቡን ተከትሎ በርካታ ተጽዕኖ ፈጣሪ ዜናዎች እንዳይሰራጩ ታግደዋል፣ የተቃዋሚ ፓርቲዎች ድረገጾችም አገልግሎት እንዳይሰጡ ተደርገዋል ያለው ሪፖርቱ፤ ከ100 በላይ ድረገጾችም አሁንም ድረስ ታግደዋል፤ መንግስት በኢንተርኔትና በሞባይል በሚደረጉ ግንኙነቶች ላይ የሚያደርገውን ክትትልና ስለላ አጠናክሮ ቀጥሏል ብሏል፡፡

መንግሥት በበኩሉ ከተቃዋሚ ፓርቲዎች የሚሰነዘሩ ተመሳሳይ ትችቶችን ማስተባበሉ ይታወቃል፡፡ የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለስልጣን በቅርቡ እንደገለፀው፤ የኢንተርኔት ስርጭትና አጠቃቀምን ለመቆጣጠር የሚያስችል ህግ ይፀድቃል፡፡

ኢትዮጵያ በርካታ ጋዜጠኞችን በማሰር ቀዳሚ ከሆኑት የአለማችን አምስት አገራት አንዷ ናት ያለው ሪፖርቱ፣ ከ2014 እስከ 2015 ባለው ጊዜም፣ መንግስት ሃሳባቸውን በገለጹ ጦማርያንና በድረገጽ ጋዜጠኞች ላይ የሚያደርሰውን እንግልትና እስራት አጠናክሮ ቀጥሏል ሲል ገልጿል፡፡የ2015 የኢንተርኔት ነጻነት ሪፖርት እንደሚለው፤ ጥናት ከተደረገባቸው 65 የአለማችን አገራት መካከል ነጻ የተባሉት 18 ሲሆኑ፣ 28 አገራት የተወሰነ የኢንተርኔት ነጻነት እንዳለባቸው፣ 19 አገራት ደግሞ  የኢንተርኔት ነጻነት እንደሌለባቸው ተረጋግጧል፡፡

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ የለሊቱ የቪኦኤ ሚስጥራዊ ጉባኤ

በአበበ ገላው (ትርጉም በታኬ)

በቅርቡ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶ/ር ቴዎድሮስ አድኃኖም እና አምባሳደር ግርማ ብሩ በዩናይትድ ሰቴትስ አሜሪካ ዋሽንግተን ዲ.ሲ በሚገኘው የቪኦኤ ሬዲዮ ጣቢያ በሌሊት በድብቅ በመግባት ሕጋዊ ስልጣኑ ሳይኖራቸው ስለስርጭቱ ለጥቂት የድርጅቱ ሠራተኞች የኢዲቶሪያል መመሪያ ከሰጡ በኋላ በአሜሪካ ድምጽ የአማርኛው አገልግሎት (ቪኦኤ) እና በህወሀት የበላይነት በሚመራው የኢትዮጵያ መንግስት መካከል ያለው የሻከረ ግንኙነት ያልተጠበቀ አቅጣጫ ይዟል፡፡ ስብሰባው በሚስጥር በተካሄደበት ጊዜ የአምባገነኑ አገዛዝ ባለስልጣኖች ለሬዲዮ ስርጭቱ ሰራተኞች ስለዜና አዘጋገብ፣ እንደዚሁም ደግሞ ወደ ኢትዮጵያ ስለሚተላለፈው የስርጭት ጥራት ሁኔታ መመሪያ የመስጠት ሙከራ ያደረጉ ለመሆናቸው ከታመኑ ምንጮች በተገኙ መረጃዎች ተረጋግጧል፡፡

Tedros Adhanom and Ambassador Girma Birru

ከቪኦኤ ባለስልጣኖች ዕውቅና ውጭ በሚስጥር እንዲከናወን የተደረገው ይህ ስብሰባ የተካሄደው በዋሽንግተን ዲ.ሲ 330 ኢንዲፔንደንስ አቬኑ በሚገኘው በቪኦኤ የአፍሪካ ቀንድ ክፍል የኢዲቶሪያል የስብሰባ ቢሮ ውስጥ ነው፡፡ ይህ ድብቅ ስብሰባ እንዲካሄድ የተደረገው ባልተለመደ እና እንግዳ በሆነ መልኩ በሰንበት፣ እ.ኤ.አ መስከረም 26 ቅዳሜ ዕለት ከስራ ሰዓት ውጭ ከምሽቱ 1 ሰዓት እስከ ምሽቱ 3 ሰዓት ድረስ ነበር፡፡

የአሜሪካ ድምጽ የአማርኛው አገልግሎት ፕሮግራም ስርጭት ባልደረባ በሆነው በሰለሞን አባተ ግንባር ቀደም አደራጅ እና አስተባባሪነት እንዲሁም በአሜሪካ ድምጽ የትግርኛው ፕሮግራም ስርጭት ባልደረባ በሆነው በበትረ ስልጣን ተባባሪነት በዲፕሎማቶቹን እና ሁለት ቴክኒሸኖችን ጨምሮ ሰባት የቪኦኤ የስራ ባልደረቦችን ባካተተው ቡድን መካከል የተካሄደው ስብሰባ ተገቢነት የሌለው እና አግባብ ያልሆነ ተብሎ ተፈርጇል፡፡

አገዛዙ በሀገር ውስጥም ሆነ በውጭ ጠንካራ ትችት የሚያቀርቡትን ብዙሀን መገናኛዎች ጸጥ ለማድረግ እና የስርጭት አድማሳቸውን ለመገደብ እያራመደ ካለው አውን ያወጣ ስልት አንጻር ከፍተኛ በሆኑ የአምባገነኑ አገዛዝ ባለስልጣኖች እንደዚህ ያለ ስብሰባ መካሄዱ እና ስለቪኦኤ እያራገቡት ያለው የጥላቻ አጀንዳ በሕጋዊ መልኩ ስልጣን የተሰጠውን የመተዳደሪያ ደንብ እና የጋዜጠኝነት ስነምግባርን የሚጥስ ዕኩይ ድርጊት እንደሆነ ተደርጎ ይታሰባል፡፡

ይህ በቅሌት የታጀበ ስብሰባ እንዲካሄድ የተፈለገበት ዋናው ምክንያት አገዛዙን በየዓመቱ የፕሬስ ነጻነትን በመደፍጠጥ የቀዳሚነቱን ቦታ ከሚይዙት የፕሬስ ደፍጣጮች መካከል እያስመደበው የመጣ ስለሆነ ይህንን ሁነት ለማደብዘዝ ሲባል በጋዜጠኞች እና በጨቋኙ መንግስት መካከል መተማመን እና ትብብር እንዲኖር ለማድረግ ከመፈለግ የመነጨ ክስተት ነው፡፡ በስብሰባው ወቅት በተደረገው ንግግር የህወሀት ተወካይ ይህንን አጋጣሚ በመጠቀም ወደ ኢትዮጵያ የሚደረገውን የሬዲዮ ስርጭት ጥያቄ በማቅረብ እና በድብቅ የማስፈራሪያ ድርጊቶችን በመፈጸም በስርጭቱ ላይ ከፍተኛ የሆነ ተጽዕኖ መፍጠር እና የስርጭቱንም ይዘት ማስቀየር እንደሚቻል የቀረበውን ሀሳብ ለደህንነታቸው ሲባል አንድ ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ ሰው ይፋ አድርገዋል፡፡

እየተካሄደ የነበረው ስብሰባ ውይይት በመቅረጸ ድምጽ እንዳይቀዳ እግድ የጣለው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር በማያያዝም ቪኦኤ ጠንካራ የሆኑ ትችቶችን ለሚያቀርቡት የአየር ጊዜ በመስጠት እና ዓላማቸውን በኃይል ለማስፈጸም የሚንቀሳቀሱትን አመጸኞች ግንቦት ሰባትን ጨምሮ መንግስትን ለመገልበጥ ለሚደረገው እንቅስቃሴ ድጋፍ ያደርጋሉ በማለት ቅሬታውን አሰምቷል፡፡ ሚኒስትሩ በመቀጠልም ቪኦኤ “አሉታዊ ትረካ” ላይ ትኩረት በማድረግ የሚሰራ ሜዲያ ነው በማለት ቅሬታውን ገልጿል፡፡

የአምባገነን ምልከታ፣
ጥቂት ጥያቄዎችን ከወሰደ በኋላ ሚኒስትሩ ባለፈው ሐምሌ ወር ለቪኦኤ የሰጠው ቃለመጠይቅ የመንግስትን ፖሊሲ በሚተቹ ትችት አቅራቢዎች በቪኦኤ በኩል ትችት የቀረበ በመሆኑ ቅሬታ የተሰማው መሆኑን ግልጽ አድርጓል፡፡ እንደዚህ ያሉ ተሞክሮዎች ስህተት ናቸው፣ እናም መደረግ አልነበረባቸውም በማለት ለተሰብሳቢዎቹ ተናግሯል፡፡

አወዛጋቢ በነበረው የቪኦኤ ቃለመጠይቅ የህወሀት ሚኒስትር ካለው እውነታ በተጻረረ መልኩ ፕሬዚዳንት ኦባማ የኢትዮጵያ የመጨረሻው ምርጫ ዴሞክራሲያዊ ስለሆነ አጽድቆታል በማለት የተዛባ መረጃ አሰራጭቷል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ባለፈው ዓመት የመን ላይ የታፈነው እና በኢትዮጵያ ውስጥ ስቃይ እየተፈጸመበት ያለው ታዋቂው አመጸኛ አንዳርጋቸው ጽጌ መልካም የሆነ አያያዝ እየተደረገለት እንደሆነ እና እንዲያውም የልማት ፕሮጀክቶችን በማድነቅ ላይ እንደሚገኝ ይፋ አድርጓል፡፡ እንደዚሁም ደግሞ አንዳርጋቸው መጽሐፍ እንዲጽፍ ላፕቶፕ የተሰጠው መሆኑን ተናግሯል፡፡

ሚኒስትሩ እና አምባሳደሩ ሁለቱም መንግስት ከቪኦኤ ጋር ተቀራርቦ ለመስራት ያለውን ዝግጁነት እና ጋዜጠኞች አዎንታዊ ትረካ እና ስዕሎችን አጉልተው ማውጣት እንዳለባቸው እና አስፈላጊ በሆነ ጊዜ ሁሉ ድጋፍ እና እገዛ እንደሚያደርግላቸው ግልጽ ያደረጉ መሆናቸውን ምንጮቹ ይፋ አድርገዋል፡፡

ባለስልጣኖቹ ሰባት የቪኦኤ የስራ ባልደረቦች ያሉበትን ስብሰባ እየመሩ ባሉበት ጊዜ ሲሰጡት በነበረው መመሪያ ቪኦኤ ወደ ኢትዮጵያ በሚያስተላልፈው የሬዲዮ ስርጭት ላይ ልዩ ትኩረት አድርጎ መዘገብ ያለበት ከአሉታዊ ትረካዎች እና አስተያየቶች፣ እንዲሁም አንገብጋቢ ከሆኑ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች፣ ስልጣንን ከሕግ አግባብ ውጭ መጠቀም እና ከሙስና ይልቅ አዎንታዊ እና የልማት ስራዎችን መዘገብ እንደሚያስፈልግ አስረግጠው ተናግረዋል፡፡

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ በዚህ ብቻ ሳያቆም ንግግሩን ቀጥሎ ባለፉት ጥቂት ዓመታት ተገኙ ያላቸውን ጥቂት ዕድገት እና መሻሻሎች ከዘረዘረ በኋላ ጋዜጠኞቹ እራሳቸው እውነታውን በግንባር ወደ ሀገር ቤት በመሄድ ማየት እንዳለባቸው የግብዣ ጥሪ አስተላልፎላቸዋል፡፡

የኢትዮጵያ መንግስት ስለቪኦኤ ውስጣዊ የስራ እንቅስቃሴ ቀጣይነት ባለው መልኩ መረጃ እንደሚቀበል ቀጥታ ባልሆነ መንገድ ይፋ አድርገዋል፡፡ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ለጋዜጠኞቹ በየስራ ክፍሎቻቸው ማን ምን እንደሚሰራ እያንዳንዱን ነገር እንደሚያውቁ እና እነዚህ ጋዜጠኞችም ከዚህ አንጻር እራሳቸውን እንደገና በጥንቃቄ መመርመር እንዳለባቸው በይፋ የተናገረ መሆኑ ተዘግቧል፡፡

አንድ ስሙ እንዳይታወቅ የፈለገ የስብሰባው ተሳታፊ የሆነ የቪኦኤ የስራ ባልደረባ እንዲህ በማለት ሀሳቡን ገልጿል፣ “በእንደዚህ ዓይነት ስራዎች ላይ ልንከተላቸው የሚገቡ ሕጎች፣ የአሰራር ሂደቶች እና የሙያ ስነምግባሮች አሉ፡፡ በአሁኑ ጊዜ ምሽት ከመሆኑ አንጻር ሰራተኛው ሁሉ ለመኝታ ወደየቤቱ በሄደበት ሁኔታ አንድ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር በድርጅቱ ኢዲቶሪያል ክፍል ውስጥ በመገኘት ጥቂት የድርጅቱ ሰራተኞችን በመያዝ እንደዚህ ያለ ስብሰባ ማካሄድ በድርጅቱ ታሪክ ውስጥ ተደርጎ የማያውቅ አዲስ እና ያልተለመደ ነገር ነው“ በማለት ሀሳቡን ግልጽ አድርጎ አቅርቧል፡፡ ምንጩ ከዚህ ጋር በማያያዝ እንደገለጸው የአሰራር የዕዝ ሰንሰለቶችን በመጣስ የቪኦኤን ነጻነት በገደበ መልኩ እየተካሄደ ባለው በዚህ ስብሰባ ላይ እኔ እና መሰል ባልደረቦቼ በእጅጉ አዝነናል የሚል መልዕክት እንዳስተላለፈ ምንጮች ዘግበዋል፡፡

የስብሰባ ምንጮች እንዲህ የሚል ግልጽ የሆነ መልዕክት የተላለፈ መሆኑን ጠቁመዋል፣ “ስለቪኦኤ የአዘጋገብ ፕሮግራም እና ስለሌሎች ማናቸውም ጉዳዮች ለመወያየት እና ቅሬታን ለማቅረብ ሲፈለግ ባለስልጣኖች የኢዲቶሪያል ስብሰባ ለማድረግ የዩኤስ ፌዴራል መንግስት ሰራተኛ የሆኑትን የተመረጡ ጥቂት የቪኦኤ ጋዜጠኞች ቡድንን በምሽት ስብሰባ ከመጥራት ይልቅ የተለመደውን የአሰራር ስርዓት እና የዕዝ ሰንሰለት መከተል ነበረባቸው“ ብሏል፡፡

ሌላው ምንጭ በመቀጠል ከተሰብሳቢዎች የቀረበውን እንዲህ የሚለውን አስተያየት ይፋ አድርጓል፣ “እኛ ለቪኦኤ የምንሰራ ነጻ ጋዜጠኞች ነን፡፡ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ወይም አምባሳደሩ ወደ ቪኦኤ ዘልቀው በመምጣት ስራዎቻችንን እንዴት መስራት እንዳለብን የሚያስገድዱን ወይም ደግሞ መመሪያዎችን የሚሰጡን ለምንድን ነው? ይህ ዓይነት አካሄድ አግባብነት የሌለው የሙያ ጣልቃገብነት ጉዳይ ብቻ አይደለም፣ ሆኖም ግን ይህ ጉዳይ በእኛ የማሰብ ችሎታ እና ሙያዊ ብቃት ላይ የተሰነዘረ ግልጽ ዘለፋ ነው“ ብሏል፡፡ ይኸው ምንጭ፣ “ቪኦኤ ያለምንም ፍርሀት እና ከምንም ዓይነት አድልኦ በጸዳ መልኩ የመስራት ተግባሩን መቀጠል እንዳለበት ጠንካራ እምነት አለኝ“ ብሏል፡፡

ቪኦኤ እንደ ነጻ የሜዲያ ተቋም በትክክለኛ እና በእውነት ላይ የተመሰረተ ዘገባን የማቅረብ ተልዕኮን የሚያራምድ ጠንካራ የሆነ ኃላፊነትን የተሸከመ ድርጅት እንደሆነ አጽንኦ በመስጠት ግልጽ አድርገዋል፡፡ ተሰብሳቢዎቹ “ሕግን መሰረት አድርጎ የተቋቋመውን እና ሕጋዊ ስልጣን ያለውን የቪኦኤን የመተዳደሪያ ደንብ እና የሙያ ስነምግባር ማንም ድርድር ሊያደርግበት እና ሊለውጠው አይችልም“ ብለዋል፡፡ ይኸ ቅንነት የጎደለው ስብሰባ “አምባገነኑ እየተመለከታችሁ ነው“ የሚል ቀጥተኛ ያልሆነ እንደምታ ይኖረዋል በማለት ሌላው ምንጭ ጠቁሟል፡፡ ለስራ በጣም ምቹ የሆነ እና ደህንነቱ አስተማማኝ በሆነ በዚህ የፌዴራል መንግስት ህንጻ ውስጥ እንደዚህ ያለ ክስተት እንዴት እና ለምን እንደተፈጠረ ጥቂት ሰዎች በጣም ያሳሰባቸው ስለሆነ ድርጊቱ ለምን እንደተፈጸመ ሊያጣራ የሚችል አጣሪ አካል መቋቋም እንዳለበት አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡

ባለስልጣኖቹ ለቪኦኤ የስራ ባልደረቦች የኢትዮጵያ ኤምባሲ በሮች በሰፊው ተከፍተው የቆዩ መሆናቸውን ነግረዋቸዋል፡፡ ሆኖም ግን የተወሰኑ የስብሰባው ተሳታፊዎች ባለስልጣኖቹ የመጡት በስቱዲዮ በመገኘት ቃለመጠይቅ እንዲሰጡ ነው ተብሎ የተሳሳተ መረጃ በመሰራጨቱ እና እዚህ ከገባን በኋላ እየተደረገ ያለው የኢዲቶሪያል ሕገወጥ ስብሰባ መሆኑን በመመልከቴ ወደ ስሰብሰባው ከፍል በመግባቴ ጸጸት ተሰምቶኛል በማለት ተናግሯል፡፡

የኢትዮ-አሜሪካ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት የሆኑት አበበ ኃይሉ ከዚህ ጉዳይ ጋር በተያያዘ መልኩ የተሰማቸውን ሀዘን እና እምነት ማጣት እንዲህ በማለት ግልጽ አድርገዋል፣ “በአሁኑ ጊዜ በቪኦኤ ላይ እየተደረገ ያለው ድርጊት የቪኦኤን ታማዕኒነት የሚያጠፋ ስለሆነ ድርጊቱ በድርጅቱ ህልውና ላይ ያነጣጠረ በጣም አስፈሪ ሁኔታ ነው፡፡ እንደ ኢትዮ-አሜሪካውያን ዜጎች ለዚህች ታሪካዊ ለሆነች ሀገር ለዩናይትድ ስቴትስ አሜሪከ ግብር ከፋይ ሕዝቦችም ነን“ ብለው ነበር፡፡

አቶ አበበ አስተያየታቸውን በመቀጠል ቪኦኤ እና የቪኦኤ የስራ ባልደረቦች በሌላ በውጭ ኃይል ጣልቃገብነት የመጦዝ እና የመታዘዝ ዕድል እንዳይገጥማቸው የሜዴያን ነጻነት ለማስከበር ወጥተን መጠየቅ እንዳለበን ምክንያት የሚፈጥር ጉዳይ ሆኗል፡፡ በመጨረሻም ይኸ ድርጊት በጠቅላይ የምርመራ ጽ/ቤት/Inspector General መመርመር እንዳለበት ጠንካራ እምነነት አለኝ በማለት ጥቆማ አቅርበዋል፡፡

የውጥረት ታሪክ፣
በኢትዮጵያ ላይ ተንሰራፍቶ የሚገኘው አገዛዝ ከሕግ አግባብ ውጭ ግድያ በመፈጸም፣ በዜጎች ላይ ስቃይ በማድረስ፣ ስልጣንን ከሕግ አግባብ ውጭ በመጠቀም፣ በሙስና በመዘፈቅ፣ ሕዝብን በጅምላ በማፈናቀል፣ በመሬት ቅርምት ወረራ በመረባረብ፣ በዜጎች ላይ አድልኦ በመፈጸም እና በሌሎች ዓይነት ጅምላ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች እና በሰዎች ልጆች ላይ በሚፈጽማቸው ሰብአዊ ወንጀሎች በሰፊው ይተቻል፡፡

እ.ኤ.አ በ2005 የተከሄደውን ሀገር አቀፍ ምርጫ ተፈጥሮ የነበረውን ውዝግብ ተከትሎ አገዛዙ በጉዳዩ ላይ የዩኤስ መንግስት ጣልቃ ገብቶ ክሱ ውድቅ እስከሚደረግ ድረስ በአራት የቪኦኤ ነባር ጋዜጠኞች ከሌሎች በርካታ ተወንጃዮች ጋር በመጨመር የሀገር ክህደት እና የዘር ማጥፋት መፈጸም የሚል የውንጀላ ክስ ተመስረቶባቸው ነበር፡፡

እ.ኤ.አ ሰኔ 2011 የቪኦኤን እና የሌሎች ዓለም አቀፍ የዩኤስ ዜና ማሰራጫዎችን የሚገመግም ሶስት አባላትን ያካተተ የሬዲዮ ስርጭቱ የቦርድ አመራሮች/Broadcasting Board Governors (BBG) ቡድን ኢትዮጵያን ለመጎብኘት ሄዶ ነበር፡፡ በዚያን ጊዜ በስልጣን ላይ የነበረው አገዛዝ በቬኦኤ የስርጭት አድማስ እንዳያገኙ እና ቃለመጠይቅም እንዳይደረግላቸው የሚፈለጓቸውን ሰዎች ስም ዝርዝር እና ሌሎች አመጽ ያካሂዳሉ ብለው የፈረጇውን ድርጅቶች ዝርዝር ያካተተ ረዥም ቅሬታ አቅርበው ነበር፡፡
የቀድሞው የአፍሪካ ቀንድ የቪኦኤ ዋና ኃላፊ የነበሩት ዴቪድ አርኖልድ አገዛዙ ትችት ለሚያቀርቡት እና አመጽን ለሚያራምዱት ግለሰቦች እና ድርጅቶች ቪኦኤ መድረክ እንዳይሰጣቸው ይፈልጋል በማለት ግልጽ አድርገው ነበር፡፡ ሆኖም ግን አርኖልድ ሀሳባቸውን ግልጽ ካደረጉ በኋላ ግልጽ ባልሆነ ምክንያት ከስራቸው እንዲታገዱ ተደርገዋል፡፡

እ.ኤ.አ በ2010 አሁን በህይወት የሌለው አምባገነኑ መለስ ዜናዊ ቪኦኤን ሀገሪቱን ካወደመው እና የዘር ማጥፋት ሰይጣናዊ የቅስቀሳ ድርጊት በማድረግ በመጥፎነቱ ከሚታወቀው ከሩዋንዳው ሬዲዮ ሚሌ ኮሊንስ ጋር አንድ ዓይነት ነው በማለት ድምዳሜ ሰጥቷል፡፡
ይህንንም በማስመልከት በኢትዮጵያ የሚሰራጨውን የቪኦኤን የስርጭት ሞገድ ካፈነ/ጃም ካደረገ በኋላ አምባገነኑ መለስ እንዲህ የሚል ዲስኩር አሰምቶ ነበር፣ “በብዙ መንገድ የቪኦኤ ድምጽ የአማርኛው አገልግሎት የመጫረሻ ዝቅተኛ የሆነውን የጋዜጠኝነት ስነምግባርን የማያሟላ እና የሁከት ፕሮፓጋንዳ የሚነዛ የሩዋንዳውን የሬዲዮ ኮሊንስን ተሞክሮ እንዳለ የሚተገብር ሜዲያ እንደሆነ ከብዙ ጊዜ ጀምሮ እምነት አድርቦብናል“ ብሎ ነበር፡፡

ይኸው የውንጀላ ክስ በዩናይትድ ስቴትስ አሜሪካ የመንግስት መምሪያ “መሰረተ ቢስ እና ቆጥቋጭ” በሚል ውድቅ ተደርጎበታል፡፡ የአሜሪካ የመንግስት መምሪያ ለቀረበው የውንጀላ ክስ ምላሽ እንዲሆን በማሰብ ይልቁንም መንግስት የሰው ልጆች መሰረታዊ መብት የሆነውን ሀሳብን በነጻ የመግለጽ መብት እንዲያከብር ጠይቋል፡፡

የሙያ ስነምግባር መርሆዎች፣
የቪኦኤ የሙያ የስነምግባር መርሆ በግልጽ እንደሚያስቀምጠው የቪኦኤ ቋሚ ወይም ደግሞ የኮንትራት ሰራተኞች በተለዬ ምክንያት በልዩ ትዕዛዝ በተላለፈ የስልጣን ተዋረድ ካልሆነ በስተቀር ለሌላ መንግስት ወይም ደግሞ የሜዲያ ተቋም ሊያገለግሉ አይችሉም፡፡ ከዚህም በተጨማሪ በጨቋኝ አገዛዝ መዳፍ ስር ወድቀው ለሚሰቃዩ ህዝብች ትክክለኛ መረጃ እና ዜና በማቅረብ ረገድ ላይ ከፍተኛ ትኩረት ሰጥቶ ይሰራል፡፡ የቪኦኤ የጋዜጠኝነት የስነምግባር መርሆ እንዲህ በሚለው ጉዳይ ላይ ትኩረት ሰጥቶ ይሰራል፣ “ቪኦኤ በነጻነት እና በዴሞክራሲ ላይ ሙሉ እምነት እና ተስፋ ላላቸው ህዝቦች ብሄራዊ ጥቅምን ለመጠበቅ እና ለዓለም ህዝብ በተለይም ደግሞ ትክክለኛ መረጃ ለማያገኙት ህዝቦች ትክክለኛ፣ ሚዛናዊ እና የተሟላ መረጃ እንዲያገኙ ያደርጋል“ ይላል፡፡

ባለፈው ዓመት በህወሀት የበላይነት የሚመራው አገዛዝ የተሟሉ የሳቴላይት መሳሪያዎችን በመጠቀም እና ዓለም ሕጎችን በማክበር ትክክለኛ የሆኑ የአሰራር ስርዓቶችን በመከተል እና በስራ ላይ በማዋ ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ መረጃዎችን እና ዜናዎችን የሚያሰራጩትን ዓለም አቀፍ ሜዲያዎች ስርጭትን ቪኦኤን ጨምሮ በማፈኑ/ጃም በማድረጉ ቢቢጂ/BBG ከቢቢሲ/BBC፣ ዶቼ ዎሌ/Deutsche Welle እና ከፍራንስ 24/France 24 ጋር በጋራ በመሆን አገዛዙ ሰብአዊ መብቶችን በሰፊው እየደፈጠጠ ነው በማለት አውግዘውታል፡፡

እነዚህ ዓለም አቀፍ የብዙሀን መገናኛ ዘዴዎች በጋራ ባወጡት መግለጫ እንዲህ የሚል ተካትቶ ይገኛል፣ “ይህ ጣልቃገብነት ዓለም አቀፍ የሬዲዮ ሞገድ የስርጭትን አጠቃቀም እና የሳቴላይት ስርዓቱ የሚመሩባቸውን ደንቦች በተጻረረ መልኩ የተባበሩት መንግስታት የሰብአዊ መብቶች ድንጋጌ አንቀጽ 19ን በመተላለፍ ግለሰቦች ነጻ የሜዲያ ሽፋን መረጃዎችን እንዳያገኙ እገዳ ጥሏል ወይም ጃም አድርጓል“ የሚል የጋራ መግለጫ አውጥተዋል፡፡

የቢቢሲ አገልግሎት ቡድን ተጠባባቂ ዳይሬክተር የሆኑት ሊሊያን ላንዶር የአገዛዙን አፋኝነት በማስመልከት እንዲህ ብለው ነበር፣ “ግልጽ ባልሆነ ምክንያት የዓለም አቀፉን የዜና ማሰራጭ አውታሮች አውከዋል፡፡“

የስትራቴጂ ለውጥ ማድረግ፣
ለጠንካራ ትችቶች እና ለሜዲያ ሽፋን ጠላት በመሆን በስልጣን ላይ ያለው አገዛዝ የቪኦኤ ድምጽ የአማርኛው አገልግሎት ፕሮግራምን ለሁለት አስርት ዓመታት ያህል በእራሱ ስልጣን ስርጭቱን ለማቋረጥ እና ለመዝጋት ያለ የሌለ ጥረት ሲያደርግ ቆይቷል፡፡ ይህንን ያህል ጥረት በኢትዮጵያ የቪኦኤን አጭር ሞገድ እና የሳቴላይት ስርጭት ለማፈን/ጃም ለማድረግ እንዲሁም የተለያዩ ዲፕሎማሲያዊ ተጽዕኖዎችን ሲያደርግ የቆዬ ቢሆንም ቅሉ ዓላማ አድርጎ የተነሳበትን ግብ ሳይመታ እና የታለመውን ውጤት ሳይስገኝ የውኃ ላይ ኩበት ሆኖበት ቀርቷል፡፡

እ.ኤ.አ በ2015 ዓለም አቀፉ የጋዜጠኞች ተከላካይ ድርጅት/CPJ የጽሁፍ እና የሕትመት ምርመራ የሚደረግባቸውን 10 ዋና ዋና ጨቋኝ መንግስታት የደረጅ ዝርዝር ባወጣው ዓመታዊ ዘገባ ኢትዮጵያ ከኤርትራ፣ ሰሜን ኮሪያ እና ከሳውዲ አረቢያ በመቀጠል በ4ኛነት ደረጃ ላይ ተቀምጣለች፡፡ የCPJ የምርመራ ውጤት ዘገባ እንደሚያመለክተው “ከፍተኛ የሆነ የህትመት እና የሜዲያ ምርመራ ከሚያደርጉ ሀገሮች መካከል ኢትዮጵያ በ4ኛነት ደረጃ ላይ የምትገኝ በመሆኗ ምክንያት የጋዜጠኞች እስራት በገፍ የሚከናወን በመሆኑ በርካታ ጋዜጠኞች ሀገራቸውን እየተው ለመሰደድ ተገደዋል፡፡ እ.ኤአ. በ2014 በጦማሪያን እና በነጻው ፕሬስ ህትመት አዘጋጆች ላይ ከፍተኛ የሆነ የኃይል እርምጃ በመወሰዱ ምክንያት ከ30 በላይ የሚሆኑ ጋዜጦች ለስደት ተዳርገዋል፡፡“ CPJ ማንኛውንም ትችት ማቅረብ እና ሀሳብን በነጻ መግለጽ ወንጀለኛ የሚያደርገውን እ.ኤ.አ በ2009 የወጣውን የጸረ-ሽብር አዋጅ አውግዞታል፡፡

አገዛዙ ይህንኝ ያህል ጥረት እያደረገ የህወሀት የብዙሀን መገናኛ ዘዴዎችን የማፈን እና በጋዜጠኞች እና በሰላማዊ አመጸኞች ላይ የሀሰት የውንጀላ ክሶችን ቢመሰርትም ያሰበው እና የሚያደርገው ሁሉ የእምቧይ ካብ እየሆነ ፍሬ ሳያፈራ ቀርቷል፡፡ ሆኖም ግን አሁን በቅርቡ ደግሞ የእስትራቴጂ ለውጥ በማድረግ በቀጥታ ከቪኦኤ ጋዜጠኞች እና ከሌሎች ነጻ የሜዲያ ተቋማት ጋር በግንባር በመገናኘት እያደረገ ያለው ንግግር አገዛዙ ከውስጥ የግንኙነት መረብ አድማሱን እያሰፋ እና እያጠናከረ እንዲሁም ካሮት እና ዱላ እያሳየ እያስፈራራ ያለው ዕኩይ ድርጊት ያለምንም ጥርጥር በአፍሪካ ቀንድ የቪኦኤ ክፍል ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ማሳደሩ አይቀርም፡፡ ከዚህም በላይ ከጋዜጠኝነት ስነምግባራቸው በተዛነፈ መልኩ ካሮት እየተሰጣቸው ለርካሽ ጥቅም በማጎብደድ መሳሪያ ሆነው የሚያገለግሉ ሊኖሩ ይችላሉ የሚል ግምት አለ፡፡

ቪኦኤ በሚስጥር ስለተካሄደው ስብሰባ ምንነት እና በኢትዮጵያ የቪኦኤ የሬዲዮ ስርጭት ላይ የሚኖረው አሉታዊ ተጽዕኖ ከግምት ውስጥ በማስገባት በስብሰባው ክፍልም የተደረገውን ውይይት በማስመልከት በዚህ ዘገባ አጠናቃሪ ለቀረቡለት ጥያቄዎች እስከ አሁን ድረስ ምላሽ አልሰጠም፡፡